Ginbot 7 launches worldwide fund raising drive

Ginbot 7 Movement for Justice, Freedom and Democracy has launched a worldwide fund raising campaign today. In a statement released to the media, Ginbot 7 said that the fund will be used to carry out an all inclusive strategy that it has devised to remove the Woyanne tribal dictatorship in Ethiopia. Read the full statement below in Amharic:

በመላው አለም ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን የቀረበ የወገን ጥሪ

ከግንቦት 7 ለፍትህ ለነጻነትና ለዴሞክራሲ ንቅናቄ – (ታህሳስ 2 2001) ሃገራችን ስላለችበት ጭንቅና መከራ ህዝባችን ስለሚኖርበት የምድር ሲኦል፣ ብዙ ተብሏል። የወያኔ ኢህአዴግ መሪዎች፣ የመለስ ዜናዊንና የኩባንያውን ጸረ-ኢትዮጵያዊነት፣ በሃገርና በወገን ላይ የፈጸሙትን በደልና ግፍ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጠንቅቆ ያውቀዋል። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሚፈልገውና የሚመኘው ነገር ቢኖር በእዛች ደሃና መከረኛ ሃገራችን ላይ ሰላም ሰፍኖ፣ የህዝብ መብት ተጠብቆ የዜጎች አንድነትና የሀገርና ህልውና ተከብሮ፣ በአለም እያዋረደን ካለው የድህነት፣ ችጋርና የስደተኛነት መለያችን መገላጋል እንደሆነ እናውቃለን።

ይህ በጎ የህዝብ ምኞት እንዲሰምር ብዙ ኢትዮጵያውያን ህይወታቸው፣ ሃብት ንብረታቸውን፣ የተረጋጋ ኑሮዋቸውን፣ የቤተሰቦቻቸውን ደህንነት ገብረዋል። እስከ ዛሬ ድረስ ኢትዮጵያን ከተከመረባት ዘረኛና አምባገነናዊ ጸረ-ኢትዮጵያ ሃይል ለመገላገል ቆርጬ ተነስቻለሁ ለሚል ድርጅት የሃገራችን ዜጎች ያላበረከቱት ድጋፍ፣ ያልተመኙት በጎ ምኞት የለም። በተለያዩ ምክንያቶች ድርጅቶች ሲነሱ ሲወድቁ፣ ገበናቸው ሲጋለጥ፣ እንኳን ህዝብና ሃገርን የሚያክሉ ታላላቅ ነገሮች ነጻ የሚያደርግ ትግል እንቅስቃሴ ማደራጀት ቀርቶ እርስ በርሳቸው ተስማምተው መሄድ የማይችሉ ስብስቦች መሆናቸው ሲታይ፣ የህዝብ ስሜት በሃዘን ሬት ሲበከል አይተናል። አደራና ቃል የማያከብሩ፣ ለኢትዮጵያ ትንሳኤና ለህዝቧ የመከራ ቀን ማሳጠሪያ፣ ህዝብ ተቸግሮ በአመኔታ የሰጣቸውን ጥሪት ቀኑ መሽቶ የሚበላ የማይገኝ እንደሚመስለው ጅብ ተስገብግበው ውጠው፣ ያለምንም ሃፍረት አይናቸውን እያጉረጠረጡ በህዝብ ውስጥ ሲሹለኮሉ በማየት አንጀቱ የበገነው ብዙ እንደሆነ እናውቃለን።

የሃገር ጉዳይ ሆነና አንዱ ድርጅት ሲከዳ፣ ቃሉን ማክበር ሲያቅተው፣ በሌላው አዲስ ቃል ኪዳን በሚገባ፣ በሌላ ጥሩ ተናጋሪና ጥሩ ጸሃፊ ባለው ድርጅት እየተተካ፣ አዲሱም እንደ አሮጌዎቹ ያንኑ የቆየ የክህደት ቡቱቶ ሲላበስ፣ በህዝብ እምነትና በድርጅቶች ከህደት መሃከል ያለው የአዙሪት ቀለበት ሳይሰበር እዚህ ደርሰናል። ህዝብ ተስፋ ከማድርግ ሌላ ምርጫ የሌለው ነውና፣ አንድ ቀን ምናልባት አንድ ቀን ምኞቴ ይሳካ ይሆናል በሚል ቀጥሏል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ራሱም ሆነ ሃገሩ ያሉበት አስቸጋሪና ፈተኛ ሁኔታ እንዲቀየር ይፈልጋል። ይህንን ለውጥ ግን በተናጠል ማድረግ እንደማይችል፣ ለውጡን የሚያደራጅና የሚመራ ድርጀት እንደሚያስፈልገው ይረዳል። የድርጅት ጉዳይ ደግሞ ደጋግሞ የህዝቡን ቀልብ የሚስበው ለእዚህ ነው። ድርጅት ለለውጥ አስፈላጊ በመሆኑ እንጂ ህዝብ እንደታዘባቸው የተለያዩ ድርጅቶች ማንነትና ድርጊት ቢሆን ኖሮ የድርጅት ጉዳይ ሲነሳ ጆሮዎቹን በጣቶቹ ደፍኖ አትድረሱብኝ ሊል ይችል እንደነበር እናውቃለን።

ይሁንና በእዚህ አስከፊ ክፉ ዘመን፣ ከረሃቡም ከችግሩም ከግድያውና ከእስራቱም በላይ፣ የኢትዮጵያችን ህልውና፣ የአገዛዙን ስልጣን በያዙ ጸረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች ለከፍተኛ አደጋ በተጋለጠበት ወቅት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ በፖለቲካ ድርጅቶችና በፖለቲካ ሰዎች ላይ ተስፋ መቁረጥ በኢትዮጵያ ላይ ተስፋ መቁረጥ አድርጎ ስለሚያየው ጣቶቹን ጆሮው ጫፍ ላይ አስቀመጠ እንጂ አልሰማም ብሎ አልጠቀጠቃቸውም። አሁንም፣ ፈራ ተባ እያለ ቢሆንም አዲስ ቃል ኪዳን ለሚገቡ፣ አዲስ ራእይና ቁርጠኛነት አለን ለሚሉ ድርጅቶች ጆሮውን ለማዋስ እድሉን ለመስጠት ከመሞከር አልቦዘነም። ይህም ሆኖ ግን በድርጅቶች መሪዎች ድክመት፣ መዝረክረክና ማንአለብኝነት የባከነው የህዝብ ህይወት፣ ሀብት፣ እውቀትና ጉልበት የተጎዳው ቀናና በጎ ስሜት በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ እናውቃለን። በእዚህ በኩል ለደረሰው ጉዳት የፖለቲካ ሰዎች ነን የምንል ሁሉ በቀጥታ ይሁን በተዘዋዋሪ ለተፈጸመው ጥፋት ተገቢ የሆነውን የየራሳችን የጥፋት ድርሻ መቀበል ይኖርብናል።

ይህንንም ብለን ግን ድርጅቶችንና የድርጅቶች መሪዎችን ብቻ ወቅሰን ጉዳዩን ብናልፈው ሰለአለንበት ችግር የተናገርነው ግማሽ ሃቅ ይሆናል። ህዝብም ቢሆን በተለይ አቅሙና ችሎታው ያለው ወገናችን የፖለቲካ ድርጅቶችን መረን በመልቀቅና መሪዎችን በማቅበጥ ለደረሰው ጥፋት የራሱን ሃላፊነት መቀበል የሚገባው መሆኑን ሳንጠቁም ማለፉ ግብዝ ያደርገናል። በስልጣን ላይ ያለው አስከፊ አገዛዝ የሚያዋርደን እኛ እስከፈቀድንለት ድረስ እንደሆነ ሁሉ የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች በህዝብ ላይ መቀለድ የሚችሉት ህዝብ እስከፈቀደላቸው ድረስ መሆኑን ልንስተው አይገባም። የፖለቲካ ድርጅቶች የህዝብን አደራ እንዳይበሉ፣ የህዝብ ቅስም እንዳይሰብሩ፣ በማንአለብኝነት ያሻቸውን እንዳይፈጽሙ ምን ያህሎቻችን ነን ከዳር ቆመን ከማውራት አልፈን በውስጣቸው ገብተን ልንቆጣጠራቸው በህዝብ ስሜት መቀለድ አትችሉም ያልናቸው? ስንቶቻችን ነን ሁሉንም የፖለቲካ ሰዎች በድፍን ካማማትና አይረቡም ከማለት አልፈን፣ ከግብዝነትና ከአድርባይነት በላይ ተሻግረን አጥፊዎቹን ፊት ለፊት ለመናገር ድፍረቱን የተላበስን? ስንቶቻችን ነን ሊደገፉ የማይገባቸውን ደርጅቶችና የፖለቲካ መሪዎች፣ ሃገራዊና ህዝባዊ ከሆነ ጉዳይ ምክንያት ውጭ በጭፍን በመደገፍ የጥፋት ስራ የሚሰሩበትን እድሜያቸውን እየቀጠልናቸው ያለነው? እያመንን ተከዳን ብቻ ሳይሆን ሁሉም ይህንን የእምነት ክህደት አዙሪት ለመስበር ምን ሰርቼአለሁ የሚል ጥያቄ ማነሳት ተገቢ እንጂ ነው እንላለን።

ግንቦት7 የተመሰረተው፣ በህዝብ ውስጥ የተጎዳ ስሜትና በአመክኖ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድርግ ለሚፈልጉ ሃይሎች ሁኔታው በጣም አስቸጋሪ መሆኑን እያወቀ ነው። በእኛም ውስጥ በህዝብ ውስጥ የሚነሳው ስሜት ተነስቶ ነበር። “ተሰባስበን ለመስራት ያደረግነው ሙከራ ከሽፏል። የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ መግባት፣ የፖለቲካ ድርጅት መስርቶ መንቀሳቀስ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው። ትርፉ ውሎ አድሮ በራስና በቤተሰብ ላይ መከራ ማብዛት ነው። እኛም ማህበራዊ ስነልቦናው ብዙ የባህል ችግሩ ለሰለጠነ ፖለቲካ ታላላቅ ፈተናዎች እያመጣ የሚደነቅርበት ህብረተሰብ አካል በመሆናችን እኛም እንዳለፉት ድርጅቶች ድንገት ልናሳየው በምንችለው ድክመት ህዝብን ልናስቀይም እንችል ይሆናል” ብለን በመተከዝ አሰላስለናል። ይሁንና እኛም እንደ ኢትዮጵያ ህዝብ ተሰፋ እንዳንቆርጥ ያደረገን፣ “አባት የሞተ እንደሁ በሃገር ይለቀሳል ሃገር የሞተ እንደሁ ወዴት ይደረሳል” በማለት እጅግ አሽቸጋሪ ፈተናዎች አልፈውና መስዋእትነት ከፍለው ይችን ውድና ክቡር ሃገር ለኛ ያስተላለፉ ቀደምቶቻችን ጩኸት ከየወደቁበት ፈፋና ፈረፈር፣ በረሀና ጫካ፣ ተራራና ሸለቆ፣ ዱርና ገደል እያሰገመገመ ስለሰማነው ነው። ሀገርን የሚያክል ነገር፣ በተለይ ኢትዮጵያን የሚክል፣ ዙሪያችን እንደምናያቸው ሃገሮች ማንም ጠፍጦ ያልሰራትን ሃገር፤ ትውልድ በደሙ ዋዥቶ ያቆያትን ምድር፤ መለስ ዜናዊን ለመሰለ በጸረ- ኢትዮጵያነት በቀል ለሚንቀሳቀስ ከሃዲ አስረክበን መቀመጥ የማይቻል የማይታሰብ ስለሆነብን ነው።

ትግሉ ሃገርን የማዳን ብቻ ሳይሆን እራስንም፣ ልጆቻችንና ቤተሰቦቻችንም ነጻ ለማውጣት የሚደረግ መሆኑን እያወቅን፣ በተለይ እኛ ግንቦት 7ን የመሰረትነው አባላት ሌላ ነጻ አውጪ ጠባቂዎች ሆነን ብንገኝ አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን በሞራል ወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑን በማወቃችን ነው፤ እኛም ምርጫችንን በትግሉ መቀጠል ብቻ ያደረግነው። ይህ በመሆኑ ነው፣ ስለወያኔ/ኢህአዴግ ማንነት ያለን እውቀት፣ ወያኔን/ኢህአዴግን ለመታግል ከሚያስችለው ህዝብን በስፋት ለማንቀሳቀስ ካለን ተመክሮዋችን፣ ማሰባሰብ ከምንችለው በዘመናዊነትና በእውቀት የታጠቀ የሰው ሃይል፣ በጥናትና ምርምር በተደገፈ የትግል አቅጣጫና መገንባት በምንችለው የደርጅት አቅም፣ መንድፍ በምንችለው የተጋድሎ ታክቲክና ስትራተጂ፣ ሁላችንምና ሀገራችን አዋርዶ ለመግዛት የሚፈልገውን እብሪተኛ አገዛዝ ለማስወገድ ባላን እልህ፣ በተለይ ከነበርንበት ድርጅትና ከሌሎችም ድርጅቶች ጥፋቶች በሚገባ ከቀሰምነው ትምህርት ተነስተን፣ የህዝብን ስሜት ማደስ፣ ምኞቱን ማስፈጸም የሚችል ንቅናቄ ማቆም፣ ሁሉንም የሃገሪቱን ዜጎች በነጻነትና በእኩልነት የሚያስተናግድ አንድነታቸውን ለማስጠበቅ አልሞ የተነሳውን ራእያችንን ማስፈጸም አያቅተንም ብለን ነው፤ የግንቦት 7ን ለፍትህ ለነጻነትና ለዴሞክራሲ ንቅናቄን ያቆምነው።

በሩቁና በቅርቡ በሆነው ተከፍቶ፣ በሃገሩ ላይ ተስፋ እንደማይቆርጠው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ እኛም ምንም አይነት ፈተና ቢገጥመን በሃገራችን ላይ ተስፋ አንቆርጥምና ከወደቅንበት ቆሻሻ ስፍራ አብሮን የተነሳውን ትቢያ አራግፈን በድፍረት ቆመናል።

ብዛታችንን፣ የትግላችን ፍትሃዊነትና የአላማችን ርቱእነት፣ ድል አድራጊነታችን አስቀድሞ የተነበየው ነውና እንደ ቀደምቶቻችን ሃገራችንን በመታደግ ለልጅ ልጆቻችን፣ ለቤተሰቦቻችንና ለትውልድ የሚተላለፍ አኩሪ ታሪክ በጋራ እንስራ እንላችኋለን።

ግንቦት 7 ንቅናቄ ላቀደው ሁለ-ገብ ትግል ማካሄጃ የሚሆን አለምአቀፍ የገንዘብ ማሰባበስብ ስራ ጀምሯል። በየሃገሩ የንቅናቄያችን አላማ የሚደግፉ ግለሰቦች፣ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በግል እንዲያነጋግሩና ንቅናቄው ከማእከል በጥንቃቄ ባዘጋጀው ሰነድ አማካይነት ገንዘብ እንዲያሰባስቡ አሰማርቷል። ለነጻነት ለሀገር ህልውና የሚደረግ ተጋድሎ በቂ የገንዝብ አቅም ሳይኖረው የትም እንደማይደርስ አውቀው የተቻለዎትን በሙሉ በመለገስ ይተባበሩ። ሌሎችም በአካባቢዎ የሚገኙ ሃገር ወዳድ ወገኖቻችንም ለእዚህ የተከበረ አላማ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ያስተባብሩ።

የኢትዮጵያ ጠላቶች ሃገራችንን ለማፍረስ ላቀዱት እኩይ አላማ ካሰባሰቡት ጉልበት እውቀትና ሀብት በላይ እጅግ የላቀ ጉልበት እውቀትና ሃብት እኛ ለሃገራችን ህልውና የምንቆረቆር ዜጎቿ በማሰባሰብ ሴራቸውን ለማክሸፍ ቆርጠን እንደምንታገላቸው፣ ታግለንም እንደ ቀደምቶቻችን እንደምናሸንፋቸው ይወቁት።

ግንቦት 7 ለፍትህ ለነጻነትና ለዴሞክራሲ ንቅናቄ
www.ginbot7.org