ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በድጋሚ ፕሬዚዳንት ሆኑ

ላለፉት ስድስት ዓመታት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ምንም ፋይዳ ያልነበራቸውና ከሰውነታቸው ውፍረት፣ ከእድሜያቸው እርጅናና ከጤንነታቸው አኳያ በድጋፍ ይንቀሳቀሱ የነበሩት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በድጋሚ ለፕሬዚዳንትነት ተመረጡ፡፡ በዛሬው እለት አገሪቱን በቀጣይነት በፕሬዚዳንትነት የሚያገለግል ለመምረጥ በተደረገው ስብሰባ ገዢው ፓርቲ ስለሚያቀርበው እጩ የተለያዩ ሰዎች ይመረጣሉ ተብሎ ሲነገር የነበረ ቢሆንም ኢሕአዴግ ፕሬዚዳንቱን በድጋሚ ያስመርጣል ብሎ ያመነ ግን ማንም አልነበረም፡፡ አቶ ግርማ ባለፉት ስድስት አመታት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት በመወጣታቸው በድጋሚ ለእጩነት ሊቀርቡ እንደቻሉ ተገልፆ በድምፅ ብልጫ እንዲመረጡ ተደርጓል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰብሳቢ ከማል በድሪ ቃለመሃላ እንዲፈፅሙ ወደ መድረኩ እየመራቸው ሲመጣ በሰውና በዱላቸው ተደግፈው በግድ ነበር የቆሙት የሚቆራረጠው ትንፋሻቸው በማይክራፎኑ ውስጥ ጎልቶ እየተሰማ ቃለ መኃላ ፈፀሙ፡፡ አጠር ያለ ንግግርም አደረጉ፡፡  በጭብጨባ እንሸኛቸው በሚል ከመድረኩ በተገለፀው መሰረት ሁሉም የፓርላማ አባላት ቆመው ማጨብጨብ ጀመሩ፡፡ እሳቸውም ከቆሙበት መድረክ ላይ ለመውረድ ድጋፍ ጠሩ አራት የሚሆኑ ጠባቂዎቻቸው ከፊታቸው ቆመው ድጋፍ ሆኑላቸው በግድ እንደመጡ በግድ ወርደው ወደ ውጭ አቀኑ፡፡ እጃቸውን ወደ ላይ ከፍ አድርገው ሰላምታ ለመስጠት ሞከሩ አቃታቸው መሰለኝ በመጡበት በር ቀስ እያሉ ተመልሰው ወጡ፡፡ አብዛኛው የፓርላማ አባል ግዴታው ስለሆነ እጁን አውጥቶ መረጣቸው እንጂ ከአቶ መለስ ዜናዊና ባለቤታቸው ወ/ሮ አዜብ መስፍን ጀምሮ ሁሉም መሸማቀቁ ያስታውቅበታል፡፡  የኔ ትዝብት ግን ሌላ ነበር ሁሉም እሳቸውን ለማስመረጥ የተለያየ አላማ ሊኖረው ይችላል፡፡ እሳቸው ግን ለፕሬዚዳንትነት ሲታጩ “እንቢ” ማለትን ማን ከአፋቸው ላይ ቀማቸው? ምናልባት ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሚቀጥሉት ስድስት አመታት በአንዱ ቀን ፕሬዚዳንቷን ትቀብር ይሆን?   በእለቱ የህብረቱ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስም ለፕሬዚዳንትነት እጩ ሆነው ቀርበው የነበረ ሲሆን በድምፅ ብልጫ ተሸንፈዋል፡፡