የህውሃት ወታደሮች ኩብለላ ቀጥሏል

የህውሃት ወያኔ ሰራዊት በአሁኑ የታሪክ ወቅት ከታጠቁ የተለያዩ አማፅያን ጋር በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚያደርጉት የተራዘመ ጦርነተና ግጭት ሳቢያ በአካልና በሞራል ረገድ ከፍተኛ ውድቀትና የተስፋ መቁረጥ ሁኔተ እየገጠማቸው በመሆኑ፣ በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ የአምባገነኑን አገዛዝ ወታደራዊ ሕይወት እየሸሹ መሄድን ከዕለት ወደ ዕለት መምረጣቸውን በተመለከተ መሪጃ ከዘጋቢዎቻችን እንደደረሰን ሳናዘገይ ማስደመጣችን የሚታወስ ነው፡፡

በዚህም መሠረት ለህውሃት ወያኔ የሰሜን ዕዝ ቀረቤታ ያላቸው የታመኑ ውስጠ አዋቂዎች ለተባባሪ ዘጋቢዎቻችን በገለፁት መሠረት የ11ኛ ክፍለ ጦር አባላት የሆኑ፣ ከደሴ ከተማ ወጣ ብሎ ከሚገኝው የጢጣ ጦር ሰፈር የተነሱ በርካታ የሬጅመንት አባላት ጎንደር ከተማ አዘዞ በሚገኝው የጦር ካምኘ እንዲያርፋ ከተደረጉና ሰኔ 29 ቀን 1999 ዓ/ም ወደ ታች አርማጭሆ ከተንቀሳቀሱት ወታደሮች መሃል ቁጥራቸው 16 ያህሉ ከአምባጊዮርጊስ ወደ ዳባት በሚወስደው መንገድ ላይ አመቺ ጊዜን በመጠበቅ እኩለ ሌሊት ላይ ከእነሙሉ ትጥቃቸው መሰወራቸውን ነው፡፡

እነዚህ ማንነታቸው ያልታወቀ የህውሃት ወያኔ መከላከያ ሠራዊት አባላት መሰወር በሰሜን ዕዝ ብቻ ሳይሆን በዋናው ጠቅላይ ኢታማዡር ቢሮ አካባቢም ከፍተኛ መደናገጥን በመፍጠሩ በኮሎኔል ምሩፅ በረኽና በኮሎኔል ጌትነት አየነ የሚመራ መርማሪ ወታደራዊ ቡድን ሐምሌ 3 ቀን 1999 ዓ/ም በጎንደር ከተማ በምስጢር ተገኘቶ ከህውሃትና ከብአዴን የፖለቲካ ካድሬዎች፣የደህንነት አባላትና ወታደራዊ ባለሥልጣናት ጋር ረዢም ሰዓት የፈጀን ውይይት እንዳደረገ ነገር ግን ይህ መረጃ ለዝግጅት ክፍላችን ተጠናቅሮ እስከተላከበት ዕለት ድረስ ሰለጠፋት ወታደሮች ምን እርምጃ እንደተወሰደ ወይም ምን መመሪያና ትዕዛዝ እንደተሰጠ ለጊዜው ማወቅ አልተቻለም፡፡

በሌላ ወታደራዊ ነክ ዜናም የህውሃት ወያኔ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በቅርቡ ከእሥር ሰለተፈቱት የቅንጅት መሪዎች በበኩላቸው ምን አመለካከት እንዳላቸው በሚገባ ለማወቅ ያስችል ዘንድ ለህውሃት ቀረቤታና ቁርኝት ባላቸው ወታደራዊ ካድሬዎች አማካይነት የውይይት ግምገማን በተመረጡ የዕዝና የክፍለ ጦር እንዲሁም የሬጅመንት አባላት መካከል ከነሐሴ 4-11 ቀን 1999 ዓ/ም በሚቆይ የጊዜ ገደብ ውስጥ ለማካሄድ ከጠቅላይ ኤታማዡር ፅሕፈት ቤት መወሰኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ይህ የግምገማ መድረክ በተጨማሪ የህውሃት ወያኔ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከአገዛዙ ጋር የትጥቅ ፍልሚያ በማካሄድ ላይ ሰለሚገኙ የታጠቁ አማፅያን ያላቸውን ግንዛቤ፣አመለካከትና አቋም በቅጡ ለመለካት ያስችላል ተብሎ በካድሬዎችና በጦር አዛዦቹ በኩል በገሐድ የታመነበት ሲሆን፣ ከዚህ ግምገማ የሚገኝው ውጤት በህውሃት ወያኔ በኩል ለወደፊቱ ሊወስድ ሰለታቀደው እርምጃ ከወዲሁ ምንም በገሐድ ያመላከተው ነገር እንደሌለ ምንጮች አክለው ገልፀዋል፡፡ Source: mahder.com