በመቀሌ “የአርበኞች ቀን” ቤት በማፍረስ ተከበረ፣ 15 ሺህ ነዋሪዎች ያለመጠለያ ተበተኑ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ዛሬ ሚያዚያ 27/2003 ዓ/ም ከ5,000 በላይ የሆኑ ቤቶች በመቀሌ ከተማ በግሬደርና በዶዘር እየፈረሱ ነው፡፡ ማይ አንበሳና ገፊሕ ገረብ በመባል የሚታወቁ እነዚህ መንደሮች በመቀሌ ከተማ በስተምእራብ የሚገኙ ሲሆን አብዛኞቹ ከኤርትራ ተፈናቅለው የመጡ ዜጎች የሚኖሩባቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ዜጎች ሁለቱ መንግስታት በመጣላታቸው ምክንያትና ኢትዮጵያውያን በመሆናቸው ብቻ በኤርትራ መንግስት ቤታቸው፥ ንብረታቸውንና ሀብታቸውን ተቀምተው አገራችን ወደ ሚሏት ኢትዮጵያ ባዶ እጃቸው የመጡ ነበሩ፡፡ በድጋሚ ለፍተው ግረው ባጠራቀሙት ገንዘብ ቤት ለመስራት ቢበቁም አሁንም የሰሩትን ቤት የሚቀማና የሚያፈርስ መንግስት ገጥሟቸዋል!

“አሁንስ ወዴት ብንሄድ ነው የሚሻለው?!” ይላሉ አንድ Aባት፡፡ “ወይ መጠለያ ይላዘጋጀልን ወይ ተለዋጭ ቦታ ይሰጠን ወይ ካሳ ይከፈለን እንዴት ለዓመታት አጠራቅመን ያሰራውን ቤት በጠራራ ፀሐይ እንቀማን? እኛ ዜጐች አይደለንም? ወይ ይህ መንግስት ዜጎቼ አይደላችሁም ቢለን ቁርጣችን አውቀን ወደ ምንሄድበት እንሄድ ነበር፡፡” በማለት ነው የሚያማርሩት፡፡

በአጠቃላይ ከኤርትራ ተባረው የመጡትን ጨምሮ በእነዚህ አከባቢዎች ከ15,000 በላይ ህዝብ ይኖርበታል ተብሎ ይገመታል፡፡ ይፈርሳሉ ተብለው ከሚጠበቁት ሁለት መዋእለ ህፃናትና ቅድስት አርሴማ የሚባል አንድ ቤተክርስቲያን ጭምር ይገኝበታል፡፡

በመቀሌ ከተማ ሕገ ወጥ የሚባል ቤት ካለና መፍረስም ካለበት አብዛኞቹ የክልሉ ባለስልጣናት ያሉበት የቡቡ መንደር ነው በቅድሚያ መፍረስ ያለበት፡፡ መጀመር ያለበት በዚያ ነው፤ ምክንያቱም እነዚህ ቤቶች በከተማው ማስተር ፕላን መስረት ለከተማዋ ውበት ተብሎ ለደን በተከለለ ቦታ ላይ የተሰሩ በመሆናቸው ነው፡፡

ከአምስት ዓመት በፊት በህወሀት ማእከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ጉዳዩ ተነስቶ “መፍረስ አለባቸው ተብሎ ተወስኗል” እየተባለ ይነገር ነበር፡፡ መፍርስ አለባቸው ያሉትም እንዳይፈርስ ያደረጉትም ራሳቸው እነዚህ ባለስልጣናት ስለሆኑ አሁንም የእነዚህ ቤቶች ግንባታ እንደቀጠለ ነው፡፡ በፊት “ሙስና ሰፈር” ይባል ነበር። አሁን በህንፃዎቹ ማማር የተነሳ “ሆሊውድ መንደር” እየተባለ ነው የሚጠራው፡፡ መቼም እነሱ በስልጣን ላይ እስካሉ ድረስ እነዚህን ቤቶች ደፍሮ የሚያፈርሳቸው አካል Aይኖርም፡፡ ድሀ ላይ ሲሆን ግን ሁሉም ለማፍረስ ይሯሯጣል! እነዚህ ባለጊዜዎች የድሀ ቤት “ሕገ ወጥ ነው” በሚል ሽፋን በዶዘርና በግሬደር እያፈረሱ ነው፡፡ ይህን ህዝብ የት ይወድቃል ብለው እንኳ አልተጨነቁበት፡፡ ቀድሞ ነገር በአከባቢው አስተዳደሮች እውቅና ቤቶቹ እንደተሰሩ እየታወቀ ትምህርት ቤቶችና ቤተ ክርስቲያን ሳይቀር እስኪቆረቆር ለዓመታት ዝም ብሎ ሲያይ ኖሮ ዛሬ ለማፍረስ እንዲያ መጣደፉ ለአገር ሀብት ብክነት ምንም ደንታ እንደሌለው የሚያሳይ ነው፡፡

ዛሬ በኢትዮጵያ የድል ቀን ነው! ጀግናች አባቶቻችን ኢጣሊያን ለመጨረሻ ጊዜ ያባረሩበት እለት! ትምህርት ቤት ዝግ በመሆኑ ተማሪዎች ቤታቸው ሲፈርስ ቆመው እያለቀሱ ይመለከታሉ፡፡ ትርሀስ የተባለች ተማሪ ትናንትና ለአባይ ማሰሪያ የሚሆን ብር ከቤቷ ይዛ እንድትመጣ ተነግሯታል፡፡ ግዴታ ነው ተብሏል ለተማሪው ሁሉ! ስለዚህ ትናንትና ወደ ቤቷ ስትመለስ ትልቁ ሀሳብዋ የነበረው በዚህ ኑሮ በተወደደበት ጊዜ ወላጆቿ እንድታመጣ የተጠየቀችውን ብር ከየት አምጥተው እንደሚሰጧት ነው፡፡ ዛሬ ግን ጭንቀቷ ሌላ ሆኗል፡፡ “አሁን ሲመሽ የት ነው የምናድረው?!” ስትል ነው እንባ እየቀደማት የተናገረችው!

ቤቶቹ የግድ መፍረስ ካለባቸው መጠለያ፤ ድንኳን ነገር ቢዘጋጅላቸው ምን ነበረበት! ይም ራሳቸው የሚኖሩበት እስኪያዘጋጁ ጊዜ ቢሰጣቸውስ ምን ጉዳት ያመጣል፤ ዓለም አትገለበጥ! ይህ ጉዳይ ከጀመረ ሳምንታት እያሰቆጠረ ባለበት ሰዓት በመንግስት በኩል እየተወሰደ ያለው እርምጃ አሳዛኝም አስገራሚም እየሆነ ነው ያለው።

1. ይህን ያስተባብራሉ ያላቸውን ሁሉ አስሯል። እመጫት ሴት አለችበት ከታሰሩት ውስጥ! እስካሁን ወደ ሀምሳ ያህሉ ሰዎች ናቸው የታሰሩት የሚባለው።

2. ቀጥሎ ያደረገው የተወሰኑ በጣም ጥቂት የሆኑ የፓርቲው አባላት ቀደመው እቃዎቻቸውን ማውጣት እንዲጀምሩ በማደረግ በህዝቡ መሀል መከፋፈለና
ተስፋ መቁረጠ እንዲፈጠር ተደርጓል።

3. ህዝቡ ንብረቱን የማያነሳ ከሆነ እንደሚወረስና ቤቱን ለማፍሰር የሚወጣውን ወጪ ሁሉ እንደሚከፍል ወረቀት እንዲለጠፍ ተደርጓል።

4. ወደ አከባቢው ማንም የውጭ ሰው ማለትም የአከባቢው ነዋሪ ያልሆነ ጋዜጠኛም ጭምር ዞር እንዳይል ተደርጓል።

5. አከባቢው በፖሊስና በጸጥታ ሀይሎች በመወረሩ ምክንያት አለመረጋጋትና ጭንቀት ሰፍነዋል።