ቀሪ እስረኞችን ለማስፈታት ጥረት እየተደረገ ነው

ምርጫ 97ትን ተከትሎ በተፈጠረው ቀውስ ወያኔ ያሰራቸውንና የተፈረደባቸውን እስረኞች ለማስፈታት በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የሚመራው የቅንጅት የስራ አስፈጻሚ ቡድን ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን አንድ የስራ አስፈጻሚ አባል ለዜና አገልግሎቱ ገለጹ፡፡ ወ/ት ብርቱካን በዚህ ሳምንት አሜሪካ ውስጥ በሚካሄደው የቅንጅት ሰሜን አሜሪካ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመገኘት የነበራቸውን እቅድ የሰረዙበት ዋናው ምክንያት ይሄው መሆኑ ተጠቁሟል::

በቅርቡ 28 ያህል የቅንጅቱ ጠንካራ አባላት የይቅርታ ሰነድ ፈርመው እንደወጡ የሚታወስ ሲሆን ጉዳያቸው በሂደት ላይ የነበሩ እስረኞች የፍርድ ውሳኔ ሳያገኙ ይቅርታውን ሊያገኙ አይገባም የሚል አቋም ወያኔ በመያዙ የቆዩ ቢሆንም በአሁኑ ሰአት አስር ያህል አባላት የፍርድ ውሳኔ ያገኙ በመሆኑ እነሱን የማስፈታቱ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን የስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡

የፍርድ ሂደቱን በማጓተት የትግሉን አቅጣጫና ትኩረት እስረኞቹን በማስፈታቱ ላይ ብቻ ለማድረግ የወያኔ ፍርድ ቤት እያደረገ ያለውን የተጓተተ አሰራር አስመልክቶ አባሉ በሰጡት አስተያየት ካለው የስራ ክፍፍል አንጻር ችግር አይፈጥርብንም ብለዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከእስር የተፈቱትና ወደየትውልድ አከባቢያቸው የሄዱት አባላት በወያኔ ካድሬዎች የማስፈራራት ሙከራ እየተደረገባቸው መሆኑን ለዜና አገልግሎቱ ገልጸዋል፡፡