አባ መላኩ ዘይገርም


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


አባ መላኩ ዘይገርም

“እስከመቼ በሁለት ሃሳብ ታነክሳላችሁ”

የዕውነትና የብርሃን ቤት የነበረችው የኢት/ኦር/ተዋ/ ቤ/ያን ዛሬ የቤተክርስቲያኒቷን አስተምህሮ በማያሟሉ እንኳን ለታላቋ ቤተክርስቲያን በግለሰብ ዓለማዊ ኑሮ አንኳን በማይመጥን ጥቅመኛ ጥቂት ግለሰቦች ስብስብ ስር ወድቃ ባለበት በዚህ አስከፊ የመከራ ዘመንና ጊዜ አደጋውን ለማምከን ከመሞከር ይልቅ በሕዝብ መገናኛ በቃለመጠይቅ ሰበብ የማይገባው ግለሰብ በማይገባው ቦታ እንዳለ እየታወቀና በጊዜው ከሃገር ውስጥ እስከ ፍልሰቱ ዓለም አባ መላኩ የሚነሱት ጥያቄዎች መልስ ሳያገኙ እንደ እንቧይ ካብ በተደረደረ የፈጠራ ዝና በማያንጽ የነውርና የሽንገላ ንግግር ቤተክርስቲያኒቷንና ምዕመኗን ግራ እያጋቡ ይገኛሉ። በመሆኑም፤

የዚህ ጽሁፍ ዋና መነሻ “ደጀሰላም” በሚባለው የጡመራ ድረገጽ ላይ እ.አ.አ. ጃንዋሪ 25/ 2012 የወጣው የሁለት ራዲዮ ጣቢያዎች ማለትም የአዲስ ድምጽ ራዲዮ ጋዜጠኛ አቶ አበበ በለውና የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ጋዘጠኛ አቶ አዲሱ አበበ ሲሆኑ እነኝህ ጋዜጠኞች ስለ አባ መላኩ ጌታነህ ባቀረቡት ዕይታ ማን እውነቱ ገሃድ እንዲወጣ እንዲደረግና ማን ሃቅ አንዲጨፈለቅ እንዳደረገ አድማጭ የራሱን ፍርድ እንዲሰጥ ለማስታወስና እኛ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢዎች የተመለከትነውንና የተገነዘብነውን ለህዝብ ለማሳወቅ ነው። በተለይ አንደኛው ጋዜጠኛ የህዝቡን የግንዛቤ አቅጣጫ በማሳት ጫካ ውስጥ ስለከተተው እውነት ያለው በመምከርና በመገሰጽ ሃቁን አስጨብጦ አቅጣጫን እንዲያሲዝ ይህ መልዕክት ወጥቷልና ደጀሰላምን በ ጃንዋሪ 25/ 2012 ያወጣውን ድረገጽ( ብሎግ) በማዳመጥ ፍርዳችሁን ትሰጡ ዘንድ ኽረ የሰው ያለህ! እያልን በተለይ ነገርመለኮቱን ተምራችሁ በቤተክስቲያን ያደጋችሁ ቀድማችሁ ፍቅርዋን የቀመሳችሁ እልፍ አዕላፋ ብትሆኑም በዓለም ዙሪያ በግል የኑሮ ውጣውረድ ተወጥራችሁ ራሳችሁን ሰውራችሁና ደብቃችሁ የትነው ያላችሁት? እንዳላችሁ የታወቀ ነው እባካችሁ ተዋህዶ ትጠራችኋለችና ውጡና በወጣትነት ዕድሜያችሁ የተሰጣችሁን የነገረመለኮት አደራ መስክሩ ተወጡ። በተለይ አለቃ (ቀሲስ) አስተርአየ ጽጌ፣ ዶ/ር መርአዊ ተበጀ፣ ሊቀመዘምራን አበባው ይግዛው፣ መጋቢ ምስጢር ወልደሩፋኤል ፈታሄና ሌሎችም መስክሩና ወደመቃብር ..ኽረ እግዚኦ ስለቤተክርስቲያን ተንቀሳቀሱ!! ለማንኛውም የመገናኛ ብዙሃን ማለትም  የድረገጾች፣ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን አገልግሎት ሰጭዎችም ጥሪው ይድረሳችሁ የእውነትን ቀስት ትስቡት ዘንድ።

በመጽሃፍ ቅዱስ ላይ ኢሳያስ 58፡ 6 “….. እኔ የመረጥኩት ጾም ይህ አይደለምን? የበደሉን እስራት ትፈቱ ዘንድ የቀንበሩንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ የተገፉትንስ አርነት ትሰዱ ዘንድ፣ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ አይደለምን?….” ይላል። ታዲያ ቀንበር ለሆኑብን ሙገሳው ምን ይሉታል? ወይንስ ዘመን የወለዳቸውን አስመሳዮች፣ ሆዳቸው አምላካቸው የሆነውን፣ የወንጌልን ቃል ከሚሸቃቅጡ እግዚያብሔር የለሾች በህዝባቸው በአማኙ ላይ ራሳቸው የመከራ፣የባርነት፣የፍትህ እጦት፣ቀንበር የሆኑትን፣ የተገፉትን የሚገፉ፣ የተሰደዱትን የሚያሳድዱ አሳዳጆች ማጅራታቸው ያበጥ ድልብ ቅልቦችን በቃለመጠይቅ ሰበብ ህጋዊነትና ተቀባይነት ለማስጠት መዳዳቱ የቀበሮ ባህታዊያንን በበጎች መካከል ነውና ልንታገለው ይገባልና ደጀ ሰላም በንጽጽር እውነትን እንድንይዝ የሚመሰገን ጥረት አድርጓልና ጥሩ ሲሰራ በርታ ማለት የህሊና ግዴታ ነው።

ምናልባትም ጊዜው ይጠር ወይንም ይርዘም እንጅ ወደፊት “በዓለማችን ነውረኛ የቤተክርስቲያን አባቶች በኢትዮጵያ” ተብሎ መመዝገቡ ላይቀር እውነቱን አንተላለፍ። ጊዜው በራሱ አብዶ ሳላ ተጨማሪ በመዘባረቅ ማበድን ምን ይሉታል? በተለይም ለቤተክርስቲያችን ትልቅ ውርደት፣የተቀደሰ መንበሯን በጠብ መዘባበቻ ያደረጉ የልጆቿን አንገት ያስደፉትን አሳፋሪዎች ድርጊት፣ በዚህም የኢትዮጵያን ውድቀት በጥቅማቸው የጠሩትን የሥጋ ሰዎች እኩይ ተግባር በሸፍጥ ለመሸፈን ከመሮጥ ይልቅ ወደራስ ተመልሶ እውነቱን መመስከር ይገባልና እውነተኛውን የጋዜጠኝነት የሙያ ኃላፊነት ረስታችሁ እውነቱን የሸፈናችሁ ለሃገራችን ለኢትዮጵያና ለቤተክርስቲያኒቷ ተጨማሪ ፈተናና አደጋ ነውና እባካችሁ ከወዲሁ ተመለሱ።

የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ልብ በሉ!! ጥቁሩን ጥቁር ነጩን ነጭ በሉ። ዛሬም ይሁን ወደፊት ለኢትዮጵያችን ውጤትም ሆነ ክስረት ድምጻችሁ ዋጋ አለውና ተጠንቀቁ! ተዋህዶም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ጋዜጠኞች እውቀት መሠረትና የማታልቅ ምንጭ ናትና መስክሩላት። ከእናንተም ይሁን ከሌላ ምንም አትሻምና ራሷ እውነት ስለሆነች ያንን ግለጡት። ተዋህዶ ነጻነት ነች። ክብር ነች። ፍትህ ነች። ሰላም ነች። ፍቅር ነች። በመናወጥ ጊዜ የማትወድቅ አርበኛ የሰው ዘር ድምጽ ነች። በጥቅሉ ራሷ ወንጌል ነች። ልብ ያለው ልብ ይበል። ማንም ይሁን ማን አዋቂ ነኝ የሚል ጠቢብ ቢገኝ ሁሉም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የኢት/ኦር/ተዋ/ ቤ/ያን የዘመናት የድካም ውጤትና ሀብት መሆናችንን ልንዘነጋው አይገባም።

“ዲያስፖራ” የሚለው ቃል እንደ ጥሩ ስም ስለደረብነው እኛ ደግሞ “ፍልሰት” እንላለን። ለእኛም ፈልሰን መኖር እስከመቼ  እንደሆነ ባናውቅም ይህ ፈልሰን የምንኖርበት አሜሪካም የቀደሙ አባቶቻቸው እየተጋዙ፣ እየተገረፉ አምርረው እየሞቱ እየተገፉ አልህ አስጨርሰው ውሸትን በመታገል መስዋዕት ሆነው ነው አሜሪካንን በመጽሃፍ ቅዱስ እውነት ላይ በመመስረታቸው ነውና፤ አስቀድማ በፈሪሃ እግዚያብሔርነት በመጽሃፍ ቅዱስ እውነት ላይ ለቆመችው ኢትዮጵያ ሀገራችንና ለተዋህዶ ግድ ሊለን ይገባል። ወደልባችን እንመለስ።ሳንዋሽ እውነቱን እንግለጠው። ሰው ምን ያደርገናል?

ከእግዚያብሔር ያልሆነ አባት ያልተከለው ይነቀላልና ከእግዚያብሔር ያልሆነ ጥበብና ማስተዋል የጎደላቸው በጋዜጠኝነት ስም ለአባ መላኩ የተሰጠው ሽፋን እውነቱን የሳተ ዕይታ ከመገለጥ አልፎ ይነቀላል። ይህ ውሸት ቤተክርስቲያናችንን ለገጠማት ኪሳራ ተጠቃሽና ተወቃሽ ነው። እንደው ምን ይሻላል አንዳንድ በጋዜጠኝነት ስም ተዋህዶ (ክርስትና) ማሊያ እየመሰላቸው እንደተኩዋሽ ቦታ እየቀያየሩ በሚለብሱት ማስመሰያ ማሊያ (ጭንብል) ማስቸገር ምን ይሉታል?  ኽረ በመድኃኔዓለም! ኽረ በስላሶች! ኽረ በወላዲት አምላክ! እግዚያብሔር ዛሬ ላይ ካቆመን አመስግነን እውነቱን አንመስክር። እስከመቼ በሁለት ሃሳቦች እናነክሳለን? ኽረ ተመከሩ! እውነት መናገር የድል ሁሉ መጀመሪያ ነውና ድፈሩት፣ ተናገሩት። በዋሻችሁ ቁጥር እውነተኛ የሙያው አርበኞችን እስከመቼ ታሸማቅቃላችሁ? በሰው ደረጃ ከማሸማቀቅ አልፋችሁ ዛሬም በውሸት የናዝሬቱን ኢየሱስ ክርስቶስን እየሰቀላችሁት እኮ ነው። እስከመቼ የወዳጅ መሳይ ጠላይ አይ መረገም! ከማህጸን መረገም ነው እንዳል የራሳችንን የሃሳብ ጸሃፊዎች ሃጢአት ብዙ ስለሆነ ፍርዱን ለአንድዬ ለባለቤቱ ሰጥተነዋል። ቢሆንም ግን መናገሩን መርጠን እነሆ ነገርናችሁ።

በቃለ መጠየቅ ሰበብ የውድቀትና የዝቅጠት ምልክት አንሁን። በዚህ በአሜሪካ ድምጽ ቃለመጠይቅ በራሳችን ታክስ ተሻግሮ የሌሎችን ጀግና የእውነት አባቶች አንገት ለማስደፋት ብቃት የጎደለው ግለሰብ ማስታወቂያ መለፍለፊያ ሆነና አረፈው። በጣም ወደታች የወረደ ስራ ነው።

እስከዛሬ በርካታ ጦማሮች የተነጣጠሩና ብዙ የተጻፈ፣ ብዙ የተነገረ ቢሆንም ልብ አላልነውምና “ምንን ምን ካላሉት አያርፍም” ነውና ለመሆኑ አባ መላኩ ማናቸው? ከየትኛው የቤተክርስቲያን የጉባዔ ትምህርት ቤት የተመረቁ ናቸው? በየትኛው ቦታ ስለምንተ ማርያም ስለ ቸሩ እግዚያብሔር ብለው ቅፍፈው በቆሎ ተማሪነት ነበሩ? ስለምንስ አየተመላሰሱ ምዕመናኑን ያውካሉ? ችግራቸውና አጀንዳቸው ምንድን ነው? በፖለቲካ ጥገኝነት የአሜሪካን መንግስት ከለላና ጠላላ የጠየቀና የተፈቀደለት ሰው፣ እንደገና ተመልሶ ያንን “ይገድለኛል፣ይፈልጠኛል፣ ይዘለዝለኛል” ‘’ምናምኔት” ካለው መንግስት ጋር  ጓንት ሆኖ በካድሬነት መሰልፍ የአሜሪካን ህግ ይፈቅዳል እንዴ? ለዚህ የህግ ሰዎች ማብራሪያ ብትሰጡበት የህዝብ ጥያቄ ነው። እኛም የህግ ባለሙያዎችን ጠይቀን ወደፊት ማብራሪያ እንዲሰጥበት እናደርጋለን።

ፍልሰት ስንቱን ያሰማል? በሬ ካራጁ የሆነ ዘመን። እስከ መቼ ስለ ጅብ እንናገራለ ጅቡን ለይተን እንቀደሰው። እናታችን ታላቋና ጥንታዊቷ፣ገናናዋ የኢት/ኦር/ተዋ/ቤ/ያን በዘመኗ በተለይም በዚህ ባለንበት በሚባላው የእሳት ዘመን የነጠሩ የበቁ አባቶች ያሉንን ያህል ጥቂት አንደበታቸውን ያልገረዙ ያልጨመቱ ከነገረ መልኮት ጋር ጭራሽ የማይተዋወቁ እንኳን ሊመሩ ለመመራት እንኳ ጥበብ የጎደላቸው በጥራዝ ነጠቅነት ካልሆነ በስተቀር ከምኑም የነገረ መለኮት ማዕድ ዙሪያ ያላለፉ በሁለት ሃሳቦች እያነከሱ ከቤል (ከጣኦት) ጋር ቆመው ዘመኑን ከቶ ሊዋጁት አይችሉም። እንኳንስ የሚባላውን የእሳት ዘመን ሊዋጁት ይቅርና ለራሳቸው ከንቱ ክብርና ጥቅም በቢተክርስቲያንችን ውስጥ የሚያስነሱት የነገር እሳት ቤተክርስቲያንያኗን ከላይ አስከ ታች ቅጥሯን እያፈረሰ የተተከሉትን እየነቀአ እያቃጠላት ተቸገረናልን እነኝህ ግለሰቦች የተሾሙበት ቀን የሀዘን ቀን ሆኗልና የሀዘን ቀን ሊባልም ይገባዋል። አዎ የሀዘን ቀን!

አሁንም እንላቸዋልን እነኝህን የሀዘን ቀኖችም ሆነ የእኔ ብጤውን በነዱት የሚነዳውን ሁሉን አውቃለሁ የሚለውን ካወቀ ማወቁ ባልከፋ ዳሩ ግን ምንም አያውቅም። “እስከ መቼ በሁለት ሀሳቦች ታነክሳላችሁ” የሚለው የእግዚያብሔር ቃል ሁላችንንም ይመለከታልና ስለ ኢትዮጵያና ስለተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከምናነክስበት ወጥተን የሃሳብ ልዩነትን ሳንፈራ እውነቱን አጥብቀን ይዘን በአንድ ሃሳብና በአንድ ልብ እንቁም። የተፈጸመ ግፍ እድሜው ቢረዝምም የዘገየ ቢመስልም፤ ፍዳን ማስከተሉ የማይቀር ነው። ወየው ለዛ ሰው። ለሁሉም ህያው እግዚያብሔር ኃይሉን ይስጠን።ዘይገረም አባ መላኩ። ተጨማሪ መረጃዎች በተከታታይ ይለቀቃሉ። ቸር ይግጠመን።