የኢትዮጵያ ተተኪ ሴቶች ትውልድ መነሳሳት!

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

“ከዚህ በኋላ ትዕግስታችን ተሟጧል!”

ሰማያዊ ፓርቲ በኢትዮጵያ እንደገና ወኔ የተሞላበት የትግል መንፈሱን በማደስ ጥንካሬውን አሳየ !

Semayawi Women  Demonstrationእ.ኤ.አ ማርች 9/2014 የተከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች በዓል ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ ተዘጋጀቶ በነበረው የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ የሰማያዊ ፓርቲ ወጣት ሴቶችም ተሳትፎ አድርገው ነበር፡፡ ከዴሞክራሲያዊ ምርጫ ባፈነገጠ መልኩ በኃይል በስልጣን ኮርቻ ላይ ተፈናጥጠው ስልጣንን የሙጥኝ በማለት ከህግ አግባብ ውጭ በህዝብ ላይ ደባ በመፈጸም ላይ የሚገኙትን የሰብአዊ መብት ደፍጣጮች ዕኩይ ምግባር የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲገነዘበው በማሰብ ወጣት ሴቶቹ እውነታውን ያለምንም መሸፋፈን በማጋለጥ እምቢ አሻፈረኝ በማለት ተቃውሟቸውን ለዓለም በይፋ አሰምተዋል፡፡ እንዲህ በማለትም ተቃውሟቸውን አጠናክረዋል፣

“ከዚህ በኋላ ትዕግስታችን ተሟጧል! ተርበናል! ነጻነት እንፈልጋለን! ነጻነት እንፈልጋለነ! እስክንድር ይፈታ! አንዷለም ይፈታ! አቡባከር ይፈታ! ርዕዮት ትፈታ! የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ ይፈቱ! ፍትህ እንፈልጋለን! ነጻነት! ነጻነት! ነጻነት! አትከፋፍሉን! ኢትዮጵያ አንድ ነች! አንድ ኢትዮጵያ! ከዚህ በኋላ ትዕግስታችን ተሟጧል! ውኃ ናፈቀን! መብራት ናፈቀን! ተርበናል!…“

ለሰማያዊ ፓርቲ ሴት ወጣት አመራሮች ባርኔጣዬን ዝቅ በማድረግ ከወገቤ ጎንበስ በማለት ያለኝን አድናቆት ልገልጽላቸው እፈልጋለሁ፡፡ በእነርሱ እጅጉን ኮርቻለሁ፡፡ ባለፉት ጥቂት ወራት ሰማያዊ ፓርቲን ለምን እንደደገፍኩ እና በጽናትም ከፓርቲው ጎን ለምን እንደምቆምኩ በርካታ ሰዎች ጥያቄዎችን አቅርበውልኝ ነበር፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ቁጥር አንድ አድናቂ (አንደኛ ቲፎዞ) ለምን እንደሆንኩ ማንም ቢሆን ጥያቄዎች ካሉት/ካሏት ይህንን ቪዲዮ (እዚህ ይጫኑ)  እንዲመለከቱት እጋብዛለሁ፣ እናም መልሱን ከእዚያው ያገኙታል፡፡

አረመኔው ገዥ አካል በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያን ወጣት ሴቶች እና ወንዶች በዱላ እየደበደበ እና እንደ እባብ እየቀጠቀጠ ሁሉንም የጭቆና ዓይነቶች በእነርሱ ላይ እየተገበረ ባለበት ሁኔታ ከዳር ቆሜ ለመመልከት ህሊናዬ ሊፈቅድልኝ አይችልም፡፡ የመናገር መብታቸውን ተጠቅመው ሀሳባቸውን ለመግለጽ በመሞካራቸው ምክንያት ብቻ የኢትዮጵያ ወጣቶች ሲታሰሩ፣ ሲደበደቡ፣ ሲሰቃዩ እና ግፍ ሲፈጸምባቸው በዝምታ አልመለከትም፡፡ በወጣቶቹ ላይ የሚፈጸመውን ግፍ እና ስቅይት የእነርሱ ድምጽ በመሆን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እናገራለሁ፡፡

ወጣት ሴቶቹ ተቃውሟቸውን የገለጹት በሰላማዊ መንገድ ነው፡፡ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን በማሰማታቸውም በጨካኙ የገዥ አካል ማሰቃየት ተፈጽሞባቸዋል፡፡ በሰላማዊ እና ከአመጽ በጸዳ መልኩ በአገሪቱ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት ሲሉ ነው በአሁኑ ጊዜ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት በመሰቃየት ላይ የሚገኙት፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ሴት ወጣት አመራሮች እና አባላት እንደማንኛውም ሰው ሁሉ የ5 ኪ/ሜ ሩጫውን ተቀላቀሉ፡፡ በሰላማዊ መንገድ እሮጡ እና ከማጠናቀቂያ ቦታው ደረሱ፡፡ ምንም ዓይነት ህግ አልጣሱም፡፡ አንድም ጠጠር አልወረወሩም፡፡ በማንም ላይ ጥቃት አልፈጸሙም፡፡ ምንም ዓይነት ሁከትን በሚያመጡ ተግባራት ላይ አልተሳተፉም፡፡ ከአንድ ሺህ በላይ ሯጮች በተሳተፉበት በዚያ ሩጫ ላይ የሰማያዊ ፓርቲ ሴት ወጣት አመራሮች እና አባላት በመሳተፋቸው (ወይም በሌላ ምክንያት) በአንድም ሰው ላይ ጉዳት አልደረሰም፡፡ ቅንጣት ያህል ንብረት ላይ ጉዳት አልተፈጸመም፡፡ አንድም ባለስልጣን ማስፈራሪያ አልደረሰበትም ወይም ደግሞ የጥቃት ሰለባ አልሆነም፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ሴቶች ምንም ዓይነት የዘለፋ ቃላት እንኳ አልተጠቀሙም፡፡ ሁሉምን ነገር በሰላማዊ መንገድ፣ ሞገስን በተላበሰበ መልኩ እና በሚያስደምም ሁኔታ ነው ያከናወኑት፡፡ እነዚያ ጀግና ወጣት ሴቶች የምርጥ ተደናቂነት ተምሳሌት ቀንዲል ናቸው! በእነዚህ ወጣቶች እጅግ ኮርቻለሁ እናም ባርኔጣዬን ዝቅ በማድረግ አድናቆቴን ልገልጽላቸው እፈልጋለሁ፡፡

በዕለቱ የተከበረውን በዓል ኃላፊነት በመውሰድ ያዘጋጀው የገዥው አካል የሴቶች፣ የህጻናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር ነበር፡፡ የገዥው አካል የዕለቱ መፈክር “የምርጥ ሴቶች የመጀመሪያው ዙር የ5 ኪ/ሜ ሩጫ“ የሚል ነበር (ምን ለማለት እንደተፈለገ ግልጽ ባይሆንም)፡፡ ገዥው አካል ዕለቱ ከ10,000 በላይ ሴቶችን እና ልጃገረዶችን ያሳትፋል በማለት ዲስኩር አድርጎ ነበር፡፡ ገዥው አካል በበዓሉ ዕለት ሴቶች እንዲሳተፉ በስፋት የጥሪ ማሳሰቢያ ሲያደርግ ጠንካራዎቹ የሰማያዊ ፓርቲ ሴት ወጣት አመራሮች ማሳሰቢያውን ሊሰሙት እንደሚችሉ እረስቶት ኖሯል፡፡ መንፈሰ ጠንካራዎቹ ወጣት ሴቶች ግን ማድረግ ያለባቸውን ነገር በሚያስደምም ሁኔታ አደረጉት፡፡ ወጣት ሴቶቹ ለገዥው አካል ፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ሳይሆን ብጫ ካናቴራ በመልበስ ተልዕኳቸውን ሲፈጽሙ ታይተዋል፡፡ እዚያ የተገኙት ለመሮጥ ነበር፣ ለነጻነታቸው ለመሮጥ፣ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ለመሮጥ፣ የኢትዮጵያ እስረኞች እንዲፈቱ ለመሮጥ፣ በመሰቃየት ላይ ላለው እና ተስፋ ለራቀው ህዝብ ትኩረት በመሳብ  ለመሮጥ፡፡ ወጣቶቹ የሰማያዊ ፓርቲ ሴቶች አረመኒያዊ እና ጨካኝ እየተባለ በሚታወቀው ገዥው አካል ፊት ደፋርነታቸውን ማሳየት መቻላቸው ብቻ አይደለም አስደናቂ የሚሆነው ሆኖም ግን የእራሳቸውን የብልህነት ፈጠራ በመጠቀም የስርዓቱን ዕኩይ ምግባር በማጋለጣቸው ጭምር እንጅ፡፡

የአምስት ኪሎ ሜትሩ ሩጫ ከተጠናቀቀ በኋላ ሰባት የሰማያዊ ፓርቲ ወጣት ሴቶች በቁጥጥር ስር ውለዋል፣ ተደብድበዋል እንዲሁም ለእስር ተዳርገዋል፡፡ የሰብአዊ መብት እረገጣው ሰለባ ከሆኑት ውስጥ፡ ሜሮን ዓለማየሁ፣ ምኞቴ መኮንን፣ መታሰቢያ ተክሌ፣ ወይኒ ንጉሴ፣ ንግስት ወንድይፍራው፣ ወይንሸት ሞላ፣ እና እመቤት ግርማ ይገኙበታል፡፡ በሰማያዊ ፓርቲ በከፍተኛ የስልጣን እርከን ላይ የሚገኙ  ጌታነህ ባልቻ (የድርጅተ ጉዳይ ኃላፊ)፣ ብርሀኑ ተክለያሬድ (የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ) እና አቤል ኤፍሬም (የህዝብ ግንኙነት ኮሚቴ አባል) የተባሉ ሌሎች ሶስት ወጣት ወንዶች ደግሞ እስረኛ ሴቶች ያሉበትን ሁኔታ ለመጠየቅ  በሄዱ ጊዜ በቁጥጥር ስር ውለው እነርሱም ለእስር ተዳርገዋል፡፡

የጣይቱ እና የምኒልክ ልጆች በይስሙላው/በዝንጀሮዎች (ካንጋሩ ኮርት) ፍርድ ቤት፣

በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል የይስሙላ ፍርድ ቤት ስርዓት በአገሪቷ ዘርግቶ በመተግበር ላይ ይገኛል በማለት ሁልጊዜ ስናገረው የቆየሁት ጉዳይ ነው፡፡ በሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ላይ የተመሰረቱት “ክሶች” የገዥው አካል የይስሙላ ፍርድ ቤቶች እንዴት ባለ ሁኔታ እየተካሄዱ እንዳሉ ከምንም ጥርጣሬ በላይ በግልጽ ያመላክታሉ፡፡ በሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ላይ የተመሰረቱት ክሶች በባዶው የትወና መድረክ ላይ ብቻ የሚከናወኑ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የይስሙላው ፍርድ ቤት  እ.ኤ.አ ማርች 14/2014 ያደረገው የሁለተኛው ቀን “የችሎት” ትወና በሳሙኤል በኬት፣ ኢጀን ኔስኮ፣ ጂን ገነት ወይም ካፍካ ላይ የተደረገ ያለቀለት የትያትር ትወና ይመስል ነበር፡፡ የህጋዊነት ትወናው በምግባር የለሾች፣ በስም የለሾች፣ የማስተዋል ብቃት በሌላቸው፣ በህሊና የለሾች፣ በሀሳብ የለሽ ደነዞች፣ታማኝነት በሌላቸው ፖለቲከኞች እና ዋናው ተግባራቸው ህዝቡን ማሰቃየትን እና መከራ ማሳየትን እንደመርሀ የሚከተሉ አስመሳዮች በግልጽ በማይታይ መልኩ የሚጦዝ የውሸት የህጋዊነት ሽፋንን ተላብሶ እየተተገበረ ያለ ኃላፊት የጎደለው እና የተዋረደ የመድረክ ተውኔት ነው፡፡ ፍትህ ፊት የሌላት እና ቅርጿ የተበላሸ የይስሙላ ስርዓት ዘርግታ ትገኛለች፡፡ ፍትህ በሚያስገርም ሁኔታ በመደምሰሷ ምክንያት አካል የላትም፡፡ በኢትዮጵያ የፍትህ ፊት እና አካል በይስሙላው ፍርድ ቤት በርቀት በቁጥጥር ስልት መጠቀሚያ መሳሪያ ተይዞ የሚመራ እና በጌቶቹ ትዕዛዝ እንዲያደርግ የተሰጠውን ብቻ ያለምንም ኃፍረት ተቀብሎ እንደበቀቀን የሚደግም የሮቦት ዳኛ (አንደየተሞላ አሻንጉሊት) የተሰማራበት ሆኗል፡፡ የፍትህ አካሉ በዘራፊዎች ቁጥጥር  ስር ዉሎአል፡፡

በ “ችሎቱ” ክፍል እንደ አንድ ተመልካች ዘገባ ከሆነ “የማታ” በሚል ስም የሚታወቅ “የፖሊስ መርማሪ” የሰማያዊ ፓርቲ ሴቶች የጣይቱ ልጆች ነን (የ19ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ንግስት የነበሩት) እና የእምዬ ምኒልክ ልጆች ነን (በ19ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ንጉስ እና የንግስት ጣይቱ ባለቤት የነበሩት) በማለት በአደባባይ በመጮህ በሽብር ተግባር ላይ ተዘፍቀው ታይተዋል በማለት የምስክርነት ቃሉን ሰጥቷል፡፡ “መርማሪው” በተጨማሪም ተከሳሾቹ እየተራቡ ያሉ መሆናቸውን እና የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ እንዲሁም በእስር ላይ የሚገኙት ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች ማለትም ርዕዮት፣ እስክንድር፣ አንዷለም እንዲሁም ሌሎች እንዲፈቱ” እያሉ በአደባባይ ጩኸት እያሰሙ ነበር ብሏል፡፡ እንግዲህ ይኸ ነው በሰማያዊ ፓርቲ ሴቶች ተፈጸመ የተባለው “የሽብር ተግባር” ይዘት፡፡

የችሎት ስነስርዓቱ ከታቀደለት በአንድ ሰዓት ዘግይቶ ነው የተጀመረው፣ ምክንያቱም የሰማያዊ ፓርቲ ሴቶች በሰልፉ ላይ ለብሰዋቸው የነበሩትን ካናቴራዎች ወደ ችሎቱ ሲቀርቡ እንዲቀይሯቸው ቢጠየቁም ለመቀየር ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነበር፡፡ ፖሊሱ እስረኞቹን ከነካናቴራቸው ወደ ፍርድ ቤቱ እንዲቀርቡ መፍቀድ የፖለቲካ እምቢተኝነትን አምኖ እንደመቀበል ያስቆጥራል የሚል እምነት አደረበት፡፡ እንደ ዘገባው ከሆነ ሴቶቹ ወደ “ፍርድ ቤቱ” ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት የለበሷቸውን ካናቴራዎቻቸውን በማስገደድ እንዲቀይሩ ለማድረግ ፖሊ ሁከት ፈጥሮ እንደነበሩ ታውቋል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ወጣት ሴቶች እስከሚወሰዱ ድረስ በተያዙበት ቦታ እንዲቆዩ ተደርገዋል፡፡ “የፍርድ ቤቱ” ክፍል በተመልካች ተጨናንቋል፣ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችም በሙሉ ተገኝተው ነበር፡፡

የፌዴራል አቃቤ ህግ ጉዳዩን ለመመርመር እና መረጃ ለማሰባሰብ ተጨማሪ የ14 ቀናት ጊዜ እንዲሰጠው ሴት እስረኞችም በእስር እንዲቆዩ ጠየቀ፡፡ (በቁጥጥር ስር የማዋል ልምድ እና ተጠርጣሪን በእስር ቤት አውሎ ለጥፋተኝነት መረጃዎችን ለመፈለግ መሞከር የገዥው አካል የይስሙላው ፍርድ ቤት አሰራር ዋናው መለያ ባህሪው ነው፡፡ አንድ ተጠርጣሪ ፍርድ ቤት ከመቅረቡ በፊት የሚደረገው አሳፋሪ ዘዴ በእያንዳንዱ ከፍተኛ የወንጀል ጉዳይ ከሁለት ደርዘን ወይም ከዚያ በላይ በሚሆኑ በቀድሞዎቹ ባለስልጣኖች እና ባለፈው ዓመት ደግሞ በንግዱ ማህበረሰብ አባላት ላይ ሙስና በሚል ሰበብ የተደረገው እስራት ሲታይ ገዥው አካል ካለፉት አስርት ዓመታት በላይ ሲፈጽመው የቆየ ተግባር መሆኑን ነው፡፡ አቃቤ ህጉ እስከ አሁንም ድረስ ለሙስናው መረጃ ፍለጋ በሚል ሰበብ ጊዜ እየነጎደ በሄደ ቁጥር እነርሱ በእስር ቤት ተረስተዋል፣ ገዥው አካል ጉዳዩን ለሁለት ዓመታት ያህል ምርመራ እየተካሄደበት ነው በማለት በይፋ የገለጸ ቢሆንም)፡፡

የይስሙላ አቃቤ ህጉ ለሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች የዋስትና መብት መሰጠት እንደሌለበት ተከራክሯል፣ ምክንያቱም “ዋስትናው ከተሰጠ አሁን በፖሊስ ቁጥጥር ስር ያሉት ታሳሪዎች መረጃዎችን ያጠፋሉ፣ እናም ምስክሮች የምስክርነት ቃላቸውን እንዳይሰጡ በማንገራገር እና በማስፈራራት እንዳይመሰክሩ ሊያደርጉ ይችላሉ” ብለዋል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ መከላከያ ጠበቃ አቶ ዓለሙ ጎቤቦ (በእስር ቤት የምትገኘው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅናን ያተረፈችው ርዕዮት ዓለሙ አባት) ጉዳዩ የፖለቲካ ባህሪ ያለው ስለሆነ ልጆቹ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ ከውጭ ሆነው እንዲከራከሩ እንዲደረግ በማለት የክርክር ጭብጣቸውን አቅርበዋል፡፡ ቀጥለውም እንደ ህጉ ከሆነ ደንበኞቼ የዋስትና መብት እንዲያገኙ ይፈቅዳል፣ እናም ይህንን ላለማድረግ እየተከናወነ ያለው የዳኞቹ ተቃውሞ ተጠርጣሪዎቹን በእስር ቤት ለማማቀቅ የተደረገ ደባ ነው ብለዋል፡፡ “ዳኛው” የዋስትና ጥያቄውን አልተቀበሉትም፣ እናም የዳኝነት ሂደቱን ቀጠሉ፡፡ (ባለፉት በርካታ ከፍተኛ የሆኑ የፍርድ ቤት ጉዳዮች የፍርድ ሂደት ላይ እ.ኤ.አ የ2006 የቅንጅት ፓርቲ አመራሮችን “የፍርድ ሂደት” ጉዳይ ጨምሮ ገዥው አካል ምስክሮችን በማስፈራራት፣ ጉቦ በመስጠት፣ በሙስና አማልሎ ተጽዕኖ በማሳደር እና ከህግ አግባብ ውጭ በሆነ መልኩ ቃለመሃላን በመጣስ የውሸት የምስክርነት ቃል እንዲሰጡ በማድረግ ዕኩይ ምግባር ላይ ተዘፍቆ ይገኛል)፡፡

እንደ ፍርድ ቤት ተመልካች ታዛቢዎች ከሆነ የሰማያዊ ፓርቲ ሴቶች በእስር ቤቱ ውስጥ በቁጥጥር ስር ሆነው እያለ ከህግ አግባብ ውጭ በፖሊስ እና በደህንነት ኃላፊዎች አካላዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው እንዲሁም የማስፈራራት ሰለባ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ለይስሙላው ፍርድ ቤት ተናግረዋል፡፡ በሌሎች የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ላይ ቅጥረኛ እና ሰላይ እንዲሆኑ ብዙ ገንዘብ ቀርቦላቸዋል፡፡ ከተከሳሾቹ መካከል ትዕግስት ወንድይፍራው የተባለችው ባለፈው እኩለ ሌሊት ላይ ሶስት ወንድ ፖሊሶች እርሷ ወደታሰረችበት ክፍል መጥተው እንድትወጣ ትዕዛዝ እንደሰጧት “ለፍርድ ቤቱ” ተናግራለች፡፡ ከኃላፊዎች መካከል አንደኛው ዱላ በማንሳት በማወዛወዝ ካልተባበረች በስተቀር እስክትሞት ድረስ እንደሚደበድቧት ማስፈራራታቸውን ገልጻለች፡፡ ሌሎችም ሴቶች ተመሳሳይ የማስፈራሪያ ዛቻ እንደተፈጸመባቸው ተናግረዋል፡፡ ፖሊስ ሴቶቹ በሰማያዊ ፓርቲ ላይ የሚያደርጉትን ንቁ የአባልነት ተሳትፎ እና ጓዳዊ የትግል መንፈስ እንዲተው እና ከድጊታቸው እንዲታቀቡ በመደብደብ እንዳዋረዳቸው እና እንዳስፈራራቸው ያላቸውን ምሬት ገልጸዋል፡፡ በተመልካቾች ዕይታ “ብቃት የለሽ” ተብሎ የተፈረጀው የዕለቱ የችሎት ዳኛ ፖሊስ ምርመራውን አጠናቅቆ እ.ኤ.አ ለመጋቢት 18/2014 እንዲቀርብ ትዕዛዝ በመስጠት አሰናብቷል፡፡

በይስሙላው ፍርድ ቤት ያለውን ኃይል መገዳደር፣

የሰማያዊ ፓርቲ ሴቶችን በቁጥጥር ስር የማዋል እና የፍርድ ሂደታቸው እንዲታይ ማድረግ እ.ኤ.አ በ2015 ይካሄዳል ተብሎ በሚታሰበው አገር አቀፋዊ ምርጫ ሰማያዊ ፓርቲ እንዳይሳተፍ እና ለመዝጋት በደጋኑ የተተኮሰ የመጀመሪያው ቀስት ነው፡፡ ገዥው አካል ለሰማያዊ ፓርቲ የሚያስተላልፈው መልዕክት ግልጽ እና ግድፈት ሊደረግበት የማይችል ሀቅ ነው፡፡ ይህም ሁኔታ በአንክሮ ሲታይ በቅርቡ ባረፉት በአቶ መለስ ዜናዊ የተጻፈው የባለ ሶስት ድርጊት የረዥም ጊዜ ተውኔት ተከታይ ነው፡፡ እነዚህ የተውኔት ድርጊቶችም እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡ ድርጊት አንድ፡ “ምርጫው” ከመድረሱ በፊት የሰማያዊ ፓርቲ, አመራሮችን እና አባላትን የይስሙላውን ፍርድ ቤቶች በመጠቀም ማሰቃየት፣ ማስፈራራት፣ ሽባ እና አቅመቢስ ማድረግ፡፡ በዚያ መንገድ ሌላ ተጨማሪ የኃይል እርምጃዎች ቢወሰዱ በህዝቡ ዘንድ የተለመደው አካሄድ እንጅ የበቀል እርምጃ አይደለም የሚል እንደምታ እንዲኖር ከመሻት የመነጨ ነው፡፡ ድርጊት ሁለት፡ ምርጫው ከመድረሱ ጥቂት ወራት በፊት የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችን እና አባላትን ሰብስቦ በእስር ቤት ማጎር፡፡  ይሄም የይስሙላውን ፍርድ ቤት አንደውነት የፍርድ ሸንጎ የሚሰራ ለማስመሰል ነው፡፡ ድርጊት ሶስት፡ ከምርጫ በኋላ እ.ኤ.አ በ2005  (1997 ምርጫ) የተደረገውን  ጭፍጨፋ ድርጊት መድገም ነው፡፡!

የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችን እና አባላትን የህግ ሂደት እና ጥቃት በተመለከተ ሁለት አማራጮች አሉ፡፡ 1ኛ) በይስሙላው ፍርድ ቤት የፍርድ ሂደት ላይ ተስፋ በመቁረጥ እራስን መነቅነቅ እና በመሰላቸት ጥሎ መሄድ 2ኛ) እንደ ኪልኬኔ አገር ድመቶች ከይስሙላው ፍርድ ቤት ጋር ጎሮሮ ለጉሮሮ መተናነቅ እና የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችን እና አባላትን መብት ማስከበር፡፡

ገዥው አካል ኢትጵያውያን እና ሌሎች በይስሙላው ፍርድ ቤት የውሸት ማስመሰያ ምክንያት እራሳቸውን በመነቅነቅ ሁሉንም ነገር ይተውታል ወይም ደግሞ ትችት በመስጠት ብቻ ጥለው ይሄዳሉ የሚል እሳቤ ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡ ገዥው አካል በጊዜ ሂደት የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችም እንደ እስክንድር ነጋ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ አንዷለም አራጌ፣ አቡባከር አህመድ እና ሌሎችም  በእስር ቤት ታጉረው “ይረሳሉ” የሚል ስሌት አለው፡፡ ገዥው አካል የይስሙላው የፍርድ ቤት ማስፈራሪያ ዘመቻ በከፍተኛ ውጤታማነት እና ብቃት ላይ ተመስርቶ የሚቀጥል ላለመሆኑ ትንሽም እንኳ ቢሆን ጥርጣሬ የለዉም፡፡

የሰላማዊ ትግል ዋና ዓላማው የጨቋኙን አካል ተቋማት እና ህጎች በመጠቀም በጨቋኙ አካል ላይ ትግሉን በሰላማዊ መልኩ በማፋፋም መቀጠል ነው፡፡ በአጠቃላይ መልኩ ሲታይ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያለው ምንም ዓይነት የተፈጸመ ስህተት የለም፡፡ በገዥው አካል የይስሙላው ፍርድ ቤቶች ዘንድ የፍትህን ጥላ እንኳ ማግኘት እንደማይችል ማንም መገመት ይችላል፡፡ ማንም ቢሆን በውሸት እምነት ላይ በተመሰረተው የይስሙላው ፍርድ ቤት ፍትህ ሰበብ መሰቃየት የለበትም፡፡ ወደፊት ምን ሊከሰት እንደሚችል በእርግጠኝነት እናውቃለን፡፡ የክስ ሰነዱ ቀደም ሲል ተጽፎ ተዘጋጅቷል፣ በግልጽ ለመናገር ቀደም ሲል የነበረዉን የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ክስ ስማቸውን በመለወጥ፣ በማደስ እና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን በማካተት የክስ ሰነዶቹ እነዚህን ለመዳኘት በስራ ላይ ይውላሉ (በግልጽ አባባል ለማጥቂያነት ይውላሉ)፡፡

ያንን ትያትር ቀደም ሲል አይተነዋል፡፡ ክስ የቀረበባቸው የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች እና አባላት በየጥቂት ሳምንታት ልዩነት ከማጎሪያ እስር ቤቶች ወደ የይስሙላው ፍርድ ቤት እንዲመላለሱ ይደረጋል፡፡ የገዥው አካል አቃቤ ህግ ማስረጃ ለመፈለግ (የሩጫው ዕለት የተጠናቀቀ ስለሆነ እና ሌላ ተጨማሪ ማስረጃ ማግኘት የተሳሳተ እና ውኃ የሚቋጥር ባይሆንም) በሚል ስልት ብዙ የማዘግየት ስራዎችን በመስራት የተለመደውን የገዥውን አካል የበቀልተኝነት የሱስ ጥማት ለማርካት ጥረት ያደርጋል፡፡ የዋስትና መብት ጥያቄዎች ተከልክለዋል፣ ሺህ ጊዜ የሚጠየቁ ቢሆንም፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ሴቶች ይደበደባሉ፣ ህግወጥ አያያዝ ይፈጸምባቸዋል፣ እናም በእስር ቤት የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ይፈጸምባቸዋል፡፡ እርስ በእርሳቸው ላይ መተማመን እንዳይኖርም ጫና ይፈጸምባቸዋል፡፡ ህሊናቸውን እንዲሸጡ ገንዘብ እና ሌላ ሌላም ነገር ይሰጣቸዋል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲን ከፍተኛ አመራሮችን እንዲክዱ ላቅ ያለ ዋጋ የሚያወጡ ጌጣጌጦችን ይሰጧቸዋል፡፡ በጓደኞቻቸው፣ በፓርቲ አባላት እና አመራሮች እንዳይጎበኙ ክልከላ ሊጣል ይችላል፡፡ ለብቻ በአንድ ክፍል ውስጥ ሊታሰሩ ይችላሉ፡፡ የህክምና እርዳታ እንዳይደረግላቸው ክልከላ ሊደረግ ይችላል፡፡ በገዥው አካል በተቀጠረ ባለሙያ እንደተገለጸው እነዚህ እስረኞች  “በሚከረፋው እስር ቤት” የገሀነም ህይወት እንዲገፉ ሊደረግ ይችላል፡፡ ይህ ጉዳይ ለብዙ ጊዜ ማለትም እ.ኤ.አ በ2015 እስከሚደረገው አገር አቀፍ “ምርጫ” ድረስ ቀጣይነት ሊኖረው ይችላል፡፡ ዘዴው ቀላል ነው፡ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችን ሃሳብ ማስቀየስ፣ ማሸማቀቅ፣ ማስፈራራት፣ ከመሰረታዊ ዓላማቸው እንዲርቁ ማድረግ እና በአጠቃላይ መልኩ ደግሞ ምርጫ እየተባለ ከሚጠራው የይስሙላ ምርጫ ተሳትፏቸውን ሽባ ማድረግ ነው፡፡

ገዥው አካል የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችን ያለምንም ውይይት በፍጥነት ወደ እስር ቤት የመውሰዱን ሁኔታ በተመለከተ በእራሱ የይስሙላ ፍርድ ቤቶች ለምን ሊጠየቅ እና ሊሞገት እንደሚገባው አራት አሳማኝ ምክንያቶች አሉ፡፡ በመጀመሪያ የጅምላ ሰብአዊ መብት ረገጣው ተግባራዊ እንዲሆን የሚያግዙት የገዥው አካል ለጋሽ እና አበዳሪ ድርጅቶች (በተለይም የምራብ መንግሥታት) እነርሱ በሚያደርጉት ልገሳ ድርጊት እየተደረገ ያለውን የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ በተጨባጭ እንዲያዩት ይገደዳሉ፡፡ ለጋሽ እና አበዳሪ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እንዲስፋፋ እና ሰብአዊ መብት እንዲጠበቅ ደንታ አንደማይሰጣቸው የታወቀ ነው፡፡ ሁለተኛ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች የይስሙላ የፍርድ ሂደት በእራሱ በይስሙላው ፍርድ ቤት ላይ አንዲፈረጅበት ማድረግ ያስፈለጋል፡፡ ገዥው አካል እራሱ ለይስሙላው የፍርድ ቤት ሂደት መቅረብ አለበት፡፡ ሶስተኛ የይስሙላው ፍርድ ቤት የፍርድ ሂደት ዛሬ በፍትህ ወንበር ላይ ተቀምጠው (እና ሌሎች ከመጋረጃ ጀርባ ተቀምጠው በዳኝት ወንበር ላይ የተሰየሙትን ዳኞች ጣቶች የሚጠመዝዙ) በእራሳቸው ዳኝነት ነገ እንደሚዳኙ በመገንዘብ ከፍተኛ ተቃውሞ መኖር አለበት፡፡ ዛሬ ከህግ አግባብ ውጭ ለመፍረድ በወንበር ላይ የተቀመጡት ሰዎች ከፍትህ ረዥም ክንድ ሊያመልጡ እንደማይችሉ የኑረምበርግ የፍርድ ሂደትን፣ የካምቦዲያ ፍርድ ቤት ልዩ የፍርድ ቤት ሂደትን፣ የሩዋንዳ የዓለም አቀፉን የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የፍርድ ሂደትን፣ የደቡብ አፍሪካ የእውነት እና የዕርቅ ኮሚሽንን፣ የቻርለስ ቴለር የዓለም አቀፉን የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የፍርድ ሂደትን እና የቦካሳን እና ሌሎች የአገር ውስጥ የፍርድ ሂደቶች ሊያስታውሱ ይገባል፡፡ ሁኔታዎች ሁልጊዜ ይገለባበጣሉ፡፡ ስለ ሁኔታዎች መገለባበጥ ጉዳይ እስቲ ደጋግማችሁ አስቡ፡፡ ሁልጊዜ ይገለባበጣሉ!

ከደቡብ አፍሪካ ታሪክ ብዙ ቁም ነገሮችን ልንማር እንችላለን፡፡ እ.ኤ.አ በ1964 የአፓርታይድ ገዥ አካል የአፍሪካ ኮንግረስ መሪዎችን እና ሌሎች የጸረ አፓርታይድ ተሟጋቾችን ኔልሰን ማንዴላን፣ ዋልተር ሲሱሉ፣ ጎቫን ኢምቤኪ፣ ራይሞንድ ሃላባ፣ አህመድ ካትራዳ፣ ኤሊያስ ሞሶሌዲ እና ቢሊ ኔይር ሰብስቦ በይስሙላው የአፓርታይድ የፍትህ ችሎት ፊት ገተራቸው፡፡ እነዚህ ሰባት አመራሮች እንደ “ጣይቱ ሰባት” የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ሁሉ በአፓርታይድ የይስሙላ ፍርድ ቤቶች ፍትህን እናገኛለን የሚል እምነት አልነበራቸውም፡፡ ሆኖም ግን መሰረተ ቢስ ክሱን አጥብቀው ተቃውመውታል፡፡ ይህንንም በማድረጋቸው  ለደቡብ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለጠቅላላው ዓለም ታሪክ ሰርተዋል፡፡ የሰባቱ የጸረ አፓርታይድ መሪዎች የሪቮኒያ የፍርድ ሂደት ለዛሬዋ ደቡብ አፍሪካ ፍትህ መስፈን መሰረትን የጣለ ነው፡፡

አራተኛው እና ምናልባትም በጣም ጠቃሚው ነገር የይስሙላውን ፍርድ ቤት አጥብቀን መዋጋት አስፈላጊ ነው ምክንያቱም በህግ የበላይነት ለሚያምኑ ሁሉ ለህጉ ተገዥ ላልሆኑት ወንጀለኞች የህይወት እና የመተንፈስን ያህል ጠቃሚ መሆናቸውን ሊያስተምሩ የሚችሉበት ብቸኛው መንገድ ነው፡፡ በህግ የበላይነት ላይ እምነት ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው ስለወንጀለኞች ማስተማር እና መጮህ ያለባቸው፡፡ እራሱ ያወጣቸውን እና ያጸደቃቸውን ህጎች የሚደፈጥጥ ወሮበላ መንግስት በእራሱ እና በህግ የበላይነት ላይ ንቀትን የሚፈለፍል ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ  የህግ የበላይነትን ለመያዝ እና ለመንከባከብ ከማንም የተሻለ መሆን አለበት፡፡

“የጣይቱ ሰባት የህግ ጥበቃ ፈንድን (ድጎማ/ዝክር)” እንደግፍ፣

Semayawi Party Legal Defense Fund 2ሁሉንም አንባቢዎቼን “ለጣይቱ ሰባት የህግ ጥበቃ ፈንድ (ድጎማ/ዝክር)” እንድታዋጡ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ የሰኞ ትችት መጣጥፌን ለበርካታ ዓመታት ስታነቡ የቆያችሁ በርካታ ወገኖቼ እንዳላችሁ እገነዘባለሁ፡፡ የሰኞ ትችት መጣጥፌ አሁን ስምንተኛ ዓመቱ መሆኑ ነው፡፡ አንዳንዶች ከእኔ ጋር በሁሉም ነገር በሀሳብ የማይግባቡ እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ እንደዚሁም በርካታ ለመቁጠር የሚያስቸግር ብዛት ያላቸው አንባቢዎቼ ደግሞ ቢያንስ በጥቂት ነገሮች ላይ ከእኔ ሀሳብ ጋር እንደሚስማሙ እገነዘባለሁ፡፡ የእኔ አቤቱታ የቀረበው ለእነዚህኛዎቹ ወገኖቼ ነው፡፡  በኢትዮጵያ በገዥው አካል የይስሙላው ፍርድ ቤት የፍርድ ሂደት እየተሰቃዩ ያሉትን “የጣይቱ ሰባት” ጀግኖችን በመርዳቱ ጥረት እያንዳንዳቸው ማገዝ እንዲችሉ ያቀረብኩትን ሀሳብ በመደገፍ በተግባር እንዲያሳዩ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ እርዳታ እንዲያደርጉም በአጽንኦ እማጸናለሁ፡፡ ምንም ትንሽም ቢሆንም እንኳን ስጋት አይደርባችሁ፣ ትልቅ ጋን በትንሽ ጠጠር ይደገፋል ነውና፡፡ ባለፉት ዓመታት ምን ለመስራት እንዳቀድኩ አድናቆታቸውን የገለጹልኝ በርካታ ኢትዮጵያዊያን/ት ወገኖቼን በተለያዩ ጊዚያት አግኝቸ ነበር፡፡ ምንም ይሁን ምን ለሰራሁት ሁሉ ምስጋናን አልሻም፣ በኢትዮጵያ ያለው የሰብአዊ መብት ያለመሻሻል ሁኔታን ስመለከት ካሁን የበለጠ ሺ አጥፍ መሆን የሆነ ስራ መስራት ነበረብኝ በማለት አራሴን ወቅሳለሁ፡፡

የዛሬ ሰባት ዓመት በዚሁ ወር “ትንሿ ወፍ እና የጫካው እሳት: የዲያስፖራው ማህበረሰብ የሞራል ትረካ” በሚል ርዕስ ስር በትችት መጣጥፌ ላይ ምን ለመስራት እንዳሰብኩ ለአንባቢዎቼ ተናግሬ ነበር፡፡ በዚህም መሰረት ማድረግ የምችለውን ሁሉ እያደረግሁ ነው፡፡ አሁን አንባቢዎቼን መጠየቅ የምፈልገው ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ እንዲያደርጉ ነው፡፡ እስቲ በጥሞና አስቡት ወገኖቼ በመቶዎች እና በሺዎች የሚቆጠሩ ትናንሽ ወፎች አንድ ላይ ተባብረው በመስራት የጫካን እሳት መግታት ይችላሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ የ”ጣይቱ ሰባት” ጀግኖች በአረመኔው ገዥ አካል የእሳት ማቀጣጠያ ጉድጓድ ውስጥ ናቸው፡፡ ሲቃጠሉ መመልከት አለብን ወይም ደግሞ ከእነርሱ ጎን በመቆም ታግለን ለድል መብቃት አለብን፡፡ “ለጣይቱ ሰባት የህግ ጥበቃ ፈንድ(ድጎማ/ዝክር)” እርዳታችሁን እንድታደርጉ እማጸናለሁ፡፡ ለወደፊቱ የኢትዮጵያ ወጣት ወንዶች እና ሴቶች ተቆርቋሪነታችሁን አሁኑኑ በተግባር አሳዩ፡፡

የሰማያዊ ፓርቲን ሴት ጠይቁ… 

Free the Taitu Seven Amharicከቀድሞዋ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ማጊ ታቼር ጋር በብዙ ነገሮች ላይ እንደማልስማማ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሯ በሴቶች የፖለቲካ አመለካከት ላይ በነበራቸው እምነት ምንም ዓይነት ያለመስማማት አዝማሚያ አልነበረኝም፡፡ “በፖለቲካው ዓለም የተነገረ ምንም ነገር በፈለጋችሁ ቁጥር ወንድን ጠይቁ፡፡ የተሰራ ምንም ነገር በፈለጋችሁ ጊዜ ግን ሴትን ጠይቁ“ ነበር ያሉት፡፡ ሰለሆነም ለእነዚህ ወጣት ሴት የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች እና አባላት አንድ ነገር እናድርግ፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ ሴቶች እሩጡ፣ እሩጡ…! ለነጻነት የምታደርጉትን ሩጫ በጽናት ቀጥሉበት…

በዚህ ድረ ገጽ የእርዳታ እጃችሁን ለምትዘረጉ:   http://www.semayawiusa.org/donate/

በባንክ ሐዋላ ለመርዳት ለምትፈልጉ

ለሰሜን አሜሪካ የሰማያዊ ድጋፍ የሚከፈል (የአሜሪካ ባንክ (Bank of America)

የሂሳብ ቁጥር፡   435031829977

የመላኪያ ቁጥር፡ 051000017

 

በቼክ ለመርዳት ለምትፈልጉ፡

ለሰሜን አሜሪካ የሰማያዊ ድጋፍ የሚከፈል

የ.ፖ ሳ.ቁ 75860

ዋሽንግተን ዲሲ. 20013

 

                                      ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

መጋቢት 9 ቀን 2006 ..