የጥራት ጉድለት ሕመም የሆነበት የሕክምና ትምህርት

 

 

ሪፖርተር ጋዜጣ

December 21, 2014

 

በአዳራሹ የታደመው የሕክምና ባለሙያ በተለያየ ዘመን በተለያየ የሥልጠና ማዕከል የተመላለሰ ነው፡፡ በሰባዎቹ መጨረሻና በሃያዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኙት ጐን ለጐን ከአንድ ቦታ ተገኝተዋል፡፡

የሕክምና ትምህርት በአገሪቱ ምን ይመስላል? የታዩ ተግዳሮቶችና ቀጣዩ ዕርምጃ ምን መሆን ይኖሩታል? በሚሉና በሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ሁሉም ቀጠሮቸውን አክብረዋል፡፡

 

ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል

ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል

 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሃምሳኛ ዓመት በዓል አከባበር ሥነ ሥርዓት አካል ሆኖ “Celebrating 50 Years of Excellence in Training of Health Professionals, Community Service and Research፡ Roadmap to Health Professionals Training in Ethiopia” በሚል ርዕስ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ የጤና ሳይንስ ትምህርት ቤቱ ቀደምት ተማሪ እንደሆኑት የ79 ዓመቱ ዶ/ር ጳውሎስ ቀንዓና በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አምስተኛ ዓመት ተማሪ እንደሆነው ወጣት ቴዎድሮስ ወርቁ ያሉ ተማሪዎችም በአንድ ላይ ለመምከር ተቀምጠዋል፡፡

በትምህርት ቤቱ አጀማመር የተማሪዎች ሥልጠና በብዙ መልኩ በወቅቱ የአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሁነቶች የተቃኘ እንደነበር የሚያወሳ ጽሑፍ በዶ/ር ጳውሎስ ቀርቦ ነበር፡፡ በትምህርት ቤቱ የመጀመሪያው 10 ዓመት ውስጥ የተማሪዎች ሥልጠና ምን እንደሚመስል በወቅቱ ተማሪ የነበሩት ዶ/ር አብርሃም አስናቀ በጽሑፍ አስቃኝተው ነበር፡፡ የጤና ሳይንስ ትምህርት ቤቱ የመካከለኛ ዕድሜ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል በሚለው ላይ በዶ/ር አበባ ተክለ ጊዮርጊስ፣ የትምህርት ቤቱ የቅርብ ጊዜ ዕርምጃና አቅምስ እንዴት ይታያል በሚለው ላይ ደግሞ በዶ/ር አበበ በቀለ ጥናቶች ቀርበዋል፡፡ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑትና የትምህርት ቤቱ የቀድሞ ተማሪ ዶ/ር አሚር አማንም ጽሑፍ አቅራቢ ነበሩ፡፡

በመድረኩ ከሕክምና ትምህርትና ከሕክምና አገልግሎት ጋር በተያያዘ በርካታ ጉዳዮች ተነስተው ነበር፡፡ ትምህርት ቤቱን ተጠቃሽ ያደረጉና ለሌሎችም የሕክምና ትምህርት ቤቶች ጠቃሚ ይሆናሉ የተባሉ ነገሮችም ተነስተው ነበር፡፡ የተቀናጀ ሥርዓተ ትምህርት በዚህ ረገድ እንደምሳሌ የተነሳ በጐ ነገር ነበር፡፡ እንደዚህ ያሉ አዎንታዊ ገጽታዎች ቢነሱም የተማሪዎች ቁጥር መብዛትን ዓላማ ባደረገ አካሄድ የሕክምና ትምህርት ጥራት ማሽቆልቆል ትልቅ ትኩረት የተሰጠው አጀንዳ ነበር፡፡

ቁጥራቸው ትንሽ ስለነበር የተማሪና የአስተማሪ ትውውቅ አስተማሪዎች አንድ በአንድ ተማሪን ለይተው የአባት እንዲያውም የአያታቸውን ስም ሁሉ እስከማወቅ እንደነበር የቀደሙት ተማሪዎች ሲያወሩ የዛሬ የትምህርት ቤቱ አስተማሪዎች ደግሞ ከወንበር አልፎ ተርፎ ተማሪዎች በፈሰሱበት ክፍል እንደሚያስተምሩ፣ ታካሚዎች ሲጎበኙም አሥራ አምስት የሚሆኑ ተማሪዎችን አስከትለው እንደሆነ ገለጹ፡፡

በሕክምና ትምህርት የተማሪን ቁጥር መጨመር ፈፅሞ ከጥራት ጋር አብሮ የሚሄድ እንዳልሆነ የሚናገሩት ዶ/ር አበበ ለጥራት ትኩረት እየተሰጠ ባለመሆኑ እየደረሰ ያለው ችግር ይበልጥ በግልፅ የሚታየው ወደ ሕክምና ትምህርት ቤቶች በገፍ እየገባ ያለው ተማሪ ተመርቆ ሲወጣና የቀድሞ ደግሞ አገልግሎቱን ጨርሶ ሲወጣ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ከአምስት ወደ ስምንት ከዚያም በአንድ ጊዜ ወደ 27 ያደገው የሕክምና ትምህርት ቤቶች ቁጥር ቆም ተብሎ ሊጤን እንደሚገባ የሕክምና ትምህርትም መመራት ያለበት በሙያ መሆን አለበት ሲሉ አስረግጠዋል፡፡

በሕክምና ትምህርት ዕውቀት፣ ሥልጠናና አመለካከት ወሳኝ ነገሮች እንደሆኑ የሚናገሩት ዶ/ር አበበ፣ ‹‹ብዙ ጊዜ የሚባለው የኢትዮጵያ ሐኪም የአመለካከት፣ የሥነ ምግባር ችግር አለበት ነው፡፡ እኛ 45 ሆነን ስንማር የዛሬዎቹ 360 ናቸው›› ይላሉ፡፡ በተማሪዎች ቁጥር መብዛት አስተማሪ በቂ ጊዜ ሳይሰጠው፣ ከአስተማሪ ማግኘት ያለበትን ነገር በበቂ ያላገኘ ተማሪ እንዴት በጨዋነት ለታማሚ ጊዜ ሊሰጥ ይችላል? የሚል ጥየቄ ያነሳሉ፡፡

የሕክምና ጥበብ ሁሉን ዓይነት የላብራቶሪና ሌሎች ምርመራዎችን እያዘዙ ብቻ የሚኬድበት ሳይሆን ለታካሚዎች የጤና ሁኔታ (Medical History) እንዲሁም ለአካላዊ ምርመራ (Physical Examination) ትልቅ ቦታ የሚሰጥበት መሆኑን የገለጹት ዶ/ር አብርሃም አስናቀ፣ ‹‹ታካሚዎች የሚሉንን ቢቻለን ወደ እዝነ ህሊናችን እንውሰድ፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ እናዳምጣቸው፡፡ ለመስማት ያህል ግን አንስማቸው›› ብለዋል፡፡ የታካሚዎች ስሜት መረዳት መቻል እንደሚያስፈልግ፤ ታካሚዎች እንዲናገሩ የማይጋብዝ አቀራረብ ግን አደገኛ መሆኑንም ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡ ዓመታት ወደኋላ ተመልሰው ሐኪሞች የታካሚዎችን አጠቃላይ የጤና ሁኔታ በአንድና በሁለት ብቻ ሳይሆን በብዙ ገፅ ይፅፉ የነበረበትን ጊዜ አስታውሰዋል፡፡

ሐኪሞች በጥድፊያ ምናልባትም ትኩረታቸው እንደተከፋፈለ በግልፅ መረዳት በሚቻልበት ሁኔታ ውስጥ ሆነው ታካሚ የሚሰማውን እንዲናገር የሚጠይቁበት፤ ሐኪም የመሆን ምስጢር ያለው የቱ ላይ ነው? እስኪያስብል ቀላል ሊባል ለሚችል የጤና እክል ብዙ ዓይነት የላብራቶሪ ምርመራ የሚታዘዝበት የአገራችን የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ እውነታ ግን ዶ/ር አብርሃም ከሚሉት ብዙ የራቀ ይመስላል፡፡

የትምህርት ጥራት ጉዳይ በመምህራንና በሐኪሞች ብቻም ሳይሆን ተማሪዎችም እዚሁ ጉዳይ ላይ ያነጣጠሩ ጥያቄዎቻቸውን አንስተው ነበር፡፡ ተማሪዎች በዚህ ረገድ የተግባር ልምምዳቸው ላይ አንድ ሕመምተኛን ለማየት ብዙ ሆነው መንቀሳቀሳቸው በልምምዳቸው ላይ ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ገልጸዋል፡፡ በእርግጥ ጥራትን ከጥያቄ ውስጥ የከተተው የተማሪዎችን ቁጥር የማብዛት ዕርምጃ የሥነ ምግባር ጥያቄም እንደሚያስነሳ የሚገልጹም አሉ፡፡ አልጋ የያዙ ታማሚዎች በቀን አሁንም አሁንም በተማሪዎች መታየት ሕመምተኞቹ ላይ የሚያሳድረው ድካምና መሰልቸትን ይጠቅሳሉ፡፡

ቴዎድሮስ በመድረኩ ጥራትን በሚመለከት በሌሎች የተንፀባረቁ ሐሳቦችን ይጋራል፡፡ በሕክምና ትምህርት ትልቅ የምርምር ክፍተት መኖሩን አንድ ዋርድን በሚመለከት የቀደመ ሥራ ማግኘት እንኳ ቀላል አለመሆኑን ይናገራል፡፡ ‹‹ሁሌም ማለት ይቻላል ስንማር የሚጠቀሰው የምዕራባውያን ዳታ ነው፤›› የሚለው ቴዎድሮስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕክምና ከመቼውም በበለጠ የቡድን ሥራ እየሆነ ባለበት በአሁኑ ወቅት በአገራችን የሕክምና ትምህርት አገልግሎት አሰጣጥም በዚህ ረገድ ክፍተት መኖሩ የጠቀሰው ሌላ ችግር ነው፡፡

በሕክምናው ዘርፍ የአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣም ለብዙ ችግሮች መሠረት መሆኑን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሐኪም የሆኑት ዶ/ር የወንድወሰን ታደሰ ይገልጻሉ፡፡ የዘርፉ አቅም ደካማ መሆንና የዕቅዶች የተቀናጁ አለመሆን የፈጠረው ተደራራቢ ሥራ መኖሩን መንግሥትም ባለሙያውም እኩል የሚገነዘበው ቢሆንም ይህን ተደራራቢ ሥራ ለመከወን እየተሄደ ያለበት ፍጥነት ላይ ትልቅ ልዩነት፣ አለመግባባትም እንዳለ ለማስረዳት ይሞክራሉ፡፡

እሳቸው ፍጥነት ሲሉ የሚያተኩሩት የሕክምና ተማሪዎችንና የሕክምና ትምህርት ቤቶችን የማብዛቱን ሩጫ ሲሆን፣ ውስን አጭር ጊዜ አስቀምጦ በዚህ ጊዜ ይህን ያህል የሕክምና ተማሪዎችን እናስመርቃለን ከሚል ጥድፊያ ይልቅ ሩጫውን ገታ አድርጎ ፍጥነት የሚያስከትለውን አደጋ በመረዳት ቢያንስ አማካይ መንገድ መፈለግ መፍትሔ ነው ይላሉ፡፡

ኢሕአዴግ ሥልጣን በያዘበት በመጀመሪያዎቹ 10 ዓመታት ውስጥ የአገሪቱን የጤና ችግር ነርሶችንና የጤና መኮንኖችን አሠልጥኖ በማውጣት እፈታለሁ ብሎ በማመኑ ሥልጣን በያዘ በ12 ዓመታት ውስጥ ሁለት የሕክምና ትምህርት ቤቶችን ብቻ በመክፈት በአገሪቱ የሕክምና ትምህርት ቤት ቁጥርን አምስት ማድረሱን በማስታወስ፤ እንዳመነው የነበረውን የጤና ተግዳሮት በጤና መኰንኖችና ነርሶች መፍታት እንደማይቻል ሲረዳ የተያያዘው ዶክተሮችን በብዛት የማስመረቅ ሩጫ ደግሞ ለባለሙያዎች ቸልተኝነት፣ ለሥነ ምግባር ጉድለቶችና ለሌሎችም ችግሮች ምክንያት እንደሆነ ያመለክታሉ፡፡ ቢሆንም ግን በአሁኑ ወቅት መንግሥትም ችግሩን እየተገነዘበው በመሆኑ ከባለሙያው ጋር መግባባት ላይ እንደሚደረስና ነገሮች እንደሚለወጡ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡

በሕክምና የትምህርት ጥራት ሲነሳ ከሕክምና ትምህርት ቤት መከፈት ጋር በተያያዘ በግሉ ዘርፍ ተግባራዊ እየሆነ ያለው መስፈርት በመንግሥትም መተግበር እንዳለበት ዶ/ር አበበ ጠቁመው ነበር፡፡ ሆስፒታሎች፣ ሰዎችም እስካሉ ድረስ እየባለ በሚመስል የመማሪያ ክፍሎችና ላቦራቶሪዎችን ብቻ እያዩ የሕክምና ትምህርት ቤቶችን የመክፈት ነገር አዋጭ እንዳልሆነ ይህንንም የሚመለከተው የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ ሊያጤነው ይገባል ይላሉ፡፡

በሌላ በኩል ግን የሕክምና ትምህርት እጅግ በጣም ውድ መሆኑን የሚናገሩት ዶ/ር የወንድወሰን፣ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ሕክምና በግል ዘርፍ እንዲሰጥ የሚፈቅድ አይደለም የሚል ጠንካራ አቋም አላቸው፡፡ ‹‹በግል ማንም የሚገባውን ያህል ኢንቨስት ሊያደርግ አይችልም አቅምም የለውም›› የሚሉት ዶ/ር የወንድወሰን፣ አሁን ያለው ነገር አስተማሪ ሳይኖር፣ የተማሪዎች የተግባር ልምምድ እንዴት ይሆናል? የሚለው ሳይታይ ሕክምና ትምህርት ቤት መክፈት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በዚህ መልኩ ቁጥራቸው እየጨመረ ያለው የግል የሕክምና ትምህርት ቤቶች በተለያየ መልኩ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደሩ መሆናቸውንም ይገልጻሉ፡፡

መምህራን ጊዜያቸውን በሚጋፋ መልኩ ጐን ለጐን በግል ትምህርት ቤቶች ማስተማራቸው፣ ግራ በሚያጋባ መንገድ የግል ትምህርት ቤቶች ቀዳሚ ቦታ ባገኙባቸው አንዳንድ የመንግሥት ሆስፒታሎች ተማሪዎቻቸው ለተግባር ልምምድ ቦታ የለንም መባላቸው በዚህ ረገድ ከሚጠቅሷቸው ችግሮች መካከል ናቸው፡፡ ‹‹በደቡብ አፍሪካ ስምንት የሕክምና ትምህርት ቤቶች ናቸው ያሉት፡፡ ሁሉም የመንግሥት ናቸው፡፡ በተቃራኒው በሱዳን 20 ሲሆኑ፣ ትርምስ ነው የመንግሥትም የግልም አለ›› በማለት ምሳሌ የሚሆኑ አገሮችን ተሞክሮ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

የአገሪቱን እውነታ ታሳቢ በማድረግ በሕክምና ትምህርት ትኩረት እየተደረገ ያለው ቁጥርም ጥራትም ላይ መሆኑን የገለጹት የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር አሚር፣ ከጥራት ጋር በተያያዘ ችግሮች መኖራቸው ግልፅ መሆኑን አምነዋል፡፡ ይህንን ታሳቢ በማድረግም በቀጣይ የተማሪዎች ቁጥር ከፍ እያለ እንዳይሄድ ማድረግን ጨምሮ ጥራትን የማረጋገጥ አሠራሮች ተግባራዊነት ላይ ጅምሮች መኖራቸውንና በሰፊው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል፡፡

በሕክምናው ዘርፍ የተማረ የሰው ኃይል ኩብለላ በመድረኩ እንደ ችግር የተነሳ ሌላው ጉዳይ ነበር፡፡ ከቀድሞ ጋር ሲነፃፀር የችግሩ መጠን በተወሰነ መልኩ መቀነሱን ብዙዎች ይስማማሉ፡፡

በአገሪቱ የሕክምና ትምህርት የቀደሙ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የዛሬዎቹ ተማሪና መምህራን ያለ ልዩነት የትምህርት ጥራት በቁጥር መጨመር እያሽቆለቆለ መሄዱን የዚህ አሉታዊ አንድምታም ለአገሪቱ የሕክምና ዘርፍ ከባድ እንደሚሆን ያስጠነቅቃሉ፡፡ ስለዚህም የችግሩ መጠነ ሰፊነት መንግሥት ጆሮ ሊሰጣቸው ግድ የሚልበት ጊዜ መሆኑን እንደሚመሰክር ይናገራሉ፡፡

 

 

 

____________________________________________________________________________________________