የቅንጅት አመራር ስኬታማ ውይይት እያካሄደ ነው

በተቀዳሚ ም/ሊቀመንበር ብርቱካን ሚደቅሳ የሚመራው የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አመራር በመላ አገሪቱ እያካሄደ ያለው ደጋፊውን የማነጋገር እንቅስቃሴ ከህዝቡ ከፍተኛ አቀባበል እየተደረገለት መሆኑን የፕሮግራሙ አስተባባሪ አቶ አለማየሁ የኔነህ ለዜና አገልግሎቱ ገለጹ፡፡

አመራሩ የመጀመርያውን ዙር እንቅስቀዋሴ ባደረጉበት የደቡብ ክልል የተለያዩ ከተማዎች በክልሉ ስላለው ፖለቲካዊ፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሰፊ ውይይት የተለያዩ ተካሂዷል፡፡

በምርጫ 97 ወቅት ታይቶ የነበረው የዴሞክራሲና የፍትህ ጭላንጭል በተፈተረው ቀውስ ወደ ባሰ አዘቅት ይገባል የሚል ፍርሃት አድሮባቸው እንደነበር በውይይቱ ወቅት የገለጹት ተሳታፊዎቹ ያንን ተስፋ ከማምከን የበለጠ በደል እንደማይኖር ተናግረዋል፡፡

የጎፋ ነዋሪዎች ‹‹በአመራሩ ላይ ያለን ተስፋ ቀቢጻዊ አይደለም፡፡›› በማለት በትናንትናው እለት በሳውላ ከተማ በተካሄደው ውይይት ላይ ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል፡፡

የፓርቲው የስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው የክልሉ ህዝብ ሳየውን ተነሳሽነት አስመልክቶ ያላቸውን አስተያት ሲገልጹ ‹‹አበረታችና የተካሄደውን ዘርፈ ብዙ ትግል ተገቢውን መስመር እንደያዘ የሚያመለክት ነው፡፡›› ብለዋል፡፡

የቡታጅራ፤ የሃድያ፤ የጋሞና የወላይታ ህዝብ ለልኡካኑ አበረታች የሆኑ የትግል ቃል ኪዳኖችን የገባ ሲሆን በተለይ የፓርቲው ስያሜ የሆነው የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ሰርተፍኬት አየለ ጫሚሶ ለተባለ ግለሰብ መሰጠቱ ቁጣቸውን ቀስቅሷል፡፡ ምርጫ ቦርድ የወሰደው እርምጃ ከወያኔ አለቆቹ የወረደለትን መመርያ ለመፈጸም ብቻ ቢሆንም በሚሊዮን በሚቆጠረው የፓርቲው ደጋፊና መራጭ ህዝብ ላይ የተፈጸመ ደባ ነው ብለዋል፡፡

በዛሬው እለት በወላይታ አረካ ከተማ ላይ ተመሳሳይ ውይይት የተካሄደ ሲሆን በቀጣይ ቀናት ሻሸመኔ፤ ዝዋይ፤ መቂ፤ ሞጆና ደብረ ዘይት ከተሞች ላይ ሰፊ ዝግጅቶች እንደሚካሄዱ ደረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡