አቶ በድሩ አደምን ለማባበል የተደረገው ጥረት አልተሳካም

ከአቶ ሃይሉ ሻውል ጋር በመሆን በተለያዩ የውጭ አገራት በመዘዋወር የገንዘብ ማሰባሰብ ሲያደርጉ የቆዩት አቶ በድሩ አደም ወደ አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላ ቸርችል ጎዳና ወደሚገኘው የቀድሞው የቅንጅት ቢሮ እንዲመጡ በእነ አቶ አባይነህ ቢጠየቁም ደርሶብኛል በሚሉት በደል የተነሳ ቅሬታ ስላደረባቸው አኩርፈው መቀመጣቸውን የቅርብ ምንጮቻችን ገለጹ፡፡

በዛሬው እለት ጠዋት ሁለት የመኢአድ አባላት እቤታቸው ድረስ በመሄድ ያነጋገሯቸው ሲሆን እረፍት ላይ ስለሆንኩ በድርጅታዊ ጉዳዮች ላይ ሊቀመንበሩ እስኪመለሱ አልሳተፍም በማለት መልሰዋል፡፡

ተልእኳቸውን ያጠናቀቁ የሚመስሉት አቶ በድሩ ያኮረፉት ላደረጉት የውጭ አገር የድጋፍ ቅስቀሳና የገንዘብ ማሰባሰብ ከፍተኛ መጠን ያለው ክፍያ በመጠየቃቸው ነው መባሉ በአቶ ሃይሉ ሻውል ስር ያሉት ግለሰቦች በሙሉ ተመሳሳይ አቋም ያላቸው አድርጓአዋል ሲሉ በትግሉ አብረዋቸው የቆዩ አባላት በቅሬታ ገልጸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አዲስ ፓርቲ የማቋቋም ጥያቄ በመያዝ ወደ ምርጫ ቦርድ የሄደው የቅንጅት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከአዲስ አበባ 750፤ እንዲሆም ከአራቱ ክልሎች (ኦሮሚያ፤ ደቡብ፤ ትግራይና አማራ) እንዲሁ 750 በአጠቃላይ 1500 መስራች አባላትን ለማቅረብ ዝግጁ ሆኖ እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡

የቅንጅት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ቢሮ ከማግኘት ጋር በተያያዘ እየደረሰበት ያለውን ጫና ለመቀነስ ይረዳል በማለትም የመከራያ ዋጋውን መጠን በእጥፍ በማሳደግ (እስከ አስር ሺህ ብር) በማፈላለግ ላይ ይገኛል፡፡