የኢትዮጵያ ራዕይ ማህበር በኔቫዳ የአቋም መግለጫ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


የኢትዮጵያ ራዕይ ማህበር በኔቫዳ አዘጋጅነት በወቅቱ የአገራችን ዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ በላስቬጋስ ከተማ በፓላስ ስቴሽን አዳራሽ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት ረቡዕ ሜይ 2/2012 ህዝባዊ ውይይ አድርጓል። በእለቱ በአማራ፣ በጋምቤላ፣ በአፋርና በሌሎችም ላይ የሚደረገውን ማፈናቀል አስመልክቶ፣ በዋልድባና በሌሎችም የእምነት ተቋማት ላይ የሚደረገውን ህገ-ወጥ የማውደም ተግባር፣ የሙስሊሙ ህብረተሰብ ጥያቄና በስርዓቱ እየተወሰደ ያለው ህገ-ወጥ እርምጃ በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያደረገውን ውይይት አጠናቆ የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

1. በአሁኑ ወቅት በስልጣን ላይ ያለው የአቶ መለስ አገዛዝ የቆየ ፀረ-አማራ እንቅስቃሴውን አጠናክሮ መቀጠሉን ተገንዝበናል። ወደፊትም ከዚህ ድርጊቱ የሚቆጠብ አይደለም። ስለዚህ ይህን ህገ-ወጥ በአማራ፣ በጋምቤላ፣ በአፋርና በሌሎችም ወገኖቻችን ላይ የሚደረግ የዘር ማጥፋት ወንጀል እናወግዛለን። ድርጊቱን ለማስቆም ሁሉም ኢትዮጵያውያን የዲሞክራሲ ኃይሎች በአንድነት በመታገል ይህንን ስርዓት ከሕዝብ ጫንቃ ላይ ለማውረድ በጋራ እንዲረባረቡ ጥሪ እናቀርባለን። በዘር ማጥፋት ወንጀል የተሳተፉ በየደረጃው ያሉ ባለስልጣናትን ለማጋለጥና ጉዳዩን ለዓለም አቀፍ ፍ/ቤት ለማቅረብና ክስ ለመመስረት የሚደረጉ ጥረቶችን ሁሉ እንደግፋለን።

2. የአቶ መለስ አገዛዝ የኢትዮጵያን አንድነት ለማፍረስና ጥንታዊ ታሪክ ለማጥፋትና የሕዝቡ የዕምነት መለያ የሆኑ ተቋማትን ለማውደም በየጊዜው የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዷል።ይህንንም ለማሳካት በኦርቶዶክስ ዕምነት ተቋማት ላይ የተለያዩ ህገ-
ወጥ እርምጃዎችን ሲወስድ፣ ለዕምነት ነጻነት የቆሙ አባቶችንና ምዕመናንን ሲያሳድድና ሲያስር ቆይቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሆን ተብሎ በገዳማት ላይ እሳት እየተለኮሰ የአገር ቅርስ ሲወድም ከድርጊቱ ጀርባ የስርዓቱ አጥፊነት በጉልህ ተስተውሏል። ዛሬም ስርዓቱ በዋልድባ ገዳም በልማት ሽፋን እየወሰደ ያለውን ህገ-ወጥ እርምጃና በመነኮሳትና በሕዝቡ ላይ የሚያደርገውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ እናወግዛለን። የሐይማኖት አባቶችና ምዕመናን በአንድነት የሚደረገውን ጥቃት በማውገዝ ይህን ስርዓት ለመለወጥ የሚደረገውን ትግል ሁሉ እንዲያግዙና እንዲቀላቀሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን። በሀይማኖት ስም የሚደረገውን የማጋጨት ሴራ በማጋለጥ ከሙስሊሙ ጎን እንዲሰለፉ እንጠይቃለን።

3. በሙስሊም ወገኖቻችን ላይ በአርሲ አሳሳና በሎሎች በስርአቱ ታጣቂዎች የተደረገውን ህገ-ወጥ ግድያና በሌሎችም ቦታዎች የተስፋፋውን መጠነ ሰፊ እስራት እናወግዛን። ገዳዮች ለፍርድ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን። የሙስሊሙን ህብረተሰብ ህጋዊ
የዕምነት ነፃነት ጥያቄ በማጣመም ስርዓቱ የሚወስደውን የኃይል እርምጃ እናወግዛለን። የሙስሊሙ ህብረተሰብ በአገሪቱ ለውጥ እስካልመጣ ድረስ ወያኔ የማንንም የዕምነት ነፃነት የማያከብር መሆኑን ተገንዝቦ የስርዓቱን በሀይማኖት ስም ሊፈጥረው የፈለገውን የእርስ በእርስ ግጭት ለማስወገድ የጥንቃቄ እርምጃ እንዲወስድና ትኩረቱን የሁሉም የጋራ ጠላት በሆነው የአቶ መለስ ስርዓት ላይ እንዲሆን እንጠይቃለን። ህጋዊ የሙስሊሙን ጥያቄ እንደግፋለን።

4. በውጭ የሚገኙ ከ10 በላይ ኢትዮጵያውያን የመገናኛ ብዙሀኖች በስልጣን ላይ ያለውን የአቶ መለስ አገዛዝ ለማዳከም ያቀረቡትን የእምቢተኝነት (የቦይኮት) ጥሪ ሙሉ ለሙሉ እንቀበላለን። ለተግባራዊነቱም ሁሉም በውጭ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ
የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያደርግ እንጠይቃለን።

5. በአሁኑ ወቅት አገራችን ከገባችበት አጣብቂኝ ለመውጣት የሁሉንም ወገኖቻችንን ያጋራ ትግል የሚጠይቅ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን በጎሳ፣ በሐይማኖት በፖለቲካ ቡድንተኝነት ሳንከፋፈል ልዩነታችንን በማቻቻል በጋራ አገር አልባ እያደረገን
ያለውን ይህን የግፍ ስርዓት በአንድነት እንድንታገል ጥሪያችንን እናቀርባለን።

በላስ ቬጋስ የምንገኝ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን

(የኢትዮጵያ ራዕይ ማህበር በኔቫዳ ኢትዮጵያውያን በአገር ጉዳይ ላይ በአንድ ላይ እንዲቆሙ እ.ኤ.አ ጁላይ 14/2010 በከተማዋ የተቋቋመና በግዛቱ የተመዘገበ የሲቪክ ድርጅት ነው።)