አቶ ተስፋዬ ኢሬሣ በሙስና ላይ ምስክር ለመሆን ሲዘጋጁ ተገደሉ

ብዙ ሳይታወቅ የተገደሉ ተስፋዬዎች አሉ

By Goolgule.com

June 17, 2013

murder

በነበራቸው የስራ ሃላፊነት በድብቅ መረጃ ሲያሰባስቡ ቆይተው ለመንግስት ካጋለጡ በኋላ ራሳቸውን ደብቀው የነበሩት አቶ ተስፋዬ
ኢሬሣ ምሳ እየተመገቡ ህይወታቸው ማለፉ ተሰማ። አቶ ተስፋዬ ሰኞ ለጸረ ሙስና ኮሚሽን የምስክርነት ቃላቸውን ለመስጠት
ከኮሚሽነር አሊ ሱሌማን ጋር ቀጠሮ ይዘው ነበር።

በቅርቡ ወደ ፌደራል መንግስት የተዛወሩት የጋምቤላ የቀድሞ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ኡሞት ኦባንግ፣ ከ83 ሚሊዮን ብር በላይ
አላግባብ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውን፣ እንዲሁም በክልሉ የሚፈጸሙትን የተጭበረበሩ የበጀት አፈጻጸሞችንና ምዝበራዎችን
የሚያጋልጡ ሰነዶችን በሚስጥር በማደራጀት ለኢህአዴግ ያቀረቡት አቶ ተስፋዬ አሟሟታቸው አነጋጋሪ ሆኗል።

አቶ ተስፋዬ ኢሬሳ ከፍተኛ ምስጢር ያላቸውን ሰነዶች በመያዝ ከመታሰራቸው በፊት መሰወራቸውን፤ “የቢሮ ሃላፊው ይዘው
የተሰወሩት መረጃ አቶ ኦሞት የፈረሙባቸው ከፍተኛ የገንዘብ ሰነዶችና ሙስና የተከናወነባቸው የኮንስትራክሽንና የተለያዩ
መረጃዎች ናቸው። መረጃዎቹ አንድ ቀን ህዝብ ፍርዱን ይሰጥ ዘንድ ይፋ ይሆናሉ” በሚል ጎልጉል ምንጮቹን ጠቅሶ በ (ጥቅምት
19፤2005/October 29, 2012) መዘገቡ ይታወሳል።

ቀደም ሲል የጋምቤላ የፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ከላይ የተጠቀሰውን የሙስና ወንጀል በማጋለጣቸው ጋምቤላ
መኖር ሳይችሉ ቀርተው ራሳቸውን ሸሽገው ለመኖር ተገደው እንደነበር የሚያውቋቸው ለጎልጉል አስረድተዋል።

“አቶ ተስፋዬ ሙስናን በማጋለጣቸው በፍርሃቻ ራሳቸውን ደብቀው ሊኖሩ አይገባም” በማለት ኢህአዴግ ከለላ እንደሚሰጣቸው ቃል
በገባላቸው መሰረት ከተሸሸጉበት የወጡት አቶ ተስፋዬ ሰንጋተራ ትንሳዔ ሆቴል ከጋምቤላ ልጆች ጋር መገናኘት ይጀምራሉ።

ባለፈው ሳምንት ከፌዴራል የጸረ ሙስና ኮሚሽነር አሊ ሱሌማን ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ ከያዙ በኋላ ኮሚሽነሩ በድንገት ለለቅሶ ወደ
ጎንደር በመሄዳቸው ቀጠሮው ለሳምንት ይራዘማል። ለሰኞ (ሰኔ10፤2005) አዲስ ቀጠሮ ይይዛሉ።

በስልክ ያነጋገርናቸው ትንሳዔ ሆቴል አካባቢ እንደነበሩና ለጉዳዩ ቅርበት እንዳላቸው የሚገልጹ የጋምቤላ ተወላጅ የስራ ሃላፊ
እንዳሉት አቶ ኦሞት ኦባንግ ለአቶ ተስፋዬ ስልክ ደውለው ነበር። አቶ ተስፋዬ ህይወታቸው ከማለፉ ሁለት ቀን በፊት የቀድሞው
የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ኦሞት በስልክ ተማጽንዖ አቅርበው ነበር።

አቶ ኦሞት “እውነት ነው ጸረ ሙስና ኮሚሽን ቀጠሮ የያዝከው?” በማለት ይጠይቃሉ

“አዎ! እውነት ነው” በማለት አቶ ተስፋዬ መልስ ይሰጣሉ።

አቶ ኦሞት መልሰው “እንግዲያውስ ጸረ ሙስና ኮሚሽን ከመግባትህና ከማነጋገርህ በፊት ሁለታችን መገናኘት አለብን።
የምንነጋገረው ነገር አለ” የሚል ጥያቄ ያቀርባሉ። አቶ ተስፋዬ ስለ ስልክ ልውውጡ እንደነገሯቸው የተናገሩት እኚሁ ሰው፣ አቶ ኦሞት
በስልክ ደጋግመው በመደወል ያቀረቡትን የ”እንነጋገር” ጥያቄ አቶ ተስፋዬ አልቀበልም ይላሉ።

ጋምቤላ ስራቸውን ለቀው ራሳቸውን ደብቀው የኖሩት በእርሳቸው ምክንያት መሆኑን፣ ፍትህ እንደሚፈልጉ፣ አሁን ለመነጋገር ጊዜው
እንዳልሆነ፣ ዘርዝረው ለአቶ ኦሞት መናገራቸውን ያወሱት የጎልጉል ምንጭ፣ ጥያቄያቸው ውድቅ የተደረገባቸው አቶ ኦሞት በንዴት
ተዛልፈው ነበር።

ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው እንግዲህ አቶ ተስፋዬ ትንሳዔ ሆቴል ሰዎችን በመላላክና በመታዘዝ ከሚኖር አንድ የጋምቤላ ሰው /አቶ
ተስፋዬ የሚረዱት በምግባር ጉዳይ የሚታማና ጸበኛ የሚባል ሰው ነው/ አብረው ተቀምጠው ምሳ እየበሉ ሳለ አቶ ተስፋዬ አረፋ
ይደፍቃቸዋል።

ወዲያው ከተቀመጡበት ተንሸራተው መሬት ይወድቃሉ። ቀጥሎም ሰውነታቸው ይዝልና ኮማ ውስጥ ይገባሉ። ከአፋቸው
እየተዝለገለገ የሚወጣው ፈሳሽ በመጨመሩና የተለያየ ርዳታ ቢደረግላቸውም ሊተርፉ ስላልቻሉ ሆስፒታል ተወስደው ህይወታቸው
ማለፉ ተረጋግጧል።

አቶ ተስፋዬ ሆስፒታል ከመድረሳቸው በፊት እንደሞቱ የሚናገሩት የጎልጉል ምንጭ አሟሟታቸው ከመርዝ ጋር የተያያዘ እንደሆነ
ተናግረዋል። አቶ ተስፋዬ በሙስና ወንጀል ላይ ያሰባሱትን መረጃ ለተለያዩ አካላት የበተኑ ስለሆነ እሳቸውን በመግደል ማድበስበስ
እንደማይቻል አስታውቀዋል።

አቶ ተስፋዬ ሙስና ካጋለጡ በኋላ መሰወራቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው። በተያያዘ በጋምቤላ ኢንቨስትመንት ላይ ከተሰማሩ
ባለሃብቶች ውስጥ ከ70በመቶ በላይ የሆኑት የህወሓት የቀድሞ ታጋዮች የነበሩና የክልል አንድ ተወላጆች መሆናቸው የአቶ ተስፋዬን
አሟሟት ይበልጥ ውስብስብ እንዳደረገው አስተያየት እየተሰጠ ነው፡፡

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ “የአቶ ተስፋዬ ሞት አሳዛኝና አስደንጋጭ ነው። ብዙ ሳይታወቅ
የተገደሉ ተስፋዬዎች አሉ” በማለት ስለ አቶ ተስፋዬ ሞትና አሟሟት መረጃ እንደደረሳቸው አስታውቀዋል።

“አቶ ተስፋዬ ለእውነት ሲል ሞቷል። ኢህአዴግ ውስጥ በርካታ የወንጀል መረጃ ያላቸው ወገኖች አሉ። እንዲህ ያሉ ዜጎች
በየትኛውም ዘመን አይረሱም። የቀን ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ስማቸውና ታሪካቸው ከጨዋነታቸው ጋር ተመልሶ ህያው ይሆናል።

ሌቦችና ነፍሰገዳዮች ወደ ህግ ሲያመሩ፣ እንደ አቶ ተስፋዬ አይነቶቹ የመጪው ትውልድ ታላቅ ምሳሌ ሆነው እየተወደሱ ህያው
ሆነው ይኖራሉ” የሚል አስተያየት የሰጡት አቶ ኦባንግ፤ አቶ ተስፋዬ ያሰባሰቧቸው የሙስናና ተመሳሳይ ወንጀሎች ማሳያ ሰነዶች
እጃቸው ላይ ስላለ አቶ ተስፋዬን በመግደልና በማስገደል ወንጀል ማድበስበስ እንደማይቻል ተናግረዋል።

የአቶ ተስፋዬ የቀብር ስነስርዓት ጋምቤላ መፈጸሙን ለመረዳት ተችሏል። ቤተሰቦቻቸውን በማግኘት ሆስፒታሉ ስለ አሟሟታቸው
የሰጠውን አስተያየት ጠይቀን ለመረዳት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካልንም።