ለኑዛዜ ሳልበቃ ልሳኔን
ይዝጋው!
የአፍሪካ መሪዎች ወደ ስልጣን ሲመጡ
መፈፀም ያለባቸው ቃለ መሃላ በተለመደው
የመሃላ ሥነ ሥርዓት መጽሐፍ ቅዱስና
ቅዱስ ቁራን ጨብጠው ሣይሆን በሚከተሉት
የቃለ መሀላ ዓይነቶች መሆን አለበት፡፡
- ሕዝቤን ለረጅም ጊዜ ከላዩ ላይ ተጎልቸ
በሥልጣን ብልግና ባጉላለ እንደ
ሙሐመር ጋዳፊ “አይጥ” ባሏቸው
አይጥ ጉድጓድ ውስጥ ተወሽቄ ተይዠ
በጥይት ግንባሬን ልቦረቀስ!
- ህዝቤን ብንቅና ባንጓጥጥ እንደ ሁሴን
ሙባረክ በፈነጨሁባት አገር ተዋርጄ
በቃሬዛ ተገፍቼ ፍ/ቤት በመቅረብ 20
ዓመት ያኮናነበኝ!
- ሕዝቤን እያነኩ ብገደል እንደ ኢዲያሚን
ዳዳና እንደ ሲያድባሬ ተዋርጄ ካገሬ
ተባርሬ ላገሬ አፈር ሳልበቃ በዚያው
ያስቀረኝ!
- በቀይ ሽብርና በነጭ ሽብር አቧድኘ
ባጨፋጭፍና እንደ አንበሳ ባገሳሁባት
አገር እንደ ውሻ ጅራቴን ሸጉጨ ወደ
ጎረቤት አገር ያስፈርጥጠኝ!
- እንደ ታምራት ላይኔ አለሁ አለሁ ብዬ
ስኳር ስልስ ወደ እስር ቤት ተወርውሬ
ከሥር ስለቀቅ ሃይማኖቴን ቀይሬ ካገር
ብን ብዬ ልጥፋ!
- “የሰው ምላስ እንኳን ሰው እንጨት
ያደርቃልና” ሕዝቤን በጎሳ፣ በነገድ . .
. ከፋፍዬ ባዳማ፣ የባሕር በር ባሰጣ፣
የአገሬን የአየር ክልል ባስደፍር፣
ታሪኳን አዋርጀ መቶ አመት ነው
ብል፣ ፍትሕን ባጓድል፣ ወጣቱን
ባሰድድ፣ በሐሰት እየወነጀልኩ ወደ
እስር ቤት ብወረወር ዜጎቼን ንቄ የሌላ
አገር ዜጎች ክብር ሰጥቼ ባሰፍር፣
የወርቅ መአድኗን ለአንድ ቱጃር
አሳልፌ ብሰጥ፣ በሃይማኖቶች ጣልቃ
ገብቸ ብበጠብጥ እንደ አፄ ስሱንዮስ
እግዚአብሄር ምላሴን ጎልጉሎ ለንዝ
እንኳን ሳልበቃ ልሳኔን ይዝጋው!!



