በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ላይ የተላለፈው የእሥራት ብያኔ ተኮነነ

ዓለምአቀፉ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት “Reporters sans frontieres” የኢትዮጵያ ከፍተኛ ፍርድቤት በሶሥት ጋዜጠኞች ላይ የእሥራት ብያኔ በማስተላለፍ የወሰደውን ዕርምጃ አጥብቆ ኮነነ። ድርጅቱ መንግሥት በመገናኛው አውታር ሠራተኞች ላይ ከባድ ቅጣት በመፈጸም በመቀጠሉ ያደረበትን ቁጣ በመግለጽ ጋዜጠኞቹ ነጻ እንዲለቀቁ ጠይቋል። ከፍተኛው ፍርድቤት የአዲስ ዜናና የሃዳር ጋዜጦች አዘጋጆች የነበሩትን አቶ ወሰንሰገድ ገብረ ኪዳንንና አቶ ዳዊት ከበደን መንግሥት ለመጣል አሢረዋል ሲል በመወንጀል በያንዳንዳቸው ላይ የአራት ዓመት እሥራት የበየነው ባለፈው ሣምንት መጀመሪያ ላይ ነው። ፓሪስ ላይ ተቀማጭ የሆነው የፕሬስ መብት ተሟጋች ድርጅት እንዳስታወቀው ሁለቱ ሰዎች ተይዘው የታሰሩት የግንቦቱን ምርጫ መጭበርበር መንስዔ በማድረግ ከተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ በኋላ ነበር። ሶሥተኛው ተከሳሽ የሣምንታዊው ልሣነ-ሕዝብ ጋዜጣ አዘጋጅ አቶ ጎሹ ሞገስ ደግሞ የአንድ የሕገ-ወጥ የፖለቲካ ድርጅት ዓባል ነው በመባል ባለፈው አርብ የአሥር ዓመት እሥራት ተበይኖበታል። “Reporters sans frontieres” ትናንት ማምሻውን በጉዳዩ ባወጣው መግለጫ እንደጠቀሰው በቅርቡ ጋዜጠኞችን ጨምሮ ለ 38  የፖለቲካ እሥረኞች የተደረገው ምሕረት በፕሬስ ሰዎች ላይ የሚካሄደው አግባብ የለሽ ቅጣት ያበቃል የሚል ተሥፋን አሳድሮ ነበር። ድርጅቱ ሣምንቱን እሥራት የተበየነባቸው ጋዜጠኞች የሃሣብ ነጻነት በመሠረቱ ሙሉ በሙሉ መከበር ሲገባው ነጻ መለቀቃቸው በመንግሥት ፈቃድ ላይ ጥገኛ መሆኑ አስከፊ እንደሆነም አስገንዝቧል።

Source: DW