የአንዳርጋቸው ጽጌ ጽሁፍ በከፍተኛ ቅጅ እየተሰራጨ ነው

የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የላእላይ ም/ቤት አባል በሆኑት በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የተጻፈውና 27 ገጽ ያለው በቅንጅት ዙርያ የሚያጠነጥን ጽሁፍ በድብቅ በከፍተኛ ቅጅ በመሰራጨት ላይ ይገኛል፡፡

‹‹ያለፈውንና ያለንበትን አይቶ የወደፊቱን አቅዶ መንቀሳቀስ›› በሚል ርእስ ጥር 2000 ዓ.ም. የተጻፈውን ይህን ፖለቲካዊ ጽሁፍ በማባዛት የሚያሰራጩት ወገኖች ማንነት የማይታወቅ ቢሆንም የብዙዎች ምስጢራዊ የመነጋገርያ ርእስ ሆኗል፡፡

በድብቅ እያባዙ እስከ 30 ብር ከሚሸጡት ግለሰቦች ጽሁፉን ያገኙት የዜና አገልግሎቱ ባልደረቦች በትንታኔው አንድም ቦታ ላይ ስለ ትጥቅ ትግል የሚያወሳ እንዳላገኙ የገለጹ ቢሆንም የወያኔ ካድሬዎች ‹‹አንዳርጋቸው የትጥቅ ትግል ጀምረናል ብሎ ጽፏል››የሚል ውዥንብር በመንዛታቸው ብዙዎች ጽሁፉን ለማግኘት እንዲነሳሱ አድርጓቸዋል፡፡

ጸሃፊው በአራት ምእራፎች በመክፈል ሃሳባቸውን ያንጸባረቁ ሲሆን በሳል የፖለቲካ መፍትሄዎችን በማቅረብ አመላካች የትግል ስልቶችን መዘርዘራቸው ተመልክቷል፡፡