ሞቃዲሾ፤ የዕለት ከዕለት ግድያና ርሸናው ቀጥሏል

(DW) ግድያና ጥቃት ዕለታዊ ድርጊት ሆኖ በቀጠለባት በሶማሊያ ርዕሰ-ከተማ በሞቃዲሾ ካለፈው ሌሊት ወዲህ አንድ ጋዜጠኛና አራት የመንግሥት ባለሥልጣናት መረሸናቸው ተነገረ። የፈረንሣይ ዜና አገልግሎት ከስፍራው እንደዘገበው ጋዜጠኛው ማሃድ-አሕመድ-ኤልሚ በሁለት ታጣቂዎች ተተኩሶበት የተገደለው ዛሬ ማለዳ ወደ ሥራው በማምራት ላይ እንዳለ ነው። አሕመድ-ኤልሚ ሁለት የራዲዮና አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ያለው ብሄራዊ መገናኛ አውታር የሆርን-አፍሪክ ባልደረባ ነበር። ባለፈው ምሽትም ሱቅ-ባአድ በተሰኘው የሞቃዲሾ ሰሜናዊ ወረዳ ሁለት ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ አራት የሶማሊያ መንግሥት ባለሥልጣናት ሕይወታቸውን አጥተዋል። አንድ የአካባቢው ነዋሪ እንዳስታወቀው ሶሥቱ ባለሥልጣናት ወዲያው ሲሞቱ አራተኛው ያረፈው ወደ ሆስፒታል ከተወሰደ በኋላ ነው። አራቱ ሰዎች የአውራጃው የውስጥ አስተዳደር ባለሥልጣናት ሆነው በሶማሊያ የሽግግር መንግሥት የተሾሙት በቅርቡ ነበር። ይህ በዚህ እንዳለ ትናንት ተይዞ የታሰረው የሞቃዲሾ ዋነኛ ራዲዮ ጣቢያ የሻበሌ ባልደረባ አሁንም ነጻ አለመለቀቁን የጣቢያው ምክትል አስተዳዳሪ ጃፋር ኩካይ አስታውቀዋል። ጋዜጠኛው የታሰረው የመንግሥቱ ጸጥታ ሃይላት በጣቢያው ላይ አሰሣ ካካሄዱ በኋላ ነበር። ጣቢያው አንድ ቀን ቀደም ሲል በሞቃዲሾ ዓመጽ ላይ የተሳሳተ ዘገባ አቅርቧል በሚል ክስ ሰባት አባላቱ ሲታሰሩና ሲዘጋ አሁን የተጠቀሱት ሰዎች መለቀቃቸውንና ጣቢያው መደበኛ ስራውን እንደገና እንደቀጠለም ታውቋል።