ፍንዳታ በኦጋዴን

በምስራቅ ኢትዮጵያ በኦጋዴን ሁለት ቦምቦች በፈነዱበት ጥቃት አንድ ሲቭል መገደሉንና ሌሎች ስምንት መቁሰላቸውን ዜና ምንጭ ሮይተርስ አስታወቀ። የኢትዮጵያ መንግስትና የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጪ ግንባር ለፍንዳታው ጥቃት እርስበርስ ተወቃቅሰዋል። አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የኢትዮጵያ ማስታወቂያ ሚንስቴር ቃል አቀባይን ጠቅሶ እንደዘገበው፡ በኦጋዴን ርዕሰ ከተማ ጂጂጋ ትናንት አንድ የገበያ ቦታና አንድ ቤተክርስትያንን ዒላማ ባደረገው ጥቃት የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች ታስረዋል። ጥቃቱን የጣለው የኢትዮጵያን መንግስት ለማሳጣት የሚፈልገው የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጪ ግንባር ነው በሚል የጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ከፍተኛ አማካሪ አቶ በረከት ስምዖን ወቀሳ አሰምተዋል።

Source: DW