ቅንጅት በመላ አገሪቱ ያሉ አባላቱንና ደጋፊዎቹን ማወያየት ጀመረ

የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የላእላይ ም/ቤት በቅርቡ ባደረገው ጉባኤ አማካይነት ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች እየተገበረ የሚገኝ ሲሆን በተለይም ‹‹ህዝባዊውን አደራ›› ለመወጣት በመላው አገሪቱ ከሚገኙ አባላቱና ደጋፊዎቹ ጋር የሚካሄድ ውይይት ዛሬ ጀመረ፡፡

በዋና ጸሃፊው አቶ ሙሉነህ ኢዩኤል አማካይነት በመላው አገሪቱ ከሚገኙ አባላትና ደጋፊዎች ጋር ከተካሄደው የቴሌ ኮንፍረንስ ለመረዳት እንደተቻለው በአመራሩ መካከል ተፈጥሮ የነበረው ልዩነት መጠነኛ ስጋት ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም ፓርቲው የተነሳለትንና የኢትዮጵያ ህዝብ ዘርፈ ብዙ መስዋእትነት የከፈለበትን ድርጅት ህልውና ማረጋገጥ ትግል ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑ በሰፊው ተነስቷል ሲሉ አንድ የአመራር አባል ገልጸውልናል፡፡

ከቴሌ ኮንፍረንሱ በኋላ በስልክ ያነጋገርናቸው አንድ ተሳታፊ በበኩላቸው አመራሩ የጀመረውን እንቅስቃሴ አድንቀው ይህ ፋና ወጊ ሂደት ፍሬ እንዲያፈራ በቁርጠኝነት ተዘጋጅተናል፤ትግሉም የአንድ ወቅት የወረት ስራ አይደለም በማለት እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአቶ ኃይሉ ሻውል የሚመራው የቀድሞ የመኢአድ አባላትን ያቀፈ ቡድን የፓርላማ አባላቱን ባልተመረጡባቸው ክልሎች በመላክ ልዩ ዘመቻ መጀመሩን ምንጮቻችን ገለጹ፡፡

ይህ ቡድን በደረሰባቸው ክልሎች ሁሉ የመኢአድን ህልውና የሚገነቡና ቅንጅቱ እንደቅንጅት መቀጠል የማይችል መሆኑን የሚገልጹ አፍራሽ እንቅስቃሴዎችን ጀምረዋል፡፡‹‹ፓርቲያችን በምርጫ 97 የተፈጠረ ሳይሆን 17 አመታትን ያስቆጠረ ነው›› የሚሉ አይነት የ97ቱን ህዝባዊ እንቅስቃሴ ዝቅ አድርገው የሚያሳዩና እብሪት የተሞላባቸው ዘመቻዎች እየተካሄዱ መሆኑን ከየክልሉ የደረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡