Update on St. George Brewery

The following is an update (see the previous post here) on the ongoing labor crisis at the St. George Brewery in Addis Ababa, Ethiopia, where the workers complain about unfair treatment by the management and chairman of the labor union, Dr Berhanu Kassa. St. George Brewery, Ethiopia’s oldest beer producer, founded in 1922, was sold to Castel Winery of France by Privatization and Public Enterprises Supervising Agency for 10 million dollars in 1998.

PDF
የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ
የሠራተኞች ማህበርና የአክሲዮኑ ማህበር
(ካለፈው የቀጠለ)

ጌታብቻ አንተነህ – ከአዲስ አበባ

የሠራተኞች ማህበሩንና የአክሲዮኑን ማህበር ሁለቱንም አካል የሚመሩት ዶክተር ብርሃኑ ካሣ ናቸው፡፡
ዶክተር ብርሃኑ ካሣ ማለት
የቅ/ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ የምርት ሂደት ሥራ አስኪያጅ
የቅ/ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ የሠራተኖች ማህበር ሊቀ መንበር
የቅ/ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ የአክሲዮን ማህበር ሊቀ መንበር ናቸው፡፡

የቅ/ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ ሠራተኛውን በዛ ባሉ ጥቅማ ጥቅሞች በማህበሩ በኩል ይደጉማል፡፡ በተለይም የተቋቋመው የሠራተኛው ክበብ የውሃና የኤሌክትሪክ ፍጆታው የሚከፈልለት በድርጅቱ ነው፡፡ ክበቡ ተስፋፍቶ እየሠራ ከሚገኘው ትርፍ በየዓመት በዓሉ ሠራተኛው ይደጎማል፡፡ እንግዲህ አሁን በቅርቡ ተነስቶ ስለሚያወዛግበው የገብስ ጭማቂ (ተረፈ ምርት) አንስተን ወደ አክሲዮኑ ሂደት እንገባለን፡፡

ድርጅቱ ቀደም ሲል የገብሱን ጭማቂ ኩንታሉን በ 8 ብር ሂሣብ ለሠራተኛው ማህበር ይሰጥና ማህበሩ በማትረፍ ሸጦ ትርፉን ለማህበሩ በማስገባት ሁሉም ሠራተኛ የጥቅም ተጋሪ ይሆን ነበር፡፡ በኋላ ግን ድርጅቱ የካርቦን ዳይወክሳይድን ጋዝ ድራፍት ቤት ከፍተው ድራፍት ለሚሸጡ ደንበኞቹ በነጻ መስጠት ሲጀምር የገብሱንም ጭማቂ ለሠራተኛው ማህበር በነጻ ይሰጠዋል፡፡ የአክሲዮን ማህበሩም እንደተቋቋመ የገብሱ ጭማቂ ሽያጭ ለአክሲዮኑ ፈሰስ ቢደረግ አክሲዮኑን ሊያቋቁመው ይችላል በሚል ሃሳብ ተሰንዝሮ ይህም በተግባር ይከወናል፡፡

አክሲዮኑ ውስጥ የተመዘገቡት የሠራተኞች ቁጥር አነስተኛ ሲሆን አክሲዮኑ ያካተተው ደግሞ የማኔጅመንቱንም አካላት በመሆኑ ለሠራተኛው የተሰጠው የመደጎሚያ ገቢ በእጅ አዙር የማይገባቸው ሰዎች እንዲቀራመቱት ተደርጓል፡፡ ይህም ሁኔታ አብዛኛውን ሠራተኛ የሚያነጋግር ሆኖ ሲሄድ ሚሥጥሮች መውጣት ጀመሩ፡፡

የሠራተኛው ማህበርና የአክሲዮኑ ሊቀመንበር ዶክተር ብርሃኑና የአክሲዮኑ ጸሐፊ አቶ ተክለማሪያም ለየራሳቸው አነስተኛ የጭነት መኪና ይገዙና የገብሱን ጭማቂ በመጫን የትራንስፖርት ገቢ ያገኙበታል፡፡ ሆኖም ትክክለኛ አሠራራቸው ግን ይህ ሳይሆን ሁለቱም ግለሰቦች ጭማቂውን ጭነው ወስደው ኩንታሉን ከ 50 ብር በላይ ይሸጡና ለአክሲዮኑ ግን ገቢ የሚያደርጉት ኩንታሉን በፊት ድርጅቱ በሚሸጠበት ሂሣብ ነው፡፡ እንግዲህ ለአንድ ጊዜ ብቻ ቢራ ማምረቻ ከ 500 ኩንታል በላይ ገብስ ሲያስፈልግ እነዚህ ግለሰቦች ምን ያህል ገንዘብ ኪሳቸው እንደሚያስገቡ

ለማወቅ በሂሣብ ትምህርት በዲግሪ መመረቅን አይጠይቅም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የትራንስፖርትም ሂሣብ ይወስዳሉ፡፡

ሰሞኑን ሠራተኛው ያቀረበውም አቤቱታ የገብስ ጭማቂው ገቢ ወደ ሠራተኛው ማህበር ሂሣብ ውስጥ ፈሰስ ይሁን ብቻ አይመስለንም፡፡ አሠራሩም እንዲስተካከል ይጠይቃሉ፡፡ የገብስ ጭማቂው በጨረታ አብልጦ ለሚከፍል እየተሸጠ ገቢውም በትክክል ወደ ሠራተኛው መህበር ሂሣብ ውስጥ ገቢ እንዲሆንላቸውም ነው፡፡

ሠራተኞቹ ሁኔታው በአስቸኳይ ካልተስተካከለ ወደ ሕግ እንሄዳለን እንዳሉም ተሰምቷል፡፡ ስለዚህም ሠራተኞቹ አምነው ባስቀመጧቸው አካሎች ሊያገኙ የሚገባቸውን ጥቅም ተመዝብረዋልና ያለአግባብ የበለጸጉትም ከተጠያቂነት ሊያመልጡ ስለማይችሉ ይህን ዘገባ መሠረት አድርጎ የሠራተኛውን የክስ ማመልከቻ ሳይጠብቅ የጸረ ሙስና ኮሚሽን እራሱ ግለሰቦቹን ማነጋገር ይኖርበታላ የሚል እምነት አለን፡፡

ሁኔታውን አገር ውስጥ ለሚታተሙ ጋዜጦች አቅርበን ሳየሳካልን ሲቀር በ Ethiopian Review በወጣ ማግስት በ 28/12/2000 በወጣው ቁጥር 156 ሰንደቅ ጋዜጣ ላይ ማስተባበያ መሰል መግለጫ እንድናነብ ተደርጓል፡፡ የሠራተኛው ማህበር ሊቀ መንበር ለቅሬታው መንስሄ የሆኑት በቅርቡ ፋብሪካውን የተቀላቀሉ ናቸው በሚል የተዘገበውም ከአንድ የሠራተኛ ማህበር ሊቀ ምንበር የማይጠበቅ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ሠራተኛውን አባል እንዲሆን አሳምነው ያስፈረሙት እራሳቸው ሲሆኑ አባል ከሆነባት ቀን ጀምሮ ባለመብት መሆኑን እንዴት እንደዘነጉት ሊገባን አልቻለም፡፡ እንዲያውም በዘገባው መጨረሻ ላይ ዶክተሩ ከገብስ ጭማቂው የሚገኘው ገቢ የሠራተኛው ማህበር መሆኑን ተናግረዋል ይላል፡፡ ከሆነ ታዲያ ሁኔታውን ለማስተካከል ለምን ጊዜ ፈጀባቸው? በዚህም ላይ እንዴት እንደሚሸጥና ገቢው ወዴት ፈሰስ እንደሚደረግ ግን አላብራሩም፡፡ እንዲያውም በድፍረት ሠራተኛውን ወደሚመዘብሩበት ወደ አክሲዮኑ ግቡ ብንላቸው አንገባም ብለዋል በሚል ቅሬታቸውን መግለጻቸውንም ጋዜጣው ዘግቦታል፡፡ ሠራተኛው የአክሲዮኑ አባል መሆን አልፈልግም ገቢውም ወደ ትክክለኛ ቦታው ፈሰስ ይደረግ ቢል እሳቸውን ማሳዘኑ አይቀሬ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ አቤት ብለው የተነሱት ጥያቄአቸው አዎንታዊ መልስ ባስቸኳይ ካላገኘ የሰራተኛው አዋጅ ስለሚፈቅድላቸው የራሳቸውን ማህበር ለማቋቋምና የገብስ ጭማቂውንም ገቢ በተመለከተ ወደ ሕግ ፈት ለመድረስ ወደኋላ እንደማይሉ እየተነገረ ነው፡፡ በፓርቲዎች መሰነጣጠቅ የተጀመረ አባዜ ወደ ሠራተኛ ማህበሮችም እንዳይዘምት ስጋታችን ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ከተከሰተ ምን ያህል የኢንዱስትሪን ሠላም እንደሚያዛባ መገመት አያዳግትም፡፡ ስለዚህም መሪዎች ሆይ ከግትር አቋማችሁ ተላቃችሁ ሠራተኛውን አድምጡት በማለት ምክራችንን እንለግሳለን፡፡

ጌታብቻ አንተነህ
ከአዲስ አበባ
[email protected]