ከአገር መውጣት የማይችሉ ባለሥልጣናት በጭንቀት ውስጥ ናቸው

አሁን ያለው ኢህአዴግ ላዩ በቀለም ቀቢ የተዋበ ይመስላል

Source:  Goolgule.com

April 10, 2014

 

EPRDF (TPLF) in the good old days.

EPRDF (TPLF) in the good old days.

 

ኢህአዴግ በሙስና ስም የ”ማጥራት ዘመቻ” ማካሄዱን ተከትሎ የተከሰተው አለመተማመንና እርስ በርስ በጥርጥር የመተያየት ችግር ካድሬውን ማስጨነቁ ተጠቆመ። ኢህአዴግን ለመሰናበት የሚፈልጉ በርካታ ካድሬዎች “ለምን” በሚል የሚቀርብላቸውን ጥያቄ በመፍራት የግድ ፓርቲውን መስለው እንደሚኖሩ ተገለጸ።

የጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ ቀደም ሲል ኢህአዴግን ተሰናብተው የወጡና በተለያዩ የውጪ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው በማገልገል ላይ ካሉ ያገኘውን መረጃ በመጥቀስ እንደዘገበው፣ የቀድሞ የትግል ጓደኞቻቸው “በደህና ጊዜ ተገላገልክ” በሚል በፓርቲው ውስጥ ችግር ስለመኖሩ እየነገሯቸው ነው። አብዛኞቹ ኢህአዴግን ተለይተው በሰላም ስለመኖር እንደሚያስቡ ነው የተሰማው።

የቤተሰቦቻቸው የወደፊት እድልና የነሱ በፍርሃትና በጭንቀት መኖር አሳዛኝ እንደሆነ የነገሩት የቀድሞ የኢህአዴግ ሰዎች “አሁን ያለው ኢህአዴግ በቀለም ቀቢ የተዋበ ይመስላል” በማለት አንድ በሚኒስትር ዲኤታ ማዕረግ እያገለገለ ያለ የቀድሞ ጓደኛቸው እንደነገራቸው ገልጸዋል።

ለስራ እንኳን ካገር መውጣት የማይችሉ ባለስልጣኖች እንዳሉ ዘጋቢያችን አመልክቷል። በተቀመጡበት ሃላፊነት ወደ ውጪ የሚያስኬድ አጋጣሚ ሲኖር የሚከለከሉ እንዳሉም ያገኛቸውን መረጃዎች ጠቅሶ ዘግቧል። ለሃላፊዎቹ ደህንነት ሲባል የሚሰሩበትን ተቋምና ስም መናገር እንደማይችሉ በመጥቀስ መረጃውን የሰጡት ክፍሎች “ባለስልጣኖቹ በመካከላቸው እርስ በርስ መተማማን ስለማይችሉ ችግራቸውን መወያየት እንኳን አይችሉም” ብለዋል፡፡

“በጣም የሚቀርቡኝ ጓደኞቼ ገንዘብ ወደ ውጪ እንድወስድላቸው እስከመጠየቅ ደርሰዋል” ሲሉ የገለጹት የቀድሞ የኢህአዴግ ባለስልጣን፣ ፓርቲው በሙስና ስም ያካሄደው የሽግግር ወቅት የማጥራት ርምጃ የፈጠረው ስሜት አሁን ድረስ እንዳለ ጠቁመዋል።

ሰሞኑንን ወደ አሜሪካ ያቀኑ የቀድሞ የኢህአዴግ ሰው በማግኘት ተመሳሳይ መረጃ ያሰባሰበው ዘጋቢያችን “ኢህአዴግ በከፍተኛ የመበስበስ አደጋ ውስጥ ይገኛል። በዚህም የተነሳ ካድሬው ተዥጎርጉሯል” ሲል ሪፖርት አድርጓል። ኢህአዴግ በውስጥ ያለበትን ችግር ለማድበስበስ የአባይ ግድብ ላይ ትኩረት በመስጠት “የንቅናቄ ሃይል” በማስፋፋት ላይ እንደሆነም ጠቁሟል።

ድፍን ህዝብ የአባይ ግድብን አስመልክቶ ያለው ስሜት በበጎ መልኩ የሚታይ በመሆኑ ኢህአዴግ ይህንኑ የህዝብ ስሜት ለቅስቀሳና ለበሽታው መደበቂያ ለማድረግ እየተጠቀመበት እንደሆነ ተጠቁሟል። የህጻናት ፕሮግራሞች ሳይቀሩ አባይ ላይ ያነጣጠሩ ቅስቀሳዎች እያስተላለፉ መሆናቸውን ያመለከቱት ሰው፣ “ስለ አባይ ግድብ የሚባለውና የሚሰራው ፕሮግራም ችግር የለውም። በአግባቡ ቢሰራበት ብሔራዊ ስሜት ሊገነባበትም በተቻለ ነበር። ይሁን እንጂ ዓለማው የችግር ማለባበሻ እንዲሆን መደረጉ ነው” ብለዋል።

“መለስ ኢትዮጵያን ቢወድ ኖሮ ከባድመ ጦርነት በኋላ የፈረሰውን ብሔራዊ አንድነትና መግባባት መልሶ መትከል ይቻል ነበር” በማለት የተናገሩት እኚሁ ሰው “በወቅቱ ይህንን ሃሳብ ያነሱ ሰዎች ነበሩ” ሲሉ ቁጭታቸውን ይሰነዝራሉ። በማያያዝም ኢህአዴግ የአባይን ግድብ ተንተርሶ ብሔራዊ አንድነት የሚገነባበት፣ መቀራረብና በጠረጴዛ ዙሪያ በመነጋገር ብሔራዊ መግባባት የሚደረስበት፣ ለወደፊቷ ኢትዮጵያ መሰረት የሚጣልበት ቢያደርገው እውነተኛው የኢትዮጵያ ህዳሴ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝን በውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቴድሮስ አድሃኖም ለመተካት ህዋሀቶች የሚያደርጉት ሽርጉድ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ሪፖርት መቅረቡ ተሰምቷል። ይኽው ሪፖርት የቀረበላቸው ክፍሎች ቀደም ሲል እንዳደረጉት የህወሃትን ከፍተኛ አመራሮች በማነጋገር ስህተት እንዳይሰሩ እየወተወቱ ነው።