የቅንጅትን ህልውና የሚያረጋግጡ ውይይቶች እየተካሄዱ ነው

ዘርፈ ብዙ መስዋእትነት የተከፈለበትና ለኢትዮጵያ ህዝብ የዴሞክራሲና የልማት ጥያቄዎች ተጨባጭ አማራጮችን ይዞ የቀረበውን ቅንጅትን ለማዳከም ውስጣዊና ውጫዊ አፍራሽ እንቅስቃሴዎች እተካሄዱበት ቢሆንም የፓርቲውን ህልውና የሚያረጋግጡ ውይይቶች በመደረግ ላይ መሆናቸውን አንድ የስራ አስፈጻሚ አባል ለዜና አገልግሎቱ ገለጹ፡፡

ባለፈው እሁድ ቸርችል ጎዳና ሊደረግ የነበረውን የላእላይ ም/ቤት ጉባኤ ያደናቀፉት ወገኖች ለጊዜው በሚያገኙት የወረት /capital/ ጥቅም ታውረው የአገራቸውን ህልውና ለጨቋኙ ስርአት ቢሰጡም ይህ የሚቀርበት ቀን በጣት የሚቆጠር ነው ብለዋል፡፡ ይህንና መሰል ችግሮችን የሚያስወግድ እቅድ መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል፡፡

የፊታችን እሁድ የሚካሄደውን የላእላይ ም/ቤት አባላት ጉባኤ አስመልክቶም ከፍተኛ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት እንደሚሆን አስታውሰዋል፡፡ የስራ አስፈጻሚው በተጓደሉ የላእላይ ም/ቤት አባላት ምትክ የሚመርጥበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል ብለዋል፡፡ ሊቀ መንበሩ በሌሉበት ይህ ሊፈጸም ይችላል ወይ በማለት ላነሳንላቸው ጥያቄም ህገ ደንቡ እንደሚፈቅድ ገልጸዋል፡፡

በትናንትናው እለት በፓርቲውየጽ/ቤት ሰራተኛ አቶ ግርማ አማረ ላይ የተፈጸመውን እገታ አስመልክቶም የዚህ አይነቱ ግብታዊ እርምጃ የሚጎዳው ፈጻሚውን ወገን መሆኑን አመልክተው ጉዳዩ ህገ ወጥ ተግባር ነበር በማለት የፓርቲውን እንቅስቃሴ እንደማያደናቅፈው አስታውቀዋል፡፡