የወያኔ ካድሬዎች የቤት ለቤት ቅስቀሳ ጀመሩ

በቀጣዩ ሚያዝያ ለሚካሄደው የአከባቢና የማሟያ ምርጫ የህዝቡን አመለካከት ለመገንዘብ በሚል በዛሬው እለት ከረፋዱ 4፡00 ሰአት ጀምሮ የወያኔ ካድሬዎች በአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች የቤት ለቤት ቅስቀሳ ጀመሩ፡፡

አብዛኛው ሰው ከጠዋት የአምልኮ ስፍራዎች ተመልሶ እቤት ይገኛል ተብሎ በሚታሰብበት ሰአት ቅስቀሳው የተጀመረ ሲሆን ህዝቡ ለካድሬዎቹ ይሰጥ የነበረው ምላሽ ተቃውሞ የነበረበት ነው ባይባልም ጉዳዩን በዝምታ በመመልከት የተወሰነና ለምርጫው ባለቤት ያለመሆኑን እንደሚያመለክት ከምልልሱ መረዳት ይቻል እንደነበር ሂደቱን የተከታተሉት ሪፖርተሮቻችን ዘገባ ያመለክታል፡፡

በቤት ለቤት ቅስቀሳው ወቅት ካድሬዎቹ ያነሷቸው ከነበሩት ጥያቄዎች የተወሰኑት ‹‹እስካሁን የነበረውን ኢኮኖሚያዊ እድገት የበለጠ ለማሳደግ መንግስት ምን ማድረግ አለበት ይላሉ?››፤ ‹‹የቤት እመቤቶች ኑሯቸውን ለማሻሻል በመንግስት ምን አይነት እገዛ ሊደረግላቸው ይገባል… (ይህ ጥያቄ የሚቀርበው ካድሬው በሩን ሲያንኳኳ የሚከፍቱት የቤት እመቤቶች ከሆኑ ነው)፤ በምርጫ 97 ያጋጠሙት ችግሮች እንዳይደገሙ ከመንግስት፤ ከህዝቡና ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን ይጠበቃል ብለው ያስባሉ?›› እና የመሳሰሉት የተለሳለሱ ውይይታዊ መሰል ጥያቄዎች ይገኙባቸዋል፡፡

በህዝቡ በኩል በምርጫ ታሪክ ይወክለኛል በሚል ሙሉ እምነት ጥሎ የመረጠው ቅንጅት ባለበት አሳሳቢ ችግር (ቀውስ) ውስጥ በመሆኑ፤ በቀጣዩ ምርጫ ራሳቸውን በተቃዋሚነት ካቀረቡት ጠንካራ ሊባሉ የሚችሉ ፓርቲዎች የተወሰኑት ብሄር ተኮር መሆናቸውና ህብረብሔራዊ ፓርቲዎቹም የጎላ ሚና መጫወት እንደማይችሉ በተለያዩ አጋጣሚዎች በማሳየታቸው፤ በጸጥታ ውስጥ ሆኖ የቅንጅትን ትንሳኤ የሚጠብቅ በመሆኑ፤ ለካድሬዎቹ መጠይቆች ተቃውሞ ማሳየቱ እርባና እንደሌለው የቆጠረ እንዳስመሰለው ሁኔታውን የተከታተሉት ሪፖርተሮቻችን ዘገባ ይጠቁማል፡፡