What’s Professor Mesfin’s mission (Amharic)

This article is an appeal to our respected scholar and human rights advocate Prof. Mesfin Woldemariam to leave Ethiopian freedom fighters alone, stop ridiculing their sacrifices, and instead focus on the Woyanne fascist regime.

ፕ/ር መስፍን፣ ልብዎትን አዩሁት

ከጽናት ፍቅሩ

ድሮ፣ ፕ/ር መስፍንን የአገሬ ማንዴላ ነበር የማደርጋቸው። እስር ቤት ውስጥ ከተገናኘን በሁዋላ ግን የማንዴላን የክብር ስም ውድ ነገር መሆኑ ይበልጥ ገባኝ። ስሙን በማባከኔ አልጸጸትም፣ ጭፍን አምላኪነቴን አውቃለሁና። ለነገሩማ ልደቱንስ ማንዴላ ብለነውም አልነበር። ትንሽ ፕሮፌሰሩን እንዴት እንዳወኳቸው ብናገር ጥሩ ነው።

በመጀመሪያ ያወኳቸው የመንፈስ ተማሪያቸው ሆኘ ነው፣ ማለቴ የጂኦግራፊ ትምህርት ስንማር መጽሀፋቸውን አንብቤ ነው። መቼም ለጉድ የፈጠራቸው ናቸው። ያንን ሁሉ ተራራ፣ ሜዳ፣ ወንዝና ምንጭ ሳይቀር በወረቀት ላይ ቁጭ አድርገውታል። ያኔ የተራሮችን ስም መሸምደድ ሲያቅተኝ እረግማቸው ነበር፣ ግን ደግሞ ለችሎታቸው ኮፍያየን ሁሌም እንዳነሳሁ ነው። የመጀመሪያ አመት ትምህርት ካለቀ በሁዋላ እረሳሁዋቸው። እንደገና ከእምስት አመት በሁዋላ እንዳስታውሳቸው የሚያደርግ አጋጣሚ ተፈጠረ። አንድ ጓደኛየ ለሁለተኛ ዲግሪው የማሟያ ወረቀት ሲያቀርብ፣ ፕሮፌሰሩ ከጻፉት መጽሀፍ ውስጥ ሀሳብ ወስዶ ተናገረ። አስተማሪያችን በቁጣ “እንዴት ከዚያ ቆሻሻ መጽሀፍ ትጠቅሳለህ” ብሎ በጓደኛየ ላይ ጮኸበት። ኮፍያየን የማነሳላቸው ሰው እንዲያ ሲጣጣሉ ሳይ እንደምናምን አደረገኝ። በሌላ ጊዜ ደግሞ ሌላ አስተማሪ ተመሳሳይ ነገር ተናገረ። ከዚያ መጽሀፎቻቸውን ለማንበብ ወሰንኩ። ሳነባቸው የተወሰኑት በጣም ግሩም ናቸው፣ የተወሰኑት ደግሞ የሳቸውን ችሎታ የማይመጥኑ ሆነው ተሰሙኝ። ስሜቴን ተናገርኩ እንጅ ትክክል ነኝ ማለቴ አይደለም።

ጋዜጠኛ ከሆንኩ በሁዋላ በአካል ተዋወቅሁዋቸው። ወደ ቤታቸው እየሄድኩም ስራ እሰራ ነበር። ሱባኤ ላይ ካልሆኑ በቀር ከሰዎች ጋር ለመወያት ዝግጁ ናቸው። እንደገና ደግሞ ወያኔ ቃሊቲ ሲወረውረን ተገናኘን። የእሳቸው መታሰር ለወጣቱ ጽናት እንደሚሰጡ ሁላችንም እናምን ነበር። እንደታሰበው ግን አልሆነም። ከቅንጅት መሪዎች ጋር ይጣላሉ። የሚጣሉትም በሌላ በምንም አይደለም ሰዎችን ስለሚንቁ ነው። ስድባቸው በመጽሀፍ ቅዱስ ሳይቀር የተወገዘው “ደደብ” የሚል ነው። እርሳቸውን የሚቃወም ሁሉ ደደብ ነው። በዚያች አገር ያሉት ምሁር እርሳቸው ብቻ ናቸው። የሚገርመው ግን ሲጽፉና ሲናገሩ “እኔ ብቻ አዋቂ ነኝ” የሚል ሰው እጠላለሁ ይላሉ። እርሳቸው በተግባር የዚህ በሽታ ተጠቂ መሆናቸውን ግን ገና አላውቁም። ማንም ደፍሮ ባህሪያቸውን አይነግራቸውምና፣ ተሰድቦ ሲበሳጭ ከመዋል ውጭ። አንድ ደፋር ሰው ነበር ፊት ለፊት የሚነግራቸው። እርሱንም በራዲዮ ማሳደዱ አልበቃ ብሎዋቸው አሜሪካ ድረስ መጥተው ሊገድሉት ይፈልጋሉ። ሰውየው ግን ከተራራ ላይ እንደተቀመጠች መብራት ሆኗልና ሊያጠፉት ቢሞክሩ አይደርሱበትም። ሰሞኑን በዋሽንግተን ባደረጉት ስብሰባ ላይ “እውነቱን ለመቀበል አለመዘጋጀት የሁዋላ ቀርነት ምልክት ነው” ብለው ነበር። እውነቱ ምን እንደሆነ ሲናገሩ ደግሞ ሰላማዊ ተግል ነው አሉ። “በኢትዮጽያ ወያኔን ማስወገድ የሚቻለው በሰላማዊ ትግል ነው፣ እውነቱም ይህ ነው” ብለውናል። እስርቤት እያለን የእነ ኦነግን የጦርነት የድል ዜና ሲሰሙ እንዳልጨፈሩ በአንዴ ዘነጉት መሰለኝ። ለነገሩ እርጅናውና ፊርማውም የሚያስረሳ ነው።

ከሰላማዊ ትግል ጋር ሙጭጭ ያላለው ሁሉ እንደ ሁዋላ ቀር ከተቆጠረ፣ እነማንዴላ፣ አፍሪካን ነጻ ያወጡ ፓን አፍሪካኒስቶች፣ ለነጻነት የታገሉ የኢትዮጽያ አርበኞች እና በአለም ያሉ የነጻነት ተዋጊዎች ሁሉ ሁዋላቀሮች ናቸው ማለት ነው። እንደዚህ ከመመጻደቅ፣ ሰዎችን ሁዋላ ቀር ብሎ ከመጥራት ውጭ ሌላ ምን ሁዋላ ቀርነት አለ?

እስቲ ሰላማዊ ትግል የሚሉትን እንመልከተው። ፕሮፌሰሩ እንዲህ ነበር ያሉን “ወያኔ፣ በቁንጮው መሪ በኩል ድርጅታችን ፈሪ ሆኗል ብሎ ያመነው በሶማሊያ ወይም በኤርትራ ጥንካሬ አይደለም፣ ከግንቦት 7፣1997 ከተፈጠረው የሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴ በሁዋላ እንጅ …ወያኔ በደም የተነከረ፣ ብዙ ሀብትና ንብረት የዘረፈ በመሆኑ ስልጣን መልቀቅ የሚችለው የማርያም መንገድ በመስጠት ነው”። ታዲያ እንዲህ ከሆነ ወያኔ ለምን ከግንቦቱ ምርጫ በሁዋላ የማሪያም መንገድ ሲሰጠው እምቢኝ አለ? ላደረሰው ጥፋት ተጠያቂ እንደማይሆን ማረጋገጫ ካገኘ ለምን ስልጣን አልለቅም ይላል? ደግሞስ ስልጣን የማይለቀው የማሪያም መንገድ የሚሰጠው ስላጣ ነው? እንኳን ወያኔ፣ ሀያ አራት ሰአት ነጮቹን ደፋ ቀና ብሎ ያገለገለው ቀርቶ በፈረንጆቹ ላይ ሲጨማለቅ የነበረው መንግስቱም ሀይለማሪያምም የማሪያምን መንገድ አግኝቷል። ወያኔ በስልጣን ላይ በመቆየት ሊያገኝ የሚፈልገው አላማ ከስልጣን እና ከገንዘብ በላይ ነው። አገር የማፍረሱ ስራ እስካላለቀ ድረስ ስልጣን አይለቅም። እየፈራ ያለውም ጠንካራ ሀይል በግንቦት 7 በኩል እየመጣ መሆኑን ስላየ ነው እንጅ ሽባ ያደረገውን የሰላማዊ ተግል እንቅስቃሴ አይደለም።

በነገራችን ላይ በሰላማዊ ትግል ውስጥም የአመጽ ትግል መኖሩን አንርሳ። ንብረት ማውደም፣ ፖሊሲ መግደል ምንድነው? ከጦርነት ጋር የመጠን ካልሆነ ምን ልዩነት አለው?

ፕሮፌሰሩ ሲናገሩ በጣም ያሳቀኝ ደግሞ “ሰዎች ሲፈሩ ሽማግሌና አደራዳሪ ይሆናሉ” ያሉት ነገር ነው። አቤት! ፕሮፌሰሩ በእስርቤት ውስጥ ስለሽምግልና የተናገሩትን እረሱት መሰለኝ። በጊዜው ይዘውት የነበረው አቋም አሁን ሰላማዊ ትግል የማድረግ ሀቅማቸውን እንደገደለው የተገነዘቡት አልመሰለኝም። ያኔ ከሽምግልና ውጭ ምንም ነገር አይሆንም ይሉ የነበሩት ፈርተው ነበር ማለት ነው። ብዙ ባልኩ፣ ለወያኔ አሳልፌ ባልሰጠሁዎ።

እኔ የምመክራቸው የትግሉን ቃታ በወያኔ ላይ እንዲያነጣጥሩ ነው። እርሳቸውም እንደወያኔ በአንድ ሰው ላይ ቢያነጣጥሩ ለዚያ ሰው ጥንካሬን ከመስጠት ያለፈ ነገር አይፈይዱም፡፤ ብረት ሲደበደብና ሲነድ አይደል የሚጠነክረው። ብቻ ፕሮፌሰሩ እንዳጠኗቸው ተራሮች እየተናዱና እየተሸረሸሩ ሲሄዱ እያየሁ ነው። እርከን በመስራት መሸርሸሩን ማቆም የሚቻል ይመስለኛል።