የምርጫ ጣቢያዎች በዝግ ችሎት እየሰሩ ነው

በምርጫ ታሪክ አስገራሚ ክንውኖች እየተካሄደበት ባለው የሚያዝያው ምርጫ ከአዲስ አበባ ደቡብ ምእራብ 19 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በምትገኘው የአለም ገና ወረዳ የሚገኙት የምርጫ አስፈጻሚዎች ጽ/ቤታቸውን በመዝጋት የወያኔ እጩዎችን ብቻ በማስተናገድ ላይ እንደሚገኙ በስፍራው ተገኝቶ ያረጋገጠው ሪፖርተራችን ዘገባ አመለከተ፡፡ የምርጫ ጣብያው ሃላፊ የሆኑት አቦይ ሃይሌ በርሄ ሃላፊነት የተሞላው ተግባር በማከናወን ላይ ነን የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ወረዳዋ ለአዲስ አበባ ካላት ቀረቤታ አንጻር ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩዎቻቸውን ያቀረቡ ቢሆንም ባለፈው ሳምንት አንድ የኦህኮ እጩ ላይ ከፍተኛ ድብደባ ከተፈጸመ በኋላ የምርጫ አስፈጻሚዎቹ ከቀበሌው የአስተዳደር ሰራተኞች ጋር በመሆን በለየለት ሁኔታ የወያኔን እጩዎች ብቻ ማስተናገድ ጀምረዋል፡፡

በተያያዘ ዜና በምእራብ ሸዋ ዞን ከአምቦ ከተማ 33 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በምትገኘው ጉርሰሉ ከተማ ኦፌዴን እጩ የነበሩ ግለሰብ ትናንት ሌሊት ላይ ከቤታቸው ታፍነው የተወሰዱ ሲሆን እስካሁን የደረሱበት እንደማይታወቅ ከጽ/ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡