የ2013 ዓመት የኢትዮጵያ የአቦሸማኔው (ወጣቱ ትውልድ) መነሳሳት ሲገመገም፣

ከፕሮፌሰር  አለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

እ.ኤ.አ በጃንዋሪ 2013 “እ.ኤ.አ 2013 የኢትዮጵያ የአቦሸማኔው ትውልድ ዓመት ይሆናል“ በማለት ትንበያ ሰጥቸ ነበር፡፡ እንዲህ ስልም ቃል ገብቸ ነበር፣ “የኢትዮጵያ ወጣቶች ለፍትህና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የሚያደርጉትን ትግል ለመደገፍ እና ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ እንዲል የእራሴን ሙሉ አስተዋጽኦ እንደማደርግ እንዲሁም ትግሉ ወደ አዲስ ምዕራፍ እንዲሸጋገር ወጣቱ ትውልድ እንዲነሳሳ ሳደፋፍር ነበር፡፡” በዚህም መሰረት ጀግኖቹ ወጣቶች ትግላቸውን ቀጥለው ከፍ ወዳለ ደረጃ ላይ አድርሰውታል፡፡ ለወጣቶቹ እንዲህ በማለትም ተማጽኘ ነበር፣ “ብዙዎቹን ወጣቶች፣ ለመድረስ፣ ለማስተማር እና የበለጠ ግንዛቤ እንዲያገኙ ጥረት አድርጉ፡፡” ከዚህ አንጻር ቃሌን ሙሉ በሙሉ በማክበር ስኬታማ ስራ በመሰራቱ የተሰማኝን ኩራት ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

እ.ኤ.አ ዴሴምበር 2013 በአሜሪካ በአርሊንግተን ከተማ ከሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ከይልቃል ጌትነት ጋር በመገናኘቴ ታላቅ ደስታ እና ክብር የተሰማኝ ሲሆን ለወደፊትም ከኢትዮጵያ የአቦሸማኔው (ወጣቱ ትውልድ) ጋር ያለኝን የትግል አጋርነት በጽናት እንደምቀጥል ቃል ገብቻለሁ፡፡

እ.ኤ.አ በዴሴምበር 2013 የአቦ-ጉማሬው (የወጣቱ እና የቀድሞው ትውልድ) ትውልድ በሰላማዊ ትግሉ ሂደት በንቃት ከሚሳተፈው ከኢትዮጵያ አቦሸማኔ ትውልድ ጋር ያለውን የትግል አጋርነት ይፋ አድርጓል፡፡ እንዲህ ብዬ ተናግሬም ነበር፣ “የአቦ-ጉማሬው ትውልድ አባል መሆኔ በኩራት እንድሞላ አድርጎኛል፡፡” በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የአቦ-ጉማሬ ትውልድን “የመፍጠር” አስፈላጊነት ከምንም በላይ ተቀዳሚ ተግባር ሆኖ ተገኝቷል፡፡ የአቦ-ጉማሬው ትውልድ በአፈጣጠሩ የጉማሬው (የቀድሞው ትውልድ) አባል ሲሆን በተግባራዊ ድርጊቱ ግን እንደ አቦሸማኔው (ወጣቱ ትውልድ) የሚያስብ፣ አቦሸማኔውን የሚመስል እና እንደ አቦሸማኔው ሁሉ የክንውን ድርጊቶችን የሚፈጽም የማህበረሰብ ክፍል ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የአቦ-ጉማሬው ትውልድ የጉማሬውን (የቀድሞውን ትውልድ) ድክመቶች በሚገባ የተረዳ እና እነዚህን ግድፈቶች በማስወገድ የወጣቱን ትግል ወደ ላቀ የእድገት ምዕራፍ ለማሸጋገር በአንድ ዓላማ ለአንድ ዓላማ የሚሰራ የህብረተሰብ አካል ነው፡፡

የአቦ-ጉማሬው ትውልዶች ድልድይ ገንቢዎች ናቸው፡፡ ወጣቱን ከቀዳሚው ትውልድ የሚያገናኙ ጠንካራ የትውልድ ድልድዮችን የሚገነቡ ናቸውና፡፡ ህዝቦችን በዴሞክራሲ፣ በነጻነት እና በሰብአዊ መብት ጥበቃ የሚያስተሳስሩ ድልድዮችን ይገነባሉና፡፡ በትውልድ ቦታቸው እና አካባቢያቸው ተጠርንፈው የተያዙ ህዝቦችን የሚያገናኙ እና ጥልቅ የጎሳ ሸለቆዎችን ሰንጥቀው የሚያቋርጡ ድልድዮችን  የሚገነቡ ናቸውና፡፡ በቋንቋ፣ በኃይማኖት እና በክልል ተነጣጥለው የተቀመጡ ህዝቦችን የሚያገናኙ ድልድዮችን ይገነባሉና፡፡ ደኃውን ከሀብታም የሚያገናኙ ድልድዮችን የሚገነቡ ናቸውና፡፡ ብሄራዊ ዕርቅ ለማውረድ እና የብሄራዊ አንድነትን ለማምጣት ህዝቦችን የሚያገናኙ ድልድዮችን የሚገነቡ ናቸውና፡፡ በአገር ቤት ውስጥ ያሉትን ወጣቶች በውጭ አገር ከሚኖሩት የዲያስፖራ ወጣቶች ጋር የሚያገናኙ ድልድዮችን ይገነባሉና፡፡

በእ.ኤ.አ 2013፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች የእራሳቸውን የኃይማኖት ጉዳይ እራሳቸው በሚፈልጉበት መልክ ማስተዳደር እንዲችሉ እና በእምነታቸው ላይ የሚካሄደውን የመንግስት ጣልቃገብነት በመቃወም በሰላማዊ ሰልፍ ብሶታቸውን በመግለጻቸው ብቻ በገዥው አካል ብዙሀን መገናኛ ዘዴዎች ረበየለሽ እና ግዙፍ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ተካሂዶባቸዋል፣ በታጠቁ ኃይሎች በዘፈቀደ ከህግ አግባብ ውጭ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርገዋል፣ በየማጎሪያ እስር ቤቶችም እንዲጋዙ ተደርገዋል፡፡ ሀገር በቀል የእስልምና አክራሪዎች እና አሸባሪዎች “የኃይማኖት ጦርነት” በማወጅ በኢትዮጵያ ውስጥ የእስላም መንግስት ማቋቋም ይፈልጋሉ በሚል ሰበብ በህዝብ ዘንድ ለማጋለጥ በማሰብ ገዥው አካል “ጅሃዳዊ ሃራካት” (“የኃይማኖት ጦርነት እንቅስቃሴ“ የሚል ርዕስ በመስጠት ለአንድ ሰዓት የዘለቀ “ዘገባዊ ፊልም” አዘጋጅቶ በአየር ላይ አውሏል፡፡ ያ የሞራል ዝቅጠት የተንጸባረቀበት፣ ሆን ተብሎ ዜጎችን ለማጥቃት በማለም እና ለምንም የማይጠቅም እርባናየለሽ ዘገባዊ ፊልም ለህዝብ በማሳየት የኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች በናይጀሪያ በመንቀሳቀስ በህዝብ ላይ ጅምላ ፍጅት በማድረስ ላይ የሚገኘው ቦኮ ሃራም የተባለው ጽንፈኛ እስላማዊ አክራሪ ድርጅት ተከታዮች እና የአልቃይዳ ታዛዦች እና አሸባሪዎች ናቸው በማለት ወጣቶቹን ከህዝብ ነጥሎ ለማሳየት የታለመ ነበር፡፡ ያንን አስቀያሚ እና መቅንየለሽ ዘገባዊ ፊልም በጣም አድርጌ እኮንነዋለሁ፡፡ ምክንያቱም “ውሸቶች ታጭቀውበታል፣ ዓይን ያወጡ ደረቅ ውሸቶች፣ የተወገዙ ውሸቶች እና ሞራለቢስ ቅጥፈቶች፡፡ ‘ጅሃዳዊ ሃራካት’ የእነዚህ የአራት ቀጥፈቶች ጥቅል አንድ መጠሪያ ስም ነው::”

በእ.ኤ.አ የ2013 የእኔን ልዩ ጀግኖች አክብሪያለሁ፡፡ ለጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና ለጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ ልዩ ክብር እሰጣለሁ፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሁለቱ ጋዜጠኞች በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ኢትዮጵያ በአምባገነኑ ገዥ አካል እየታሰሩ፣ እየተሰቃዩ፣ ከህግ አግባብ ውጭ ብይን እየተሰጠባቸው፣ እና የማስፈራሪያ ውርጅብኝ እየተፈጸመባቸው ለሚገኙት ወጣት ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ቋሚ ተምሳሌት በመሆናቸው ነው፡፡ እነዚህ ጋዜጠኞች ለእኔ ልዩ ናቸው፣ ምክንያቱም በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ በአሁኑ ጊዜ ከአምባገነኖች ጋር እተካሄደ ያለውን ትግል እና የኢትዮጵያ ወጣቶች ለነጻነት የሚያደርጉትን ተጋድሎ የሚወክሉ የወጣቱ ቀንዲል በመሆናቸው ነው፡፡ እውነትን እና ትክክለኛውን መርህ ከመያዝ በስተቀር ሌላ ምንም ዓይነት የሚዋጉበት ነገር የላቸውም፡፡ ቅጥፈትን እና ውሸትን በእውነት ጎራዴ ድል ያደርጋሉ፡፡ ብዕርን ብቻ በመታጠቅ ተስፋ ማጣትን በተስፋ፣ ፍርሀትን በድፍረት፣ ቁጣን በምክንያታዊነት፣ እብሪትን በክብር፣ ድንቁርናን በዕውቀት፣ ታጋሽየለሽነትን በትዕግስት፣ ጭቆናን በትግል፣ ጥርጣሬን በመተማመን፣ እና ጭካኔን በሩህሩህነት ይዋጋሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ እነዚህ ጋዜጠኞች በስልጣን ላይ ላሉት እና ስልጣናቸውን ለታዕይታ ለሚያወሉ፣ ስልጣንን አላግባብ ለሚጠቀሙ፣ ስልጣናቸውን ከተሰጣቸው ስልጣን በላይ ለሚያውሉ እና ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ በሙስና ለሚዘፈቁ ባለስልጣናት ትኩረት በመስጠት ፊት ለፊት በመግጠም እውነት እውነቱን እስከ አፍንጫቸው ድረስ ይነግሯቸዋል፡፡

እ.ኤ.አ በ2013 በኢትዮጵያ ጥልቀት እና ስፋትን በመያዝ ተንሰራፍቶ የሚገኘውን አስደንጋጩን ሙስና ዓለም ተመልክቷል፡፡ ሙስናው በየትኛውም ኢከኖሚያዊ እና ማህበራዊ ዘርፍ ላይ ተንሰራፍቶ ይገኛል- በኮንስትራክሽን፣ በቴሌኮሙኒኬሽን፣ በመሬት፣ በጤና፣ በፍትህ፣ እና በትምህርት፡፡ በትምህርት ላይ የሚፈጸም ሙስና ምናልባትም በጣም የአውዳሚነት ባህሪ ይኖረዋል፣ ምክንያቱም በወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ላይ ጠንከር ያለ አሉታዊ ተጽዕኖ ስለሚያስከትል ነው፡፡ ኔልሰን ማንዴላ ትምህርትን አስመልክቶ እንዲህ ብለዋል፣ “ትምህርት ዓለምን ለመለወጥ የምትጠቀምበት ጠንካራ መሳሪያ ነው፡፡“ በኢትዮጵያ ላለው ገዥ አካል ግን ድንቁርና ለውጥን ለመከላከል እና በስልጣን ኮርቻ ላይ ተፈናጥጦ ለመኖር የሚያገለግል ጠንካራ መሳሪያ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ገዥው አካል የተሳሳተ መረጃ በመስጠት፣ የውሸት መረጃ በመጋት፣ የማሳሳቻ ለውጥ በማቅረብ፣ አቅጣጫቸውን የሳቱ ሀሳቦችን በማሰራጨት፣ ጊዜ ያለፈባቸውን መፈክሮች እና ካለፉት ዘመናት የመከኑ ቀኖናዎችን በመምዘዝ እና ለወጣቱ በማቅረብ የሀሰት የፕፓጋንዳ ዳቦ በማስገመጥ ላይ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያን ደንቆሮ ንጉሶች፣ ንግስቶች፣ ልዑላን እና ልዕልቶች የነገሱባት “የደንቆሮዎች ግዛት” እንድትሆን አድርገዋታል፡፡ የትምህርት ሙስና የወደፊቱን ወጣት ትውልድ እድል ይሰርቃል፡፡ እውቀትን ለማግኘት፣ ህይወታቸውን ለመለወጥ፣እና የአገራቸውን ዕጣፈንታ ለመወሰን የሚያገለግሏቸውን ዕድሎች በመዝጋት ለዘላለም የዕውቀት እና የምሁርነት ሽባ አድርጓቸው ይቀራል፡፡ ማልኮም ኤክስ በውል እንዳጤኑት፣ “ያለ ትምህርት በዚህች ዓለም ላይ የትም መሄድ አይቻልም” ብለዋል፡፡ በዚህ በወጥመድ በተያዘ እና ቁጥጥር ባለበት ዓለም እና ሙስና በተንሰራፋበት የትምህርት ስርዓት የኢትዮጵያ ወጣቶች የትም መሄድ ይችላሉን?

እ.ኤ.አ በዴሴምበር 2013 አጋማሽ የኢትዮጵያ ወጣቶች ቃልኪዳናቸውን አድሰዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ በኢትዮጵያ ያሉ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፣ የኃይማኖት ነጻነት እንዲከበር፣ ሰብአዊ መብቶች እንዲጠበቁ እና የህገ መንግስት እና ህዝባዊ ተጠያቂነት መኖርን በመጠየቅ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በአገሪቱ ማዕከል በሆነችው በአዲስ አበባ ከተማ የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡ በወጣቱ ስራ አጥነት፣ በዋጋ ግሽበት እና በተንሰራፋው ሙስና ላይ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ ገዥውን አካል ጠይቋል፡፡ እኔ በዚህ ሁኔታ በጣም ተመስጫለሁ፡፡ “በኢትዮጵያ ወጣቶች ረዥሙ የነጻነት እና የክብር ጉዞ ተጀምሯል፡፡ በጣም ቆንጆ ነገር ነው፡፡ በጣም ቆንጆ ነገር ነው፣ ምክንያቱም ሰላማዊ ነው፡፡ በጣም ቆንጆ ነገር ነው፣ ምክንያቱም የአንዲት አገር ኢትዮጵያ ውድ ልጆች እርስ በእርሳቸው በመዋደድ እና በአገር ፍቅር ስሜት ሆ ብለው በአንድነት ሆነው ድምጻቸውን ከፍ አድርገው እንዲህ እያሉ ሲጮሁ ነበር፣ “ከዚህ በኋላ ምንም ዓይነት ትዕግስት የለንም! ለውጥ እንፈልጋለን!”

በሰማያዊ የአቦሸማኔ (ወጣቱ ትውልድ) መነሳሳት ጊዜ የኢትዮጵያ ወጣት የህብረተሰብ ክፍል የለማ ምናባዊ አስተሳሰቡን በመጠቀም አዲስ ልዩ የሆነ ለውጥ በኢትዮጵያ ሀገሩ ለማምጣት እየተነሳ ነው በማለት የክርክር ጭብጤን ሳቀርብ ነበር፡፡ ወጣቶቹ አዲሲቷን የጀግኖች ሀገር የሆነች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ያልማሉ፡፡ በዘር ክፍፍል ላይ የተመሰረተችውን፣ በጎሳ አፍቅሮ የተዋቀረችውን፣ የኃይማኖት ጽንፈኝነት እና አፍቅሮ ዘረኝነትን አካታ የተመሰረተችውን አሮጊቷን ኢትዮጵያ አይፈልጉም፡፡ የጾታ እኩልነት እንዲሰፍን ይፈልጋሉ፡፡ በድፍረትም እንዲህ በማለት እጠይቃለሁ፣ “ወጣቶቹ የራሳቸው የሆነች ኢትዮጵያ ለምን አትኖራቸውም? የእኛ የእራሳችን የሆነች ኢትዮጵያ አለችን፣ ወጣቶቹ የራሳቸው ኢትዮጵያ እንድትኖራቸው ጊዜው አሁን አይደለምን?”

እ.ኤ.አ በሳመር 2013 ፕሬዚዳንት ኦባማ አፍሪካን በጎበኙበት ጊዜ የኢትዮጵያን ወጣት የህብረተሰብ ክፍል በስፋት ለመድረስ ስል በማዘጋጃቸው ትችቶቼ ላይ ተጨማሪ ፈጠራ ለመጨመር በማሰብ ሁለት “ፍላሽ ድራማ” (ትያተር) ጭውውቶችን አካትቼ ነበር፡፡ በዚያ ጽሁፌ ላይ የተጠቀሱት ሁለቱ ተዋሃኒዎች ኦባማ ለምን “ወደ አፍሪካ እንደመጡ” በእርግጠኝነት የሚያውቁት ነገር አልነበረም፡፡ የንግግራቸው ዳህራ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡


ዱማ፡ አሃ! ኦባማ ወደ ትውልድ አሁጉሩ ወደ አፍሪካ ተመልሶ መጣ፣ ጥሩ ነው ሹዲ
ሹዲ፡ የለም፣ ከአፍሪካውያን ጋር ለመነጋገር ነው የመጣው

ዱማ፡ ለመነጋገር?  ጣፋጭ ንግግር? ጠንካራ ንግግር? ትንሽ ንግግር? የሰላም ንግግር?
የጦርነት ንግግር? የሚተገበር ንግግር? ንግግር ብቻ?  የስሜት ንግግር? ትርጉመቢስ ንግግር?
ርካሽ ንግግር? ገንዘብ ይናገራል… ንግግር፣ ንግግር፣ ንግግር…?

ከኦባማ የአፍሪካ ጉብኝት በኋላ ሁለቱ ወጣት ተዋሃኒዎች የእራሳቸውን ዳኝነት ሰጡ፣

ሹዲ፡ ኦባማ መጡ እና ሄዱ…
ዱማ፡ ኦባማ መጡ እና አዩ፣ ግን ምን አሸነፉ? አገኙ?
ሹዲ፡ ኦባማ መጡ፡፡ አዩ፡፡ ተመልሰው ሄዱ፡፡

በእ.ኤ.አ 2013 ፕሬዚዳንት ኦባማ “አፍሪካን ማጠናከር” በሚል ለጀመሩት ተነሳሽነት የአፍሪካን ወጣቶች ለማጠናከር የእራሴን ጠቃሚ ምክሮች ልለግሳቸው ሞክሬ  ነበር፡፡ “አፍሪካን ከማጠናከራቸው” በፊት ወጣቱን እንዲያጠናክሩት፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ አፍሪካ የኃይል (ኤሌትርክ) ችግር እንዳለባት እንደሚያውቁ እና ለዚህ ችግር መወገድም አጋር እንደሚሆኑ የተናገሩትን ንግግር እኔም እስማማለሁ፡፡ አፍሪካ በኃይል ስልጣን ከሚባልጉ፣ በኃይል ስልጣናቸውን አላግባብ ከሚጠቀሙ፣ በኃይል ስልጣናቸውን እና ኃላፊነታቸውን ከሚያደበላልቁ እና በኃይል ስልጣናቸውን ትክክል በማስመሰል አላግባብ ከሚጠቀሙ ሌባ መሪዎች ፕሬዚዳንት ኦባማ በእርግጥም አፍሪካን ባለ ኃይሎች እያጠናከሩ ነው፡፡ ጥያቄው አፍሪካን ከማጠናከሩ ላይ አይደለም፣ ነገር ግን አሜሪካ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በእየዓመቱ በእርዳታ፣ በብድር እና በቴክኒክ እገዛ ሰበብ ኃያላን አምባገነን አፍሪካውያን ገዥዎች ኪስ እያጨቀች ኃይል የሌላቸውን የአፍረካ ህዝቦች እንዴት መጠበቅ እንደሚቻል ከማወቁ ላይ ነው፡፡ ኦባማ አፍሪካውያንን ማጠናከር ከፈለጉ ተራ አፍሪካውያን ህዝቦችን ስልጣናቸውን አላግባብ ከሚጠቀሙ እና በስልጣን ከሚባልጉ አምባገነን ገዥዎች መዳፍ በመጠበቅ የማጠናከር ስራውን መጀመር ይችላሉ፡፡ የፖለቲካ ስልጣኑን ይዘው የወጣቱ እምቅ ኃይል ጎልቶ እንዳይወጣ እንቅፋት የሚሆኑበትን እንዲሁም ብዝበዛ እና ስልጣንን አላግባብ መጠቀምን በማስቆም የወጣቱን ኃይል ማጠናከር አለባቸው፡፡ በየዓመቱ የሚለገሰውን በቢሊዮን የሚቆጠር የዶላር ዕርዳታ የአፍሪካ የሌባአምባገነኖችን ኃይል በመቀነስ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠረውን የአፍሪካ ወጣቶችን ኃይል ማጠናከር ይኖርባቸዋል፡፡

አ.ኤ.አ በማርች 1963 የተካሄደውን የአሜሪካ የሲቪል መብቶች እንቅስቃሴን የመሩትን ወጣቶች 50ኛ ዓመት በዓል በዋሽንግተን ዲሲ አክብሪያለሁ፡፡ በ26 ዓመታቸው የአሜሪካንን የሲቪል መብቶች እንቅስቃሴ የጀመሩትን እና ፍቅር የነገሰበት ማህበረሰብን ለመመስረት ማርቲን ሉተር ኪንግ “በህብረተሰቡ ህይወት የይዘት ለውጥ እንዲሁም በኑሮው የመጠን ለውጥ“ በሚያመጡት ነገሮች ልዩ ትኩረት ሰጥተው ሲታገሉ ነበር፡፡ የማርቲን ሉተር “ፍቅር የነገሰበት ማህበረሰብ” ከዘረኝነት፣ ከድህነት እና ከጦረኝነት ነጻ የሆነ ማህበረሰብ ነው፡፡ ፍቅር እና ፍትህ የነገሰበት ማህበረሰብ በእትማማቾች እና በወንድማማቾች ፍቅር እና መተሳሰብ መርሆዎች ላይ በመመስረት ለህይወት ትርጉም የሚሰጥ ነው፡፡ ማርቲን ሉተር ኪንግ እንዲህ ብለዋል፣ “የዘመናችን ዋና የፖለቲካ እና የሞራል ጥያቄዎች መልስ ሰላማዊ ትግል ነው፡ ጭቆናን እና ኃይልን በሰላማዊ መንገድ ለማስወገድ ጭቆንና እና ኃይልን አለመጠቀም የሰው ልጅ ፍላጎት መሆን አለበት፡፡ የሰው ልጅ በቀልን፣ ኃይልን እና አሉታዊ የአጻፋ ምላሽ የመስጠት መንገዶችን በማስወገድ በሰዎች መካከል ያሉትን ግጭቶች በሰላም መፍታት አለበት፡፡ እንግዲህ የዚህ ሁሉ መሰረቱ ፍቅር ነው፡፡”  ሲሉ ማርቲን ሉተር ኪንግ ተናግረዋል::

እ.ኤ.አ በ2013 “የኢትዮጵያ ወጣቶች ህዳሴ” እውን እንዲሆን ጥሪ አቅርቢያለሁ፡፡ እንዲህ በማለት የክርክር ጭብጤን አቀርባለሁ፡፡ በኢትዮጵያ እውነተኛ “ተሀድሶ”, “እንደገና የመወለድ” ወይም “እንደገና የመፈጠር” ዓይነት ዕድል እንዲመጣ ከተፈለገ ሊመጣ የሚችለው በወጣቱ ደም፣ ላብ እና እንባ ብቻ እንጅ በአምባገነኖች ወይም በእነርሱ አፈቀላጤዎች ከሚፈበረክ የውሸት ፕሮፓጋንዳ አይደለም፡፡ ሀገሪቱን ወደ ኢኮኖሚ ተሀድሶ ለመምራት የጦሩ ጫፍ ኢትዮጵያውያን/ት ወጣቶች ናቸው:: ኢኮኖሚዉን የሚንቀሳቀሱት ኢትዮጵያውያን/ት ወጣት ኢንተርፕሪነሮች መሆን እንዳለባቸው፡፡ ወጣት ኢትዮጵያውያን/ት ምሁራን የዕውቀት ኃይል ሽግግርን በግንባርቀደምትነት መምራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ወጣት የኢትዮጵያ ሳይንቲስቶች እና ኢንጅነሮች አገሪቱ እራሷን እንድትችል እና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነቷም እንዲጎለብት ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ወጣት የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ወጣቶች የፍትህን ጎራዴ መታጠቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ወጣት የኢትዮጵያ መሪዎች ጠንካራ የማህበራዊ እና የፖለቲካ ለውጥ አራማጆች በመሆን የ21ኛው ክፍለ ዘመን የተከበረች እና ኩሩ ኢትየጵያን መመስረት አለባቸው፡፡

እ.ኤ.አ በ2013 በሳውዲ አረቢያ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ወጣት ስደተኛ ሰራተኞች ለአስደንጋጭ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተዳርገዋል፡፡ የሳውዲ ፖሊሶች፣ የደህንነት ሰራተኞች እና ዘራፊዎች ኢትዮጵያውያን/ት ዜጎችን በመንገድ ላይ በማደን የመደብደብ፣ የማሰቃየት እና አንዳንድ ጊዜም የመግደል ወንጀሎችን ፈጽመውባቸዋል፡፡ የሳውዲ ፖሊሶች ኢትዮጵያውያን/ት ዜጎችን ሲያሰቃዩ የሚያሳዬውን የቪዲዮ ክሊፕ መመልከት ለህሊና የሚሰቀጥጥ ነገር ነው፡፡ የሳውዲ አረቢያ ፖሊሶች እና የደህንነት ኃይሎች ኢትዮጵያውያን/ት ዜጎችን በየመንገዶች ላይ ሲያሳድዱ፣ ሲያጠቁ እና ሲገድሉ የሚያሳየው የቪዲዮ ክሊፕ ትርምስ በሰው ልጆች ዘር ላይ የተፈጸመ የሰብአዊ መብት ወንጀል ዋና ማረጋገጫ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል “የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር” “የሳውዲ አረቢያ ባለስልጣኖች በህገወጥ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን/ት ዜጎች ላይ ያሳለፉትን ውሳኔ እና ህገወጥ ኢትዮጵያውያንን/ትን ወደ ሀገራቸው በመመለሱ ፖሊሲ ላይ ኢትዮጵያ ያላትን አክብሮት ትገልጻለች፡፡” በማለት በሳውዲ አረቢያ ያለው ገዥ አካል በስደተኛ ኢትዮጵያውያን/ት ላይ ለፈጸመው የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንዲህ ሲሉም አክለዋል፣ “አገሮች በጦርነት ላይ በሚሆኑበት ጊዜ ህገወጥ ናቸው የሚሏቸውን ዜጎች እንደዚህ ያለ ወደ አገራቸው የመመለስ ፈጣን እርምጃ ቢወስዱ ህዝብም ሊቀበለው እና ሊረዳው ይችላል፣ ሆኖም ግን በሰላማዊ ጊዜ እንደዚህ አይደረግም” በማለት የሳውዲ አረቢ ገዥ አካል በኢትዮጵያውያን/ት ስደተኛ ሰራተኞች ላይ የፈጸመውን ሁኔታ ገልጸዋል፡፡ በሌላ አገላለጽ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን/ት ሰራተኞች ለተፈጸሙባቸው የመብት እረገጣዎች እራሳቸውን ተጠያቂ ማድረግ አለባቸው ማለት ነው፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለጥንቱን አባባል “የሚያጎርስህን እጅ በፍጹም አትንከስ” አዲስ ትርጉም ሰጥተውታል፡፡

የእኔን አፍሪካዊ ጀግና ታላቁን ኔልሰን ማንዴላን ደህና ይሁኑ ብዬ የምሰናበትበት ጊዜ ነበር፡፡ ኔልሰን ማንዴላን በፍጹም ላገኛቸው አልቻልኩም፣ ባገኛቸው እንዴት ደስ ባለኝ! ለማግኘት የምፈልገው ደግሞ በዓለም ላይ እጅግ ከተከበሩት ሰው ጋር ተገናኝቸ ነበር በማለት ለስሜቴ ክብር ለመስጠት አይደለም፣ ነገር ግን ለአፍሪካውያን ክብርን፣ ኩራትን እና ሞገስን ላጎናጸፉት እኒያን ጀግና ኔልሰን ማንዴላን በዚህ አጋጣሚ አመሰግናለሁ የምትለዋን ቃል በትህትና ለማቅረብ እንጅ፡፡

ኔልሰን ማንዴላ ድልድይ ቀያሽ ነበሩ፡፡ ዘርን፣ ጎሳን እና የህብረተሰብ መደብን የሚያገናኙ ድልድዮችን ገንብተዋል፡፡ ኔልሰን ማንዴላ እሳት አጥፊ ነበሩ፡፡ በዘር እና በጎሳ ጥላቻ ተቀጣጥሎ የነበረውን ቤት እሳት በማጥፋት በደቡብ አፍሪካውያን ዘንድ እውነት እና ዕርቅ እንዲሰፍን አድርገዋል፡፡ ኔልሰን ማንዴላ መንገድ ቀያሽ ነበሩ፡፡ በረዥሙ ጉዞ ወደ ነጻነት የሚያደርሱ በስም “ደግነት” እና  “ዕርቅ” የሚባሉ ሁለት መንገዶችን በመገንባት የተናገሩትን በተግባር አሳይተዋል፡፡ ኔልሰን ማንዴላ የህንጻ ንድፍ ነዳፊ/architect ነበሩ፡፡ በአፓርታይድ አመድ ላይ በብዙሃን ዘር ዴሞክራሲ የተዋበውን ማማ ገንብተዋል፡፡ ኔልሰን ማንዴላ የልዩ ተሰጥኦ ባለቤት ነበሩ፡፡ ከባርኔጣ ላይ ጥቁር እና ነጭ እርግቦችን በአንድ ጊዜ በመልቀቅ በነጻነታቸው ተንፈላስሰው እንዲበሩ አድርገዋል፡፡ ኔልሰን ማንዴላ ለዘላለም የሚኖር የለውጥ ሐዋርያ ነበሩ፡፡ ጥላቻን በፍቅር፣ ፍርሃትን በወኔ፣ ጥርጣሬን በእምነት፣ ታጋሽየለሽነትን በትዕግስት፣ ቁጣን በመግባባት፣ ጥላቻን በስምምነት፣ እና ቅሌትን በክብር የሚለውጡ ነበሩ፡፡

የማንዴላን መልዕክት ለኢትዮጵያውያን/ት ወጣቶች አስተላልፌአለሁ፡፡ “ፍቅር የነገሰበትን የኢትዮጵያን ማህበረሰብ ለመመስረት ደግ ነገርን አድርጉ፣ ይቅርታን እና እርቅን አውርዱ፡፡ የስኬት ቃልኪዳን ባይኖርም ሞክሩ፣ ውድቀት እንዳለ ብታውቁም ሞክሩ፣ ጥርጣሬ ያለ እና እርግጠኝነት የጎደለ መሆኑን ብታውቁም ሞክሩ፡፡ ደክማችሁ እና መቀጠል የማትችሉ መሆኑን ብታውቅም እንኳ ሞክሩ፡፡ ተስፋ በማይኖርበት ጊዜም ሞክሩ፡፡ ዓላማችሁን ካሳካችሁህ በኋላም ቢሆን ሞክሩ፡፡ ማንዴላ እንደሞከሩት ሁሉ ሞክሩ፡፡”

እ.ኤ.አ በ2013 የሰማያዊ ፓርቲ አስረጅ ምስክርነት ሆኘ ቀርቢያለሁ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ሰማያዊ ፓርቲን የምደግፍበት ምክንያት ከወጣቶች፣ በወጣቶች፣ ለወጣቶች፣ የተቋቋመ የፖለቲካ ፓርቲ ስለሆነ ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ የአብዛኛውን የኢትዮጵያን ህብረተሰብ ፍላጎት እና ጥቅም ሊወክል የሚችል ፓርቲ ስለሆነ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከኢትዮጵያ ህዝብ ከ35 ዓመት የዕድሜ ክልል በታች ያለው የህብረተሰብ ክፍል 70 በመቶውን ይሸፍናል፡፡

በአሁኑ ጊዜም የኢትዮጵያ ወጣቶች ለዴሞክራሲ፣ ለህግ ልዕልና፣ ለነጻነት እና ለሰብአዊ መብት ጥበቃ ሲባል የደም፣ የላብ እና የእንባ መስዕዋትነት በመክፈል ላይ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ ምርጡ እና ብሩህ አዕምሮ ያለው ወጣት እየተቀጣ፣ ፍርደገምድል ፍርድ እየተበየነበት፣ እየታሰረ፣ እና ጸጥ እረጭ ብሎ እንዲገዛ እየተደረገ ነው፡፡ ከእነዚህ የወጣት ዝርዝር የመጀመሪያው እረድፍ ላይ የሚገኙት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ እስክንድር ነጋ፣ አንዷለም አራጌ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ በቀለ ገርባ፣ አቡበካር አህመድ፣ ውብሸት ታዬ፣ ኦልባና ሌሊሳ፣ አህመዲን ጀቤል፣ አህመድ ሙስጣፋ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ በቅርቡ ከህይወት የተለየው የኔሰው ገብሬ እና ሌሎች ለቁጥር የሚያታክቱ ትንታግ የኢትዮጵያ ወጣቶች ናቸው፡፡ “የሰማያዊ ፓርቲ ንቅናቄን” የኢትዮጵያ ወጣቶች ለእራሳቸው እና ለወደፊቱ ትውልድ የሚተላለፍ ህልማቸውን እና ሀሳቦቻቸውን የሚተገብር ድርጅታዊ ተቋም አድርጌ እወስወደዋለሁ፡፡ ዝምታውን ከዚህ በኋላ እናቁም እና “ከሰማያዊ ፓርቲ ንቅናቄ” ጎን በመሰለፍ ድጋፋችንን እንድንሰጥ ለሁሉም ህዝቦች ተማጽዕኖዬን አቀርባለሁ፡፡

የኢትዮጵያ ወጣቶች፡ ከተኛችሁበት እንቅልፍ በመንቃት እንደ አንበሳ በመነሳት እና እንደ አቦሸማኔ በመወርወርውዲቱን ኢትዮጵያገንቡ፣

በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2013 የአቦሸማኔዎች ትውልድ ዓመት ዋና የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ ያለፈው ከድንቁርና፣ ከጎሳ ጥላቻ፣ ከዘር አድልኦ እና ከጾታ ኢፍትሀዊነት የጸዳች “ውዲቷን ኢትዮጵያ” ተገንብታ የማየትን ህልም ወጣቶቹ በፍጹም በፍጹም እንዳያቆሙ የሚለው ነው፡፡ ዓመቱ የኢትዮጵያ አቦሸማኔዎች የስኬት ዓመት ነው ማለት እችላለሁ፣ ሆኖም ግን ስራዎቻቸው ገና ሙሉ በሙሉ አልተከናወኑም፡፡ ከፊታቸው ገና ረዥም እና አስቸጋሪ ጉዞ ይጠብቃቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ከመጨረሻው ግባቸው ከመድረሳቸው በፊት በጣም አደገኛ የሆኑ ሸለቆዎችን የማቋረጥ፣ ድንጋያማ እና ቀጥ ያሉ ተራራዎችን የመውጣት፣ እና  ጎርፍ የሞላው ወንዞችን የመሻገር ተግባራትን ማለፍ ይጠብቃቸዋል፡፡ ጉዟቸውን በድፍረት እንዲቀጥሉ እማጸናለሁ፡፡ እ.ኤ.አ በ1819 የእንግሊዝ ሙሰኛ፣ ጨካኝ እና ቀጣይነት ያለው የአምባገነን አገዛዝ ጥቃትን በመቋቋም በሰላማዊ ትግሉ ሲፋለሙ ለነበሩ ወጣቶች ድጋፍ ይሆን ዘንድ ፔርሲ ባይሸ ሸሌይ የቋጠሯቸውን ስንኞች እንድያጣጥሙ እጋብዛቸዋለሁ፣

ታላቅ ስብሰባ ይደረግ፣
በታልቅ ግነዛቤ፣
በነጠሩ ቃላቶችም አውጁ፣
አምላክ ነጻ አድርጎ ፈጥሯችዋልና፣

አምባገነኖቹም ከደፈሩ፣
ከማሀላችሁ ታጥቀው በፈረሳቸው ይጋልቡ
ይውጉ ይቁረጡ ይጨፍጭፉ
እንደልባቸው ያርጉ፡፡

በታጠፉ እጆች እና አተኩረው በሚያዩ ዓይኖች፣
አለቅንጣት ፍርሃት አለመገረም፣
ሲገድሉ ሲያርዱ ልብ በሏቸው፣
ቁጣቸው እስኪበርድላቸው፡፡

ከዚያም ከእንቅልፋቸው እንደነቁ አንበሶች ተነሱ፣
በቁጥር የለሽ ብዛታቸሁ፣
በንቅልፍ የጣሉባችሁን የእስር ሰንሰለቶች እንደጤዛ አራግፏቸው፣
እናንተ ሺ ናቸሁ፣ እነርሱ ግን ጥቂት፡፡

የኢትዮጵያ ወጣቶች፡ እንደ አንበሶች ተነሱ! እንደ አቦሸማኔዎች ተሰንዘሩ!

ታህሳስ 22 ቀን 2006 .