በዘር ማጥፋት ወንጀል በተከሰሱ ግለሰቦች ሞትና የተለያዩ የቅጣት ውሳኔዎች ተላለፈ

(የኢትዮጵያ የዜና አገልግሎት)
አዲስ አበባ, መጋቢት 26 ቀን 2000 (አዲስ አበባ)

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ ከተመሠረተባቸው 20 ግለሰቦች አምስቱን በሞት ሲቀጣ በቀሪዎቹ ላይ ደግሞ የዕድሜ ልክና የተለያዩ ውሳኔዎች ዛሬ አሳለፈ፡፡ ከተከሳሾች መካከል በተመሳሳይ ወንጀል በሌላ መዝገብ ተከሰው እየታየ የሚገኘው የሻምበል ለገሠ አስፋው ጉዳይ ቅጣቱ ተጣምሮ እንዲወሰን ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ተዘዋዋሪ እና የቀይ ሽበር ጉዳይ ችሎት የሞት ቅጣቱን ያሳለፈው በእነ ሻምበል ለገሠ አስፋው የክስ መዝገብ ጉዳያቸው በሌሉበት በታየው በኮሎኔል መንገሻ ሁንዴ፣ ሻምበል ታደሠ አጎናፍር፣ ኮሎኔል ዓለማየሁ እሳቱ፣ ሜጀር ማርቆስ ሰለሞን፣ እና ሜጀር ጌታሁን ካሣ በተባሉት ተከሳሾች ላይ ነው፡፡

በዚሁ መዝገብ ክስ ተመሥርቶባቸው ጉዳያቸው በሌሉበት የታየው ካፒቴን አቦነህ ነጋሽ፣ ሻምበል መሥፍን መንግሥቱ፣ ሻምበል ጌታቸው መንገሻ፣ ካፒቴን ዘበነ አስፋው እና ሌቴና ኮለኔል ጥላሁን ቦጋለ የተባሉት ደግሞ እያንዳንዳቸው በዕድሜ ልክ ፅኑ እሥራት እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ ወስኖባቸዋል፡፡

እንዲሁም ምክትል መቶ አለቃ ጀልቻ ደራ፣ ካፒቴን ደረጀ አብዲሣ፣ ካፒቴን አሰፋ ተገኝ፣ ሜጀር ወንድወሰን በቀለ እና ሌቴና ኮሎኔል የሺጥላ መርሻ የተባሉት ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በ25 አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ጉዳያቸው ባሉበትና በማረሚያ ቤት ሆነው እየተመላለሱ ከተከራከሩት አምስት ተከሳሾች ኮሎኔል ብርሃነመስቀል ኃይሌ በሞት ሊቀጡ የነበረው በ25 አመት፣ ኮሎኔል ግርማ አስፋው ከዕድሜ ልክ በ20 አመት ፅኑ እስራት፣ ኮሎኔል ሰለሞን ከበደ እና ሻምበል ክፍሌ ውቤ ደግሞ ከ25 አመት በ19 አመት ፅኑ እስራት ቀጥቷቸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን ያሻሻለው በ1997 የወጣው አዲሱ የወንጀለኛ መቅጫ ተከሳሹን ሊጠቅም በሚችል የህግ አግባብ ቅጣቱ እንዲወሰን ስለሚደነግግና ተከሳሾቹም በሕግ አደባባይ ቀርበው በመከራከራቸውና ያቀረቡትን የቅጣት ማቅለያ አስተያየት ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ ፍርድ ቤቱ በውሳኔው አትቷል፡፡

ሻምበል ለገሠ አስፋው የተባሉት ከፍተኛ የደርግ አመራር የነበሩ ተከሳሽ ጉዳይ በእነ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የዘር ማጥፋት የወንጀል ክስ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲታይ ቆይቶ ውሳኔ ከተላለፈበት በኋላ በልዩ ዓቃቤ ሕግና በተከሳሾቹ ይግባኝ ጠያቂነት በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመታየት ላይ ስለሚገኝ ቅጣቱ ተዳምሮ እንዲሰጥ በማለት ትእዛዝ አስተላልፏል፡፡

ፍርድ ቤቱ በተከሳሾቹ ላይ የሞት እና የፅኑ እስራት ቅጣቱን የወሰነው በደርግ ዘመን በትግራይ ክፍለሀገር በተለያዩ ጊዜያት የእርዳታ እህል ለመቀበልና ወደገበያ ወጥተው በተሰባሰቡ ሠላማዊ ሰዎች ላይ ተዋጊ ሚግ አውሮፕላን እና ሔሊኮፕተር በማሠማራት በመትረየስ፣ በቦምብና በተቀጣጣይ ፈንጂ በመደብደብ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሠላማዊ ሕዝብና እንስሳት ጨፍጭፈው መግደላቸውንና የአካል ጉዳት ማድረሳቸው በልዩ ዓቃቤ ሕግ ማስረጃ በመረጋገጡ መሆኑን ፍርድ ቤቱ በውሳኔው ገልጿል፡፡

ከተከሳሾቹ መካከል ኮሎኔል ብርሃነ መስቀል ኃይሌ፣ ኮሎኔል ግርማ አስፋው፣ ሜጄር ጌታሁን ካሣና ኮሎኔል ዓለማየሁ እሳቱ የተባሉት ተከሳሾች በየካቲት 1975 ዓ.ም በቀድሞ ትግራይ ክፍለሀገር ጭላ ከተማ ፈራሲት በተባለ ገበያ ቦታ የነበሩ በሺ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች በተዋጊ አውሮፕላኖች በተቀጣጣይ ፈንጂ በመደብደብ አሰቃቂ ወንጀል መፈፀማቸው በማስረጃ እንደተረጋገጠባቸው ፍርድ ቤቱ በውሳኔው አመልክቷል፡፡

እንዲሁም ኮሎኔል መንገሻ ሁንዴ፣ ካፒቴን ዓለማየሁ እሳቱ፣ ሌተና ኮሎኔል የሺጥላ መርሻ እና ሻምበል ታደሠ አጎናፍር የተባሉት ተከሳሾች ደግሞ በትግራይ ክፍለሀገር ውቅሮ ከተማ መጋቢት ወር 1980 ዓ.ም እርዳታ ለመቀበል የወጣና ቁጥሩ ሦስት ሺህ በሚሆን ሰላማዊ ሕዝብ ላይ በተዋጊ ሚግ አውሮፕላን በቦምብና በተቀጣጣይ ፈንጂ እንዲደበደብ በማድረግ አሰቃቂ ሞትና የአካል ማጉደል ወንጀል መፈፀማቸውን ውሳኔው ገልጿል፡፡

ሻምበል ለገሠ አስፋውን ጨምሮ ኮሎኔል መንገሻ ሁንዴ፣ ምክትል የመቶ አለቃ ጄልቻ ዱራ፣ ሜጄር ወንድወሰን በቀለ፣ ሻምበል መሥፍን መንግሥቱ፣ ካፒቴን አስፋው ተገኝ፣ ካፒቴን ደረጀ አብዲሳ፣ ሻምበል ዓለማየሁ እሳቱ፣ ካፒቴን አቦነህ ነጋሽ፣ ሻምበል ጌታቸው መንገሻ፣ ኮሎኔል ሰለሞን ከበደ፣ ሻምበል ክፍሌ ውቤ፣ ሜጄር ማርቆስ ሰለሞን፣ ሜጀር ጌታሁን ካሣ፣ ካፒቴን ዘበነ አስፋው፣ ሌተና ኮሎኔል ጥላሁን ቦጋለ የተባሉት ተከሳሾች ሰኔ 15 ቀን 1980 ዓ.ም ለገበያ በተሰበሰበ 5 ሺህ ሕዝብ እንዳይሸሽ ዙሪያውን በሔሊኮፕተር ከበው ቦምብና ተቀጣጣይ ፈንጅ በማዝነብ መግደላቸውና የአካል ጉዳት ማድረሳቸው በማስረጃ መረጋገጡን ፍርድ ቤቱ በውሳኔው አመልክቷል፡፡

በሐውዜን ከተማ በተሰበሰበው ሠላማዊ ገበያተኛ ላይ በወረደው የቦምብ፣ የተቀጣጣይ ፈንጅ እና በመትረየስ በተካሄደው ጭፍጨፋ የሰውና የእንስሳት አካል መለየት በማይቻልበት አካላቸው ተቆራርጦ ከመደባለቁም በላይ በበርካታ ሰዎች ላይ የዕድሜ ልክ የአዕምሮ ጠባሳ ከመተውም ባሻገር የአካል ጉዳት መድረሱንም ምስክሮች መናገራቸውን ፍርድ ቤቱ በውሳኔው አብራርቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ጉዳያቸው በሌሉበት ታይቶ ውሳኔ የተላለፈባቸው ተከሳሾች የፌዴራል ፖሊስ ይዞ ለማረሚያ ቤት እንዲያስረክብና ማረሚያ ቤቱም በውሳኔው መሠረት እንዲያስፈፅም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

በሞት እንዲቀጡ ውሳኔ የተላለፈባቸው ተከሳሾች በአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ከፀደቀ በኋላ በማረሚያ ቤቱ ቅጥር ግቢ ሰብአዊ ርህራሄ በተሞላበት እንዲፈፀም ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡

ጉዳያቸው በማረሚያ ቤት ሆነው በመከታተል ላይ የነበሩት ተከሳሾች ውሳኔው እጃቸው ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ እንዲታሰብላቸው ካለ በኋላ የይግባኝ መብታቸው የተጠበቀ መሆኑንም ገልጿል፡፡