Tesfaye GebreAb’s new book to be released April 10

Author Tesfaye GebreAb’s new book, Yederawiw Mastawesha, is due to be released on April 10 in Ethiopian stores around the world. The 400-page book is Tesfaye’s best work yet.

The following is an interview Netsanet Publishers recently conducted with Tesfaye GebreAb:

PDF

የኢትዮጵያውያን ባለአክስዮኖች ንብረት የሆነው “ነፃነት የመፃህፍት አሳታሚና አከፋፋይ” በቅርቡ፣ “የደራሲው ማስታወሻ” የተባለውን መፅሃፍ አሳትሞአል። መፅሃፉ 10 April 2010 ለህዝብ ይቀርባል ተብሎ እየተጠበቀ ነው። አሳታሚ ኤጀንሲው ከመፅሃፉ ደራሲ ከተስፋዬ ገብረአብ ጋር በመፅሃፉ ዙሪያ አጭር ቃለመጠይቅ አካሂዶአል። የመፅሃፉ አንባብያን ስለ መፅሃፉ ይዘት ግንዛቤ ይኖራቸው ዘንድ የቃለመጠይቁን ጭማቂ በዚህ መንገድ አቅርበነዋል።

ነፃነት – “የደራሲው ማስታወሻ” ተፅፎ ማለቁን የሰማነው 2009 ማብቂያ ላይ ነበር። እስካሁን ለምን ዘገየ? ምን ችግር ገጠመህ?

ተስፋዬ – እንዳሰብኩት አልሆነልኝም። ካቀድኩት ሶስት ወራት ዘግይቼያለሁ። አስተማማኝ አሳታሚ የማግኘቱ ሂደት እንደገመትኩት ቀላል አልነበረም። ለማሳተም ፈቃደኛ የነበሩ ግለሰቦች ጥሩ የስርጭት መዋቅር አልነበራቸውም። በርከት ያለ ቁጥር ለማሳተምም አስተማማኝ ካፒታል ይጠይቅ ነበር። ለማንኛውም መፅሃፍ ለማሳተም ሶስት ወራት መዘግየት አጭር ጊዜ ነው። ዋናው ነገር አሁን ተሳክቶአል። ነፃነት አሳታሚ በምፈልገው መንገድና ጊዜ መፅሃፉን በማሳተሙና ለማሰራጨት በመዘጋጅቱ ከልብ አመሰግነዋለሁ።

ነፃነት – ቀዳሚው መፅሃፍህ “የጋዜጠኛው ማስታወሻ” ነበር ስሙ። ይህን “የደራሲው ማስታወሻ” ብለኸዋል። ልዩነቱ ምንድነው?

ተስፋዬ – ልዩነት የለውም። አንባብያን ሁለቱን መፃህፍት በቀላሉ መለያየት እንዲችሉ ብቻ ነው ስሙን የለወጥኩት። “ክፍል 2” ማለቱን አልወደድኩትም። በተቀረ ደራሲውም ሆነ ጋዜጠኛው እኔ ነኝ። እዚህም ላይ በተመሳሳይ የአፃፃፍ ዘዴ ማስታወሻዎቼን ነው ያሰፈርኩት።

ነፃነት – ቀዳሚውን ከዚህኛው እንዴት ታወዳድረዋለህ።

ተስፋዬ – ሁለቱንም በጥንቃቄ እንደሰራሁ ይሰማኛል።

ነፃነት – “የደራሲው ማስታወሻ”ን ፅፈህ ለመጨረስ ምን ያህል ጊዜ ፈጀብህ?

ተስፋዬ – ስምንት ወራት።

ነፃነት – ማወዳደር ካለብህ ከሁለቱ የትኛው የተሻለ ነው?

ተስፋዬ – አንባቢ ሊያወዳድራቸው ይችላል። በኔ በኩል ሁለቱም በተመጣጣኝ ደረጃ ላይ እንዳሉ እገምታለሁ። በመረጃ ደረጃ ግን ይህኛው ሳይጠነክር አይቀርም። የሰው ልጅ ከእለት እለት ወደ ሙሉ ነፃነት የመጓዝ ልምዱን ማዳበር እንደሚችል አዲስ እውቀት አግንቼያለሁ።

ነፃነት – የEthiopian Review ድረገፅ ዋና አዘጋጅ አስመራ ላይ አግኝቶህ እንደነበርና የወያኔን የተቀበሩ ታሪኮች ፍለጋ ላይ እንደነበርክ ፅፎ ነበር። አስመራ ላይ ምን አገኘህ?

ተስፋዬ – አስመራ ላይ መገመት ከሚቻል በላይ ኢትዮጵያውያን አሉ። የሚገባው የሚወጣው ሳይቆጠር በርካታ አስፈላጊ ሰዎችን አግንቼያለሁ። እንደአስፈላጊነቱ በመፅሃፌ ላይ ገልጬዋለሁ። በተለይም የወያኔ ስልጣን ላይ የነበሩ ሁለት ኮሎኔሎች ጋር ያደረግሁት ቆይታ በጣም ጠቃሚ ነበር። መፅሃፌ ላይ እንደወረደ ቀርቦአል። መረጃው ለኔ ሙሉ በሙሉ አዲስ ባይሆንም በህብረተሰባችን በዝርዝር የማይታወቁ የስርአቱን ውስጣዊ አሰራርና ጠባይ የሚያጋልጡ በርካታ መረጃዎችን አግንቼያለሁ። የኢትዮጵያ የሱዳንና የኤርትራ ድንበሮች ላይም ጥቂት ቀናት ቆይቻለሁ። ከገበሬዎች ጋር ረጅም ቆይታ በማድረግ በርካታ ማስታወሻዎችን ይዣለሁ። “ቦ ጊዜ ለኩሉ” እንዲሉ ከእለታት አንድ ቀን እፅፈዋለሁ።

ነፃነት – “የደራሲው ማስታወሻ”ን ይዘት ባጭሩ ልትገልፅልን ትችላለህ?

ተስፋዬ – 424 ገፆች ያሉትን መፅሃፍ በአጭሩ መግለፅ ያስቸግራል። በጥቅሉ ግን የ“ደራሲው ማስታወሻ”ን የሚያነብ ሰው ኢትዮጵያ የተባለችውን ሃገር የሚመሩት ሰዎችን ሰብእና በትክክል ለመረዳት ይችላል። ቀደም ሲል ልገልፃቸው ያልፈለግሁትን ጭምር ይፋ አድርጌያለሁ።

ነፃነት – የግንቦት 7 የድርጅት አባል ሆነሃል ይባላል። እውነት ነው?

ተስፋዬ – የማንም የፖለቲካ ድርጅት አባል አልሆንኩም። እኔ ደራሲ ነኝ። የዘረኛውን አገዛዝ ስርአት ለመገልበጥ ለሚታገሉ ኢትዮጵያውያን ሃይሎች ሁሉ ድጋፍ እሰጣለሁ። ወያኔ መወገድ አለበት። ከኔ በላይ የወያኔን አደገኛነት ቀርቦ የሚያውቅ ማንም የለም።

ነፃነት – በቀዳሚውና በአዲሱ መፅሃፍህ ከተገለፀው ባሻገር ስለ ወያኔ ያልነገርከን ምስጢር ይኖር ይሆን?

ተስፋዬ – ተሳቅቄ ያልፃፍኩት ብዙ ነገር አለ። የህዝቡን ስሜት ሊጎዳ ይችላል ብዬ የተውኩት ታሪክ ከደርዘን ምእራፍ በላይ ነው። የወያኔ አመራር አባላት (በተለይ ስብሃት ነጋ) ከሌሎቹ የበለጠ ያምኑኝና ያቀርቡኝ ስለነበር ብዙ ምስጢር የማወቅ እድል ገጥሞኝ ነበር። ህዝብ በህዝብ ላይ እንዲቆጣ የሚያደርጉ መረጃዎች ለዘልአለሙ ተቀብረው ቢቀሩ ይሻላል።

ነፃነት – ህዝቡ የማወቅ መብት የለውም ትላለህ?

ተስፋዬ – በዚህ ወቅት መፃፍ ያለበትን እየፃፍኩ ነው።

ነፃነት – ህዝቡ ማወቅ የማይገባው ምንድነው?

ተስፋዬ – ጄኔራል ታደሰ ብሩ ለህዝብ መግለፅ ያልነበረባቸውን ምስጢር ይፋ በማድረጋቸው የተፈጠረ አደጋ አለ። ያ መረጃ አደጋውን እንደ ሰደድ እሳት አቀጣጥሎታል። ያንን መድገም አልፈልግም።

ነፃነት – ምንድነው ጄኔራሉ የገለፁት ምስጢር?

ተስፋዬ – “የደራሲው ማስታወሻ” ላይ ገልጬዋለሁ። በጥቅሉ እውነት ሁሉ መገለፅ አለበት ብዬ አላምንም። እውነትን መግለፅ መጪውን አደጋ የሚያድንና ለአንድነታችን የሚበጅ ከሆነ ብቻ ነው መገለፅ ያለበት። አለመረጋጋትን የሚያባብስ እውነት በተቻለ መጠን ተቀብሮ መቆየት አለበት። አሜሪካኖች እንደሚያደርጉት ባለታሪኮቹ ከሞቱ በሁዋላ በ50ኛው አመት ቢገለፅ ይሻላል።

ነፃነት – የወያኔ ባለስልጣናት “የጋዜጠኛው ማስታወሻ”ን አንብበውታል?

ተስፋዬ – መለስ ዜናዊ እንዳነበበው መረጃ አለኝ። መረጃውን ያገኘሁት ከአንድ የወያኔ ዲፕሎማት ነው። መለስ ካነበበው በሁዋላ፣ “የዚህ መፅሃፍ ደራሲ ጠይም ይሁን ጥቁር ትዝ አይለኝም” ብሎ መናገሩን ዲፕሎማቱ ፕሪቶሪያ የመጣ ሰሞን ነግሮናል። ተፈራ ዋልዋና በረከት ስምኦን እንዳነበቡትም ከሌላ የመረጃ ምንጭ ሰምቻለሁ። የወያኔ ካድሬዎች በአንድ ስብሰባ ላይ ስለመፅሃፉ ጉዳይ ለበረከት አንስተውለት ጠረጴዛ እየደበደበ መሳደቡን ነግረውኛል። ተፈራ ዋልዋ ባንፃሩ “የተፃፈው ልክ ነው” ማለቱን ሰምቻለሁ። ስብሃት ነጋ፣ “የኮበለለ ሰው ውዳሴ እንዲዘምርልን አንጠብቅም። እንኳን የሚያውቀውን የማያውቀውንም ቢፅፍ አይገርመኝም። ስህተት የተፈጠረው የአባላት አያያዛችን ላይ ነው” ብሎ ተጠያቂነቱን በረከት ላይ እንደጫነበት ሰምቻለሁ። የፋና ሬድዮ ጋዜጠኞች “በረከት ስምኦንና ሴኮ በመፅሃፉ ውስጥ በትክክል ተገልፀዋል” ብለው እንደሚያምኑ ከሚታመን ምንጭ አረጋግጬያለሁ። የሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤት አማረ አረጋዊ፣ “ጥቂት ማጋነን አለበት እንጂ የተፃፈው ሁሉ እውነት ነው” ብሎ ስለመናገሩ መረጃው ደርሶኛል። ከዚህ ባሻገር የወያኔ ካድሬዎች በተለያዩ የብእር ስሞች መፅሃፉን በማውገዝ ፅፈዋል። በአብዛኛው አይጋ እና ኢትዮ ሚዲያ የተባሉትን ድረገፆች በመጠቀም ቁጣቸውን አንፀባርቀዋል። ይህም በመፅሃፉ የተጋለጡት ሃቆች እንዳበገናቸው የሚያሳይ ነው። በጥቅሉ ኢትዮጵያ ላይ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ተነቦአል። ለአንድ ደራሲ ከመነበብ በላይ ግብ እና እርካታ የለውም። አዲሱ መፅሃፍ ከቀዳሚው የመረረ ነው።

ነፃነት – “የጋዜጠኛው ማስታወሻ” ላይ መለስን በአግባቡ አልነካኸውም የሚል ትችት አለ። በዚህኛውስ?

ተስፋዬ – “የደራሲው ማስታወሻ” ላይ መለስ ዜናዊ እና ስዬ አብርሃን ቀረብ ብለን እንድናውቃቸው ለማድረግ ሞክሬያለሁ። “ሁለቱ ዝሆኖች” የሚለው ምእራፍ ስዬና መለስን ይመለከታል።

ነፃነት – ቀዳሚውን መፅሃፍ ያነበቡ በረከት ስምኦን ላይ ጥላቻ አንፀባርቆአል’ ሲሉ ገልፀዋል። ምን አስተያየት አለህ?

ተስፋዬ – በረከት ላይ በግል የተለየ ጥላቻ የለኝም። የጋንጊስተር ጠባይ ስላለውና ችኩል በመሆኑ ለመሪነት አይመጥንም ብዬ ግን አምናለሁ። ይህን እዚያው አዲሳባ እያለሁ አሰፋ ማሞ የተባለ የወያኔ ካድሬ ይመራው የነበረ ስብሰባ ላይ በግልፅ ተናግሬያለሁ። በጥቅሉ በረከት ስምኦን ግራ የተጋባ ሰው ነው። አማርኛ የመናገር ፍላጎት እንደሌለው ይታወቃል። ይሄ ለሃገሪቱ ፀያፍ ስድብ ነው። በረከት እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ለኢትዮጵያዊነት ቢታገል ባከበርኩት ነበር። በዘር ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ መንቦጫረቁ ሳይበቃ፣ አማራ ሳይሆን በድርቅና ‘የአማራ ድርጅት መሪ ነኝ’ ብሎ የህዝቡን ስቃይ ማራዘሙን እንደ ከባድ ወንጀል አይበታለሁ። በመፅሃፌ ላይ በረከትን የተመለከተው አንቀፅ ሰፋ ብሎ የቀረበው ግን የቅርብ አለቃዬ ስለነበር ነው።

ነፃነት – በቀጣይ ካንተ ምን ልንጠብቅ እንችላለን?

ተስፋዬ – “የስደተኛው ማስታወሻ” የተባለ መፅሃፍ ጀምሬያለሁ።

Netsanet Publishing Agency.
Email: [email protected]
http://www.NPAbooks.com

(Tesfaye Gebreab can be reached at [email protected])