ቤተ-መንግስት ስር የሚኖሩ ቤት አልባዎች በጅብ መንጋ ልንበላ ነው አሉ

Addisadmassnews.com

Apri 7, 2014

ቦታው ለልማት ይፈለጋል ተብሎ ቤት ሲፈርስ፣መጠለያ አጥተው ቤተ-መንግስት ስር መኖር የጀመሩት  48 ቤት አልባዎች፤ሰሞኑን “በጅብ መንጋ ልንበላ ነው” ሲሉ ምሬትና አቤቱታቸውን ገለፁ፡፡ ከጅቦቹ ይከላከሉናል ብለን የሰበሰብናቸው ውሾችም በወረዳው ባለስልጣናት በመርዝ ስለተገደሉብን ከፍተኛ ስጋት ላይ ነን ብለዋል – ቅሬታ አቅራቢዎቹ።

የወረዳ ስምንት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ደሳለኝ ደበሌ ስለጉዳዩ ጠይቀናቸው ሲመልሱ፤በወረዳው ሸራተንና ፓርላማ በመባል የሚታወቁ ሁለት ፕሮጀክቶች እንዳሉ ገልፀው፤ በሸራተን ፕሮጀክት ለመልሶ ማልማት 1319 ቤቶች ሲፈርሱ፣ምትክና ካሳ እየሰጠን መመሪያው የሚፈቅድላቸውን አስተናግደናል ብለዋል፡፡ በወረዳው ረጅም ዓመት ለኖሩ ምንም መረጃ የሌላቸው ከ60 በላይ ሰዎችም አስተናግደናል ይላሉ- ሥራ አስፈፃሚው፡፡ በሸራተን ዙሪያ በጥገኝነትና በተከራይነት ከ15-23 ዓመት እንደኖሩና የቀበሌ መታወቂያ እንዳላቸው የነገሩን  ቤት አልባዎች የወረዳ ኃላፊዎቹን ይወቅሳሉ፡፡ “ከዛሬ ነገ ቤት ይሰራላችኋል፤መጠለያ ተፈልጎ ትገባላችሁ” ሲሉን ቢቆዩም እስካሁም መፍትሄ አላገኘንም ይላሉ፡፡ አሁን ከቤቱም በላይ ሃሳብ የሆነባቸው የጅቦቹ ጉዳይ ነው፡፡ ጅቦች ከነጋ በኋላም እየመጡብን ከፍተኛ ስጋት ፈጥረውብናል ብለዋል – ነዋሪዎቹ፡፡

“ወረዳው ቀደም ሲል በእኛው ጉዳይ ከአዲስ አድማስ ጥያቄ ቀርቦለት ‘ከክፍለ ከተማው ጋር ተመካክረን የመጠለያ ቦታ አፈላልገን አግኝተናል’ የሚል ምላሽ ቢሰጥም እኛ ግን እስካሁን መፍትሄ አላገኘንም” ያሉት ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ የአምስት ልጆች አባት፤ በላስቲክ ቤት ውስጥ መኖራቸውን በመቀጠላቸው  ጅቦች ስጋት እንደፈጠሩባቸው ጠቁመው፣ “ዜጎች እንደመሆናችን መንግስት መፍትሄ ይፈልግልን” ሲሉ ተማፅነዋል፡፡

የወረዳ ስምንት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ደሳለኝ በበኩላቸው፣ “ከዚህ በፊት ጉዳዩን እየተመለከትን በወረዳው እንደመኖራቸው መንግስት የእነዚህን ዜጎች ችግር የመፍታት አቅም ይኖረዋል አይኖረውም የሚለውን ለክ/ከተማው አቅርበናል” ካሉ በኋላ በክፍለ ከተማው ወረዳ 14 ባለወልድ ጀርባ የቆርቆሮ መጠለያ እንደነበረና መጠለያው ከተቃጠለ በኋላ ቦታው ባዶ መሆኑን በማስረዳት፣ እዚያ ቦታ ላይ የቆርቆሮ መጠለያ እንዲሰራ አመልክተን ነበር ይላሉ፡፡  “በወቅቱ የነበሩት የክ/ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ፣ ከካቢኔ አባላት ጋር ተመካክረው ምን ያህል በጀት እንደሚፈጅ ሰርተን እንድናቀርብ ገልፀው ነበር” ያሉት ስራ አስፈፃሚው፣ በዚህ መሰረት የወረዳው ኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ባለሙያዎች ምን ምን እንደሚያስፈልግ ሰርተው፣ ለክ/ከተማው አቅርበው ነበር ይላሉ፡፡ ይሁን እንጂ በ2005 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ የመዋቅር ለውጥ በመደረጉና የቀድሞው የክ/ከተማው ስራ አስፈፃሚ ከቦታው በመነሳታቸው፣ የእነዚህ ዜጎች ጉዳይ ሊቀጥል እንዳልቻለ አቶ ደሳለኝ አስረድተዋል፡፡

“በሸራተን ፕሮጀክት ውስጥ ቤት የሚጠይቁት ቤት የማግኘት መብት ኖሯቸው ሳይሆን በወረዳው ብዙ ጊዜ ስለቆዩ የሚቻል ነገር ካለ ብለን የጀመርነው ነበር” ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፣ ነገር ግን ገና ለገና ቤት እናገኛለን በሚል ከጎዳና ላይ እየገቡ ላስቲክ ቤት እየሰሩ እንደሚቀመጡና ረጅም አመት የኖሩትን ለመለየት በተደረገው ማጣሪያ 31 አባወራዎች መኖራቸውን፣እነዚህንም ከነቤተሰቦቻቸው በፎቶ አስደግፈው መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡ የጅቦቹን ጉዳይ በተመለከተ፣ ኮተቤና በአካባቢው ለመንገድ ስራ ጫካ ሲነካ እየሸሹ የሚመጡ መሆኑን ገልፀው፣ በሸራተን ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን በባለወልድ አካባቢ ለነዋሪዎች ስጋት በመሆናቸው ወረዳው ከደንና የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ጋር በመመካከር፣መፍትሄ በመፈለግ ላይ እንደሆኑ ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል፡፡
“ወደፊት በወረዳው ኮንዶሚኒየም ቤት ደርሷቸው የሚለቀቁ ቤቶች ሲኖሩ ቅድሚያ ይሰጣቸዋል” ያሉት ስራ አስፈፃሚው፤ በዚህ ጊዜ እንዲህ እናደርግላቸዋለን ለማለት እንደሚቸገሩና ለክ/ከተማው ሲወስን ጉዳያቸው እንደሚታይ ተናገረዋል፡፡

ሐምሌ 27 ቀን 2005 ዓ.ም ለንባብ በበቃው አዲስ አድማስ ጋዜጣ “ትራሳቸውን ቤተ-መንግስት ግርጌያቸውን ሸራተን ያደረጉ ቤት አልባዎች” በሚል ርዕስ ስለእነዚሁ 48 ቤት አልባ አባወራዎች መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ የወረዳ ስምንት ዋና ስራ አስፈፃሚ ከክ/ከተማው ጋር በመነጋገር፤ ለቤት አልባዎች የቆርቆሮ መጠለያ ለመስራት ቦታ በመፈለግ ላይ እንደሆኑ ገልፀውልን ነበር፡፡