Archive for the ‘ethiopia reporter’ Category

ዋኤል ጎኒም ኢትዮጵያዊ ቢሆን ኖሮ…?

Friday, January 11th, 2013

-->ዋኤል ጎኔም የግብጽ ደኅንነት ሰዎች ደብድበው የገደሉትን ካሊድ ሰኢድ ለማሰብ ‹‹እኔም ካሌድ ሰኢድ ነኝ›› የተሰኘ የፌስቡክ ገጽ ከፍቶ ለግብጽ አብዮት ያበቃ ሰው ነው፡፡ የመጀመሪያውን የአደባባይ እንውጣ ጥሪ ያቀረበው ይኸው የፌስቡክ ገጽ ነው፡፡ ዋኤል አደባባይ የወጡበትን የመጀመሪያ ቀን (ጃንዋሪ 25) አንድ ዓመት ለማክበር (Revolution 2.0 የተባለ) መጽሐፍ አሳትሟል፡፡ የመጽሐፉ ገቢ በሙሉ በአብዮቱ ለተጎዱ ሰዎች መደጎሚያ እንደሚውልም ተነግሯል፡፡ አሁን እዚህ ልጽፍላችሁ ያሰብኩት ግን ዋኤል ገጹን እና የግል ማንነቱን አስመልክቶ ለሚቀርብለት ጥያቄ ይሰጥ የነበረውን መልስ ነው (መጽሐፉ ላይ እንዳሰፈረው)፤ ዋኤል ኢትዮጵያዊ ቢሆንና የከፈተው ገጽም ኢትዮጵያዊ ቢሆን ኖሮ… በሚል ምናባዊ ምሳሌ፡፡ ስለዚህ ጽሑፉ በዋኤል የተጻፈው በኢትዮጵያኛ ተተርጉሞ ነው ልትሉት ትችላላችሁ፡፡

ስምህ ማነው?
[1]ስሜ ሽብሬ ደሳለኝ ነው፤
[2]ስሜ ዩሱፍ አብደላ ነው፤
[3]ስሜ እስክንድር ነጋ ነው፤
[4]ስሜ ርዕዮት አለሙ ነው፤
[5]ስሜ አሕመዲን ጀበል ነው፤
[6]ስሜ አንዱአለም አራጌ ነው፤
[7]ስሜ በቀለ ገርባ ነው፤
[8]ስሜ ኦልባና ሌሊሳ ነው፤
[9]ስሜ መስፍን ነጋሽ ነው፤
[10]ስሜ አርጋው አሽኔ ነው፤
ስሜ…. ብዙ ነው፡፡
እኔ በጎዳና ላይ የተገደልኩ፣ ያለወንጀሌ የታሰርኩ፣ ያለሀጢያቴ የተገረፍኩ፣ መብቴን በፍርሐት የተነጠቅኩ፣ ከገዛ አገሬ የተሰደድኩ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡
ዕድሜህ ስንት ነው?
ዕድሜዬ ይህን ያህል ነው አልልም፤ ነገር ግን ከተወለድኩ ጀምሮ ያለው ያው አምባገነን መሪ ነው፤… ሙስናውም ያው ነው፤…. ጭቆናው ያው ነው፤… እናም በአገሬ የገነነው የፖለቲካ ፓርቲ ‹‹ተስፋ የለም›› ይባላል፡፡
ከጠቀስካቸው ሰዎች ጋር ዝምድና አለህ?
እነዚህ ሰዎች የተኛውን ውስጤን ቀስቅሰውታል… ዕድሜ ለነርሱ አሁን ለውጥ ማምጣት እንደምችል ይሰማኛል፤… ታዲያ በራዕይ አልተዛመድንም ማለት ይቻላል?... አንድም ቀን አግኝቻቸው የማላውቃቸው እነዚህ ሰዎች ወንድሞቼ/እህቶቼ ናቸው፡፡
ይህንን የምታደርገው ለምንድን ነው?
ወገኖቼ ላይ የሚደርሰውን በደል ተመልክቼ ወደጥናት ክፍሌ ስገባ እምባዬን መግታት አልችልም፤… ፍርሐት የተጫናቸው ኢትዮጵያውያን ምን ያህል ውርደትን እንደሚታገሱ አየሁ… ከራሴ በመጀመር በፍርሐት የምሠራውን ስህተት ሁሉ ማረም ጀመርኩ፤ እናም ለዛ ነው ይህንን ገጽ የፈጠርኩት፡፡ ለተበደሉ ወገኖቼ ያለቀስኩት ለሞቱ ዘመዶቼ ካለቀስኩት በላይ ነው… በየዕለቱ ፎቷቸውን ስመለከት ድብታ ውስጥ እገባለሁ፤ ኢ-ፍትሐዊነትን እስከመጨረሻው ለመዋጋትም ለራሴ ቃል እገባለሁ፡፡
ማነው በገንዘብ የሚረዳህ?
ፈጣሪ ይመስገን፣ የገንዘብ ምንጮቼ ብዙ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ንቃተ ሕሊናዬ ነው… ይህ ምንጬ በቀን አራት ሰዓተ ብቻ እንድተኛ እና ጠዋትም ፊቴን ከመታጠቤ በፊት የፌስቡክ ገጼን እንድከፍት ያስገድደኛል፡፡

ሁለተኛው ምንጬ መማሬ ነው፡፡ በመማሬ ደስተኛ ነኝ፤ ዕውቀቴን አገሬን ለማገልገል አውለዋለሁ፡፡
ሦስተኛው ምንጬ የልጆች አባት መሆኔ ነው፡፡ ሁሌም የሚጨንቀኝ ልጆቼ አንድ ቀን ‹‹አባዬ፤ ዜጎች ሲጨቆኑ እያየህ አቅምህ የሚፈቅደውን ለምን አላደረግክም?›› ብለው ይጠይቁኛል ብዬ ነው፡፡
የመጨረሻው ምንጬ የሕዝብ ፍቅር ነው፡፡ አይቶኝ የማያውቅ፤ አይቼው የማላውቀው እና በስም የማንተዋወቀው ሕዝብ ፍቅር… በየዕለቱ የአመሰግናለሁ ማስታወሻ ይደርሰኛል…. የተለያዩ ዲዛይኖች፣ ሎጎዎች፣ ቪዲዮዎች ይልኩልኛል… ገጹ ብዙ ሰዎች ጋር እንዲደርስ ያስተዋውቁልኛል፡፡
ስለዚህ ምንድን ነው የምትፈልገው?
ይህንን ገጽ የፈጠርኩት ራሴን ከአደጋ ለመጠበቅ ብቻ አይደለም.. ነገር ግን አገራችን መልሳ የኛው የሕዝቦቿ እንድትሆን ከመፈለግ በላይ ሌላ ዓላማ የለኝም… አንድ ቀን እንዲህ ይሆናል ብዬ አልማለሁ፡- እርስ በእርስ ዳግም እንዋደዳለን፤ ሁላችንም ኢ-ፍትሐዊነትን እንቃወማለን፤ ከመሐከላችን ማንኛውም ሰው ክፉ ነገር ቢያይ ራሱ ይፈታዋል… እናም የመንግሥት ቅጥረኛ አንድን ዜጋ በጥፊ ከመምታቱ በፊት አንድ ሺሕ ጊዜ ያስብበታል፡፡
አትፈራም?
በጣም እፈራለሁ እንጂ፤… ፍርሐት እኮ የሰው ልጅ ተፈጥሮ ነው… ለተጨቆኑ ዜጎች የሚቆረቆር እንደእኔ እና እናንተ ያለ ሰው ግን ካለ ፍርሐቴ ይከስማል… ዕጣፈንታችንንም የምንወስነው እኛው ራሳችን እንሆናለን… እንዲህ እያልን፡- ‹‹ማንም ያለዕድሜው አይሞትም፣ ማንም ያለወንጀሉ አይታሰርም፣ ማንም አገሩን ለቅቆ አይሰደድም…›› አንድ ዘመዴ በ25 ዓመቱ ሞተ… ቁም ነገር ካልሠራሁበት የኔ ዕድሜ መርዘሙስ ምን ዋጋ አለው?
ብዙ ሰዎች ይህንን ለማመን ይቸገራሉ፤ እውነቱን ለመናገር ቃሉ የወጣው ከልቤ ነው… አገሬን ከልቤ እወዳታለሁ እናም በተሻለ ሁኔታ የምንኖርባት አገር እንድትሆን እፈልጋለሁ፡፡ መፈንቅለ መንግሥት ወይም አብዮት የማቀጣጠል ዓላማ የለኝም… እራሴን እንደፖለቲካዊ መሪም አልቆጥርም… ዋሊያዎችን እና ሉሲዎችን የሚደግፍ፣ ካፌ ደጃፍ ላይ ቁጭ ብሎ ተቆራጭ እየበላ፣ ማኪያቶ እየጠጣ ጋዜጣ የሚያነብ ተራ ዜጋ ነኝ፡፡… የሚከፋኝ ብሔራዊ ቡድናችን በሰው አገር ሲሸነፍ ነው፡፡ … ቁምነገሩ በኢትዮጵያዊነቴ መኩራት እፈልጋለሁ፡፡… ማንም ሰው የዜግነት ክብሩን ተገፍፎ እንዲጨቆን አልፈልግም፡፡ ይኸው ነው ምኞቴ፡፡
----
[1] - ሽብሬ ደሳለኝ፤ ምርጫ 97ን ተከትሎ በተነሳው ብጥብጥ የመንግሥት ጥይት ሰለባ የሆነች ወጣት ተማሪ፤ [1] - ዩሱፍ አብደላ፤ በተመሳሳይ ወቅት የተገደለ የኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ተማሪ፤
[3] - እስክንድር ነጋ፤ በሽብርተኝነት ተከሶ የተፈረደበት ጋዜጠኛ፤
[4] - ርዕዮ ዓለሙ፤ መረጃ ለሽብርተኞች አቀብለሻል በሚል የተፈረደባት ጋዜጠኛ፤
[5] - አሕመዲን ጀበል፤ በሙስሊሞች የመጅሊስ ይቀየር ጉዳይ የታሰረ፣ ጋዜጠኛ እና ደራሲ፤
[6] - አንዱአለም አራጌ፤ ሽብር አሲረሃል በሚል የተፈረደበት የአንድነት ፓርቲ አባል፤
[7] - በቀለ ገርባ፤ ከኦነግ ጋር ግንኙነት አለህ በሚል የተፈረደበት የኦፌዴን ም/ሊቀመንበር፤
[8] - ኦልባና ሌሊሳ፤ ከኦነግ ጋር ግንኙነት አለህ በሚል 8 ዓመት የተፈረደበት የኦብኮ አባል፤
[9] - መስፍን ነጋሽ፤ በሽብርተኝነት አዋጅ/ክስ ምክንያት ከተሰደዱ የቀድሞዋ አዲስ ነገር ጋዜጠኞች አንዱ፤
[10] - አርጋው አሽኔ፤ የመረጃ ምንጩን እንዲሰጥ በመንግሥት ኃይሎች በግዴታ በመጠየቁ የተሰደደ ጋዜጠኛ፤

የርዕዮት ዓለሙ ክስና የጠበቃዋ ተቃዉሞ

Wednesday, January 9th, 2013

ርዕዮት ዓለሙ ከዚሕ ቀደም የበታች ፍርድ ቤት አስራ-አራት ዓመት እስራትና የገንዘብ መቀጮ በይኖባት ነበር።ይግማኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ግን ቅጣቱን ወደ አምስት-ዓመታት እስራት ዝቅ አድርጎታል።ርዕዮት ዓለሙ ለሰበር ሰሚዉ ችሎት አቤት ያለችዉ የአምስት ዓመቱ እስራትም የሕግ አተረጓገም ክፍተት አለበት በሚል ነበር

የጋዜጣ አምደኛ ርዕዮት ዓለሙ በአሸባሪነት ወንጀል የተበየነባት ቅጣት እንዲሠረዝ ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሠበር ሰሚ ችሎት ያቀረበችዉን አቤቱታ ችሎቱ ዉቅድቅ አደረገዉ።ርዕዮት ዓለሙ ከዚሕ ቀደም የበታች ፍርድ ቤት አስራ-አራት ዓመት እስራትና የገንዘብ መቀጮ በይኖባት ነበር።ይግማኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ግን ቅጣቱን ወደ አምስት-ዓመታት እስራት ዝቅ አድርጎታል።ርዕዮት ዓለሙ ለሰበር ሰሚዉ ችሎት አቤት ያለችዉ የአምስት ዓመቱ እስራትም የሕግ አተረጓገም ክፍተት አለበት በሚል ነበር።ትናንት አዲስ አበባ ያስቻለዉ ሰበር ሰሚ ፍርድ ቤት ግን አቤቱታን ዉድቅ አድርጎታል።የርዕዮት ጠበቃ የችሎቱን ዉሳኔ አልተቀበለቱም።ዩሐንስ ገብረ እግዚ አብሔር ዝር ዝር ዘገባ ልኮልናል።

የርዕዮት ዓለሙ ይግባኝ ውድቅ መደረጉን ዓለምአቀፍ ድርጅቶች አወገዙ

Tuesday, January 8th, 2013

VOA – በጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ ላይ የበታች ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ማፅናቱ ያሣዘናቸው መሆኑን ዓለምአቀፉ የሴቶች የመገናኛ ብዙኃን ድርጅት – IWMF እና ዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች ደኅንነት ተሟጋች ድርጅት CPJ አስታውቀዋል፡፡

IWMF መግለጫውን በይፋ አውጥቶ ያሠራጨ ሲሆን የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ኤሊሣ ሊዝ ሙኞዝ ለቪኦኤ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሃሣብን የመግለፅ ነፃነት ጉዳይ ድርጅታቸውን በእጅጉ የሚያሠጋው መሆኑን አመልክተዋል፡፡

“ርዕዮት ለጋዜጠኝነት ነፃነት ያላትን ድፍረት፣ ቁርጠኝነትና ጥንካሬ እናደንቃለን፡፡ ቀደም ፀሰል የተላለፈባት ፍርድ በመፅናቱ ማዘናችንን እንገልፃለን፡፡ ይህ ለእርሷ ሕይወት ብቻ ሣይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ሃሣብን በነፃነት ለመግለፅ ነፃነትም ጭምር አሣዛኝ ቀን ነው፡፡ ለሌሎች በእሥር ላይ ለሚገኙ ጋዜጠኞችም የሚሰማንን መቆርቆር እንገልፃለን” ብለዋል ዳይሬክተሯ፡፡

ዓለምአቀፉ የሴቶች የመገናኛ ብዙኃን ባወጣው ይፋ መግለጫው ኢትዮጵያ ውስጥ እሥር ቤት ውስጥ ባሉ ጋዜጠኞች ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ፣ በፕሬስ ነፃነት አያያዟ በዓለም እጅግ ጨቋኝ ከሚባሉ ሃገሮች ተርታ መመደቧን አስታውሶ ባለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ዘመን በአፍሪካ ውስጥ ከኤርትራ በስተቀር ሌላ ማንም ሃገር በማይስተካከለው ሁኔታ ጋዜጠኞችን ማሠሩን አመልክቷል፡፡

“የሚወቅሱትን ድምፆች ለማፈን በአደናጋሪው የኢትዮጵያ ፀረ-ሽብር ሕግ መንግሥቱ በተደጋጋሚ መጠቀሙ እጅግ አሣሣቢ ነው” ያለው ይኸው መግለጫ ርዕዮት በሰኔ 2003 ዓ.ም (በኢትዮጵያ አቆጣጠር) ከተያዘች ወዲህ ለብዙ ወራት ያለ ክሥ መታሠሯን እና በኋላም ተግባሯ ሙሉ በሙሉ የጋዜጠኛ ሥራ ሆኖ ሣለ በሽብር ፈጠራ መከሰሷን ዘርዝሯል፡፡

“ባለፈው ነሐሴ በከፊል በተሣካው ይግባኝ በርዕዮት ላይ ቀድሞ የተላለፈው የ14 ዓመት እሥራት ፍርድ ወደ አምስት ዓመት እንዲቀንስ ቢደረግም እስከአሁን የቆየችባቸው 19 ወራት እያንዳንዷ ቀን ወይም ወደፊት በእሥር የምትቆይባቸው 41 ወራት እያንዳንዷ ቀን የኢትዮጵያ መንግሥት የፕሬስ ነፃነትን ዋጋ እንዳረዳ የምትጎተጉት ማስተወሻ ነች” ብሏል መግለጫው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች ደኅንነት ተሟጋች ድርጅት ሲፒጄ ውሣኔውን እንደሚቃወምና እንደሚያወግዝ የአፍሪካ የአድቮኬሲ አስተባባሪ መሐመድ ኬይታ አስታውቋል፡፡

“ያሣዝናል – አለ ኬይታ – ኢትዮጵያ ውስጥ ለሕግ የበላይነት መከበር ቀኑ የኀዘን ቀን ነው፡፡ ምክንያቱም በርዕዮት ዓለሙ ላይ የተመሠረተቱት የሽብር ፈጠራ ክሦች በማስረጃ ለማስደገፍ የቀረቡት ፍፁም አስቂኝ ናቸው፡፡ እነዚህን ክሦች ፈትሸናቸዋል፡፡ የተከሠሠችው በጋዜጠኝነት ላከናወነቻቸው ሥራዎች ነው፡፡ እነዚህ ተቀባይነት ያላቸውና ሕጋዊም መረጃን የመሰብሰብና የማሠራጨት ሥራዎቿ መንግሥትን የሚወቅሱ ናቸው፣ የተቃዋሚ ቡድኖችን እንቅስቃሴ በተመለከተም ዘግባለች፡፡ ይህ መንግሥቱን የሚተቹ የግርግዳ ላይ ፅሁፍ ሣይቀር እንደማስረጃ የቀረበበት ክስ አስገራሚ ነው፡፡” ብሎታል፡፡

በክሦቹ ላይ የተጠቀሱት ጭብጦች በማንም ነፃ ወገን እንደሽብር ፈጠራ አድራጎት ማረጋገጫ አለማግኘታቸውን ወይም አለመደገፋቸውን የሲፒጄው አስተባባሪ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የታየው “የፍትሕ መጨናገፍ ነው” ብሎታል፡፡

ሃገሪቱ ለሽብር ፈጠራ አድራጎት የተጋለጠች መሆኗንና መንግሥቷም የበረታ የሽብር ፈጠራ እንቅስቃሴዎች ሥጋት እንዳለበት ሲፒጄ እንደሚገነዘብ ሞሐመድ ኬይታ አመልክቶ “የጋዜጠኝነት ሥራቸውን በሚያከናውኑ ባለሙያዎች ላይ የሽብር ፈጠራ ክሥ እየመሠረተ ሽብር ፈጠራን ከእውነተኛው መገለጫው እያሣሣተና ክብደቱንም እያቀለለው ነው” ብሏል፡፡

“በዚህ አድራጎቱ ርዕዮትና ባልደረቦቿ ዓለምአቀፍ ዕውቅና እንዲያገኙ እያደረገና የመናገር ነፃነትን ለማፈን እያደረገ ያለውን ተግባር እያጋለጠ ዋጋውን እራሱ ይከፍላል” ብሏል የሲፒጄው የአፍሪካ አድቮኬሲ አስተባባሪ ሞሐመድ ኬይታ፡፡

ርዕዮት ዓለሙ የዓለምአቀፉ የሴቶች ሚድያ ድርጅት የ2012 ዓ.ም በጋዜጠኝነት ላሣየችው ድፍረት እና የዚሁ የ2012 ዓ.ም የሄልማን/ሃሜት ሽልማቶች ተሸላሚ መሆኗ ይታወቃል፡፡

ሃይማኖት የግል ሃገር የጋራ ነው

Monday, December 17th, 2012

ይህን ኣባባል ስንቀባበል የኖርነው ያለ ምክንያት ኣልነበረም። ሃገራችን ብዙህነቷ የሚገለጸው በ ቋንቋና በ ባህል ብቻ ሳይሆን በ ሃይማኖትም በመሆኑ ነው። ብሂሉ ተቻችለን መኖር እንዳለብን ቃል የምንገባበት፣ የሃይማኖት ነጻነታችን የ ግል ሆኖ ኣገራችን ግን የሁላችን መሆኑዋን የምናጸናበት ኪዳን፣ የ ኣንድነት ጉዟችን ደሞ ስንቅ ነበር።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህን ትልቅ ኣላማ የሚያናጋ ሁኔታ ሲፈጠር ይታያል። የሚያሳዝነው በሃገራችን ከተነሱ ሃይማኖታዊ ግጭቶች መካከል እጅግ ብዙዎቹ ፖለቲካዊ ይዘቶች ያሉዋቸው መሆኑ ነዉ ።

በመሰረቱ ፖለቲካና ሃይማኖት የሚጣሉ ባይሆኑም ኣላማቸው ግን ኣይገናኝም። ሃይማኖታዊ ተቋማት ከዚህ ኣለም ባሻገር ሌላ ኣለም ኣለ ወደዚያ ሄጄ ዘላለም እኖራለሁ የሚል ዋና ግብ ያነገቡ ሲሆን ፖለቲካ የዚህ ኣለም ጣጣ በመሆኑ ለየብቻ መሄድ ኣለባቸው።

ከሁሉ በላይ ግን መንግስት ከሃይማኖት ጣልቃ ገብነት መቆጠቡ የሚጠቅመው ራሱን ነው።የ ሃይማኖት ተቋማት በ ህብረተሰብ ህይወት ውስጥ ካላቸው የጎላ ጠቀሜታ መካከል ኣንዱ የፍትህ ስርዓቱን በመደገፉ ረገድ ያላቸው የጎላ ሚና ነው። ለምሳሌ በሃገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ስናይ ኣንድ ሰው ለ ምስክርነት ወደ ፍርድ ቤት ሲሄድ በ መጀመሪያ እውነት ለ መመስከሩ ቃል የሚገባው ህገ መንግስቱ ላይ እጁን ጭኖ ሳይሆን ክርስቲያን ከሆነ መጽሃፍ ቅዱስ ላይ ሙስሊም ከሆነ በቁራን ላይ ነው። ይህ የሚያሳየው ፍርድ ቤት ወይም የፍትህ ስርዓቱ ከ ሃይማኖት ጣልቃ ገብነት ነጻ ቢሆንም ግን በነዚህ ተቋማት ላይ መደገፉን ነው።

እነዚህ የ ሃይማኖት ተቋማት ኣባሎቻቸውን የሚያስተምሯቸው እሴቶች ለምሳሌ፣ ኣትግደል፣ በሃሰት ኣትመስክር፣ ኣታዳላ፣ ግፍ ኣትስራ፣ ወዘተ. የፍትህ ስርዓቱ ምሶሶዎች ናቸው። እነዚህን እሴቶች መንግስት በሌላ መንገድ ከሚያስተምረው የበለጠ በሃይማኖት ተቋማት በኩል ፍሬ ሲያፈሩ የበለጠ ሃይል ይኖራቸዋልና መንግስት የሃይማኖትን ተቋማት በ ኣክብሮትና በ እንክብካቤ ሊይዛቸው ይገባል።

መንግስት በሃይማኖት ኣስተዳደር ኣካባቢ እጁን ሲያጠልቅ ኣባላት መንፈሳዊ ሽታ እየራቃቸው ይሄዳሉ። ይሰጋሉ። በተቋማቸው ያላቸው መተማመን እየቀነሰ ሲመጣ ደሞ ዞሮ ዞሮ የሚጎዱት ተቋማቱ ብቻ ሳይሆኑ የፍትህ ስርዓቱም ነው።

ዜጎች ምንም ሃይማኖት ባይኖራቸው የሚኖራቸው የህሊና ህግ ያን ያህል ጠንካራ ላይሆን ይችላል። ምንም ሃይማኖት ከሌለ ምን ኣልባትም ገንዘብ ካለህ ሃምሳ የ ሃሰት ምስክር ለመሰብሰብ ላይከብድ ይችላል። በማህበራዊ ግንኙነት ጊዜ ተማምሎ የጋራ ስራ ለመስራት ኣስቸጋሪ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ይህ ማለት ግን ሃይማኖት የሌለው ሁሉ ኣይታመንም ማለት ኣይደለም። ኣሉ ኣንዳንድ ዳኞች ለ ሙያቸው የሚሞቱ ኣሉ ኣንዳንድ ፖለቲከኞች ለ ኣላማቸው የሚሞቱ፣ ይሁን እንጂ በሰፊው እንዳገር እንደ ህዝብ ስናስበው ሃይማኖት ጠቃሚ ሃገርን እንደ መልህቅ የሚያቆም ትልቅ የተከበረ ተቋም ነው።

ለነገሩ በሃገራችን መንግስት በ ሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ መግባት የጀመረው በ ደርግ ጊዜ ነበር። ደርጉ የ ሶሻሊዝምን ስርዓት እንገነባለን ብሎ ባበደበት ሰኣት “ጎታች” ብሎ ከፈረጃቸው ተቋማት መካከል ኣንዱ ነበሩ። ዝግ እያለ ገብቶ ቄሱን ሁሉ የጾም እንዲበሉ በማድረግ የ ኦርቶዶክስን ቤተ ክርስቲያን እምነት ሊያስጥል ሞክሯል፤ ጎድቷታልም። የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮችን በፊት ለፊት ሲገድልና ሲያስር እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

ኢህኣዴግ ሲመጣ የተሻለ ነገር ይመጣል ተብሎ ተገምቶ ነበር። በተለይ መንገላታት ያደከመው የፕሮቴስታንቱ ኣማኝ ኣንጻራዊ ነጻነት ያገኛል ተብሎ የታሰበ ቢሆንም ራሳቸው የኢህኣዴግ ካድሬዎች በፈጠሩት ቀውስ በተለይ በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል ብዙ የፕሮቴስታንት ና የ ኦርቶዶክስ ሰዎች ተጋጭተው ብዙ ብዙ ጉዳት ደርሷል።

ኣሁን ደሞ የዜጎችን ቀልብ በመልካም ስራ መሳብ ያቃተው መንግስት ዜጎች ልባቸውን የጣሉበትን ባህላዊና ሃይማኖታዊ ተቋማት እያሸተተ ዜጎችን ሊቆጣጠር ይፈልጋል። በተለይ በቅርብ ጊዜ የሚታየው የከፋ ነገር ደሞ በ ኢትዮጵያ ሙሲሞች ዘንድ መንግስት የሚያሳየው ኣስጸያፊ ጣልቃ ገብነት ነው። ይህ ችግር ብዙ መዘዞችን ለሃገራችን ያመጣል ተብሎ የሚታሰብ ሲሆን ኣንዱና ትልቁ ችግር ኣክራሪነትን ይወልዳል የሚለው ስጋት ነው።

የሃይማኖት ሰዎች የሃይማኖት ነጻነት ጥያቄ ሲያነሱ ፖለቲከኞች ለፖለቲካ መብት ከሚታገሉት የከረረና የመረረ ነው። ከሁሉም በላይ የሃይማኖት ደጃቸው ሲደፈር፣ ኣምላካቸው ሲያዝን ስለሚታያቸው ቁጣቸው ይበዛል። መስዋእትነት ለመክፈልም ቢሆን ለ ሃይማኖታቸው ለ ኣምላካቸው ቢሞቱ በሰማይ ብድራት ስላላቸው ኣይፈሩም።በመሆኑም በሃይማኖት በኩል የሚመጣ ቁጣ እንዲህ በቀላሉ ኣይበርድም። ከሁሉ የሚከፋው ግን በሃይማኖቱ ውስጥ ካሉ ኣባላት ውስጥ በጣም ኣጥባቂ ያልሆኑትን ወደ ሌላ ጽንፍ እየወረወራቸው እልህና ቁጣ ይሞሉና ኣክራሪ ኣሸባሪ ሊያደርጋቸው ይችላል። ጥያቄያቸው እየከረረ ሲሄድ ኣመጹ ራሱ ከሚፈጥራቸው ኣንዳንድ መሪዎች መካከል የሚነሳ ኣስተምህሮም ሊፈጠር ይችላል። ከሁሉም በላይ ሃይማኖታቸው ፖለቲካዊ ይዘት እንዲኖረው ማድረግ ይጀምሩና ኣክራሪነት እየተወለደ ሊመጣ ይችላል። ዛሬ በኣለማችን ያሉ ኣክራሪዎች የተወለዱት ከ መልካም ኣስተዳደር እጦት ከመብት ገፈፋ ጋር እየተያያዙ የመጡ ናቸውና፡፡

መንግስት ሊረዳው የሚገባው ነገር የ ሃይማኖት ጥያቄ የሚፈታው በፖለቲካዊ መንገድ ኣለመሆኑን ነው። ልክ የፖለቲካ መብት እንዳነሱ ኣይነት በቴለቪዥን “ህጉንና ህገ መንግስቱን ኣክብረው መኖር ኣለባቸው” የሚባል ፈሊጥ መልስ ኣይሆንም፡፡ ኣያስፈራቸውምም። የሃይማኖትን ችግር በሸምግልናና በትህትና በሃይማኖት ሰዎች በኩል መፍታት ያስፈልጋል። ኢህኣዴግ የ ሙስሊሙን ጤያቄ ሌሎች የ ህዝብ ኣመጾችን በሚያፍንበት የዘወትር መሳሪያው ሊያበርደው ኣለመቻሉን መረዳት ኣለብት።

እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!
geletawzeleke@gmail.com