የኃይሉ ሻውል መመለስ አጠራጣሪ ሆኗል

አምስት የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ የስራ አስፈጻሚ አባላትን ከፓርቲው ህገ ደንብ ውጭ አግጃለሁ በማለት ህዝባዊው ድርጅት በገዢው ፓርቲ እየተፈጸመበት የነበረውን የማፍረስ ጥረት ከፍተኛ እገዛ የሰጡት ኃይሉ ሻውል ወደ አገር ቤት የመመለሳቸው ጉዳይ አጠራጣሪ መሆኑን የቅርብ ምንጮች አመለከቱ፡፡

ሊቀ መንበሩን መመለስ ከሚጠራጠሩት ወገኖች አንደኛው በቀድሞው የመኢአድ ጽ/ቤት በመሆን የአቶ ኃይሉን ትእዛዝ የሚያስፈጽሙት አባላት ጭምር መሆናቸው ጉዳዩን አስገራሚ አድርጎታል፡፡ በጽ/ቤቱ በሚደረጉ የውይይት አጀንዳዎች ላይም ይህ ሃሳብ ተነስቶ እንደማያውቅ ማንነታቸው እንዲገለጽ ያለፈለጉ የቅርብ ወዳጆቻቸው ገልጸዋል፡፡

በተለይ ሰሞኑን ሳሪስ አቦ የሚገኘውን የአቶ ኃይሉን ቤት ለማከራየት በደላሎች አማካይነት እየተደረገ ያለው ጥረት አቶ ኃይሉ መኖርያቸውን በዘላቂነት በአሜሪካ ሊያደርጉ ይችላሉ የሚለውን ጥርጣሬ አጉልቶታል፡፡ለዚህ የመኖርያ ቤት የተጠየቀው የኪራይ መጠን 60 ሺህ ብር (U.S. $6,500 በወር) ያህል መሆኑን የተከራይ አፈላላጊዎቹ ገልጸውልናል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የፓርቲውን ሃላፊነት ተረክቦ ወሳኝ እንቅስቃሴዎችን የጀመረው የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የስራ አስፈጻሚ አካል በእሁዱ ላእላይ ም/ቤት አባላት የተላለፉትን ውሳኔዎች ለማስፈጸም ከፍተኛ እንቅስቃሴ የጀመረ ሲሆን በትናንትናው እለት በመሰብሰብ በተግባራዊ ሂደቶች ዙርያ በሚያከናውናቸው አጀንዳዎች ዙርያ መክሯል፡፡