ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሳይሰጥ ተበተነ

በዛሬው እለት የመጨረሻ ውሳኔ ያገኛሉ በሚል ተጠብቀው የነበሩት አቶ ዳንኤል በቀለ እና አቶ ነፃነት ደምሴ ለኅዳር 12 ተቀጠሩ፡፡ ሕገመንግሥቱን በማፍረስ ወንጀል በ1998 ዓ.ም ከቅንጅት አመራሮች ጋር ክስ ቀርቦባቸው የነበሩት የአክሽን ኤይድ የፖሊሲ ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል በቀለና የማህበራዊ ፍትህ በኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ አቶ ነፃነት ደምሴ በዛሬው እለት በተቀጠሩት መሰረት የፍርድ ውሳኔ ያገኛሉ በሚል ተጠብቆ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን ውሳኔውን ሰርተው ያልጨረሱት ስለሆነ እንደገና ተጨማሪ 42 ቀናት ቀጠሮ ሰጥቷቸዋል፡፡ ተከሳሾቹ ፍርድ ቤቱ በአጭር ቀጠሮ ውሳኔ እንዲሰጣቸው ቢማፀኑም ውሳኔው ከተባለው ቀን አስቀድሞ ሊደርስ ስለማይችል ኅዳር 12 ቀን 2000 ዓ.ም ለውሳኔ እንዲመጡ ሲል እየተናገሩ ሶስቱ ዳኞች ጥለዋቸው ሄደዋል፡፡