የቅንጅት ከፍተኛ አመራር በደቡብ ኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ሊያድርግ ነው

በተቀዳሚ ም/ሊቀመንበር ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የሚራው የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በመላ አገሪቱ የሚገኙ ደጋፊዎቹን ከነገ ጀምሮ ሊያነጋግር ነው፡፡

በነገው እለት የሚጀመረውን በተለያዩ ክልሎች በመዘዋወር የፓርቲውን ደጋፊዎች የማነጋገር አጀንዳ በቂ ዝግጅት ሲደረግበት እንደቆየ አንድ የሥራ አስፈፃሚ አባል ገልፀውልናል፡፡ የአመራር አባላቱ በውጭ አገራት ሲያካሂዱ የነበሩትን እንቅስቃሴ አጠናቀው እንደተመለሱ ለምን በአገር ውስጥ ያሉ ደጋፊዎቻቸውን ማነጋገር አልጀመሩም በሚል ጥያቄ ያቀረብንላቸው እኚሁ የሥራ አስፈፃሚ አባል ሲመልሱ “በፓርቲው አመራር መካከል የተፈጠረው ልዩነት እየሰፋ የሚሄድ ስለነበርና ችግሩን አንድ መቋጫ ላይ ሳናደርስ ይህን ሰፊና ጥልቅ ተግባር ለመጀመር አልቻልንም” በማለት አሁን ግን “በድርጅቱ ሕግ ደንብ መሠረት አስፈላጊ እርምጃዎች ስለተወሰዱና ዝግጅቱም ስለተጠናቀቀ ሕዝባዊውን ተልእኮ በጠንካራ አመራር እንወጣዋለን” ብለዋል፡፡

የመጀመሪያው የልኡኩ ጉዞ የሚሆነው በደቡብ ክልል ሲሆን ለዚህም ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውና ሕዝቡም የአመራሩን መምጣት በመጠባበቅ ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የልኡካን ቡድኑ በከተሞች አካባቢ ብቻ ሳይወሰን ራቅ ወዳሉ የገጠር መንደሮች ሳይቀር በመሄድ የአገሪቱ መሠረት የሆነውን አርሶ አደር ወገን ጭምር እንደሚያነጋግሩ ጨምረው አስታውቀዋል፡፡