On the meaning and practical implication of corruption

Also available in PDF

የሙስና ትርጉም፤ ተዛማጅ ክስተቶቹና በአገርና በሕዝብ ላይ የሚያስከትላቸው ጠንቆች

ፕሮፌሰር ሰይድ ሀሠን፤ መሪ ስቴት ዩኒቨርሲቲ

ሀ) የሙስና ትርጉምና ባህሪያት፤

ከሙስና (Corruption) የመዝገበ-ቃላት ትርጉሞች አንዱ ሙስና “የአእምሮ መዛባት ወይም ብልሽት” ማለት እንደሆነ ይጠቁማል። ከመንግሥታዊ ባህሪና ድርጊት ጋር የተያያዘውና አጠር ያለው አንደኛው ትርጉሙ ደግሞ “የመንግሥት ተቋምን ወይም ሥልጣንን ተጠቅሞ የራስን ሀብት ማካበት” ማለት እንደሆነ በግልጽ ያመለክታል። በመሆኑም ሙስና በስልጣን መባለግንም ያጠቃልላል። ይህ ራስን አግባብ ባልሆነ መልክ ማበልጸግ የሚገለጸውም በሥልጣን ላይ የሚገኙት ሃላፊዎች በመንግሥት የተያዙ ንብረቶችን በድብቅ በመሸጥ ላይ ሲሰማሩ፤ ለመንግሥት መገልገያ የሚሆኑ ዕቃዎችን እንዲገዙ የተመደቡ ሰዎች ለግላቸው ክፍያ በጓሮ በኩል እንዲከፈላቸው ሲያደርጉ (kick backs via government procurement and false invoicing)፤ የተቀጠሩበትን ሥራ ለመፈጸም በሥልጣን ላይ ያሉ ግለሰቦች ጉቦ ሲወስዱና ጉቦው ካልተገፋላቸው ደግሞ የተጠየቁትን/የተቋጠሩበትን አንፈጽምም ሲሉና በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች በግዴለሽነትም ሆነ በሌላ ምክንያት የመንግስት ሃብቶች እንዲባክኑ ሲያደርጉ ነው። በተጨማሪም ሙስና አዲስ ሠራተኛ ሲቀጠር በስልጣን ላይ ያሉ ሃላፊዎች አድሎ በማድረግ ዘመዶቻቸውን ወይም ጓደኞቻቸውን ወይም የራሳቸውን ቡድን ወይም ፓርቲ አባላት ወይም የጎሳ አባላቸውን በማስቀደም ሲቀጥሩ (nepotism and favoritism)፤ በመንግሥት ሥር የነበሩትን ድርጅቶችና ተቋማት ግልጽ ባልሆነ መልክ ለጓደኞቻቸው ወይም ለዘመዶቻቸው በርካሽ ሲሸጡ እንዲሁም በሌሎች መልኮቹ ይከሰታል።

ሙስና በጣም በርከት ባሉ መልኮች የሚገለጥ ሲሆን ከላይ የተጠቀሱት ባህሪያት በጣም ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። አብዛኞቻችን ግን ሙስና ማለት ጉቦ መስጠት ወይም መቀበል ብቻ ይመስለናል። ጉቦ መውሰድ ወይም መስጠት የሙስና አንደኛው መልኩ እንጂ ሁሉንም ገጽታውን አያሳይም። ስለሆነም ሙስና በገንዘብ ስጦታ ብቻ የሚገለጽ አይደለም። አንዳንድ ጊዜ አገልግሎት በመለዋወጥ፤ ሕጋዊ አገልግሎትን ባፋጣኝ መልኩ ለጥቅም አጋሮች አሳልፎ በመስጠት፤ ወንጀለኛ እስረኛን ያለጊዜው በመልቀቅና ከእስር እንዲያመልጥ በማድረግ፤ የታክስ ክፍያ ለአንዳንድ ሰዎች እንዲቀርና እንዲቀነስ በማድረግ፤ ወይም አግባብ በሌለው መልክ ታክስን በሌሎች ላይ በመጫን፤ በየግል ንግድ ተቋማት መካከል መልካም ውድድርና ፉክክር እንዳይካሄድ በማድረግ፤ መንግሥታዊ ምስጢሮችን ለግል ድርጅቶች ወይም ግለሰቦች አላግባብ በማካፈል፤ አንዳንድ ጊዜም ምስጢር አሾልኮ በማውጣት፤ እቃ በመለዋወጥና በመሳሰሉት መልኮች ይከሰታል። በውትድርናም መስክ በሠራዊት መዋቅር ውስጥ መሪዎች ለጭፍን ተከታዮቻቸውም ሆነ ለብሄር አባሎቻቸው ባልተገባና ደረጃቸውን በማይመጥን መልክ ከፍ በማድረግ ሂደትም ይከሰታል።

ሙስና በመንግሥት አውታሮችና ሠራተኞች መካከል ብቻ ሳይሆን በግል ድርጅቶችም ውስጥ ሊከሰት ይችላል። ለምሳሌ፤ በእግር ኳስ ተጫዋች ቡድኖች በሚደረግ ፉክክር አግባብ በሌለው መልክ አንዱ ቡድን እንዲሸነፍ ማድረግ ወይም ሁለት ወይም ከሁለት የበለጡ ኩባንያዎች የዕቃዎቻቸውን ዋጋ ከፍ በማድረግ መመሳጠራቸውም ከሙስና የሚቆጠር ነው። አንዳንድ ጊዜ ሙስና በማስፈራራትና በተራ ግድያም (ማፍያ) መልክ ይከሰታል። እንደነዚህ ዓይነት በግለሰቦችና በግል ድርጅቶች መካከል የሚደረጉ የሙስና ጠባዮች መንግሥታዊ የአሠራር ብልሹነትን የሚያንፀባርቁ ክስተቶች ናቸው፤ በተለይ ደግሞ የኋለኞቹን መንግሥት እያወቀ ዝም ካላቸውና ወይም በተመሣጥሮው ውስጥ እጁን ካሰገባ!

ከዚህም በተጨማሪ የህግ አስጠባቂ ፖሊሶች ወንጀለኛ ያልሆነውን ሰው እንደ ወንጀለኛ አድርገው ሲከሱ፤ የፍርድ ቤት ዳኞች በወንጀል የተከሰሰውን ግለሰብ በሆነው ባልሆነው ያለበቂ ምክንያት ሲያጉላሉ፤ የፖሊስ ባልደረቦች የሥራ ባልደረባቸው በግለሰብ ዜጎች ላይ ባደረገው ደባ ወይም ግድያ ለመመስከር ፍላጎታቸው ሲቀንስና በመሣሰሉ ሌሎች ሁኔታዎችም ሙስና ይከሰታል። አንዳንድ መንግሥታት ደግሞ በስልጣን ያሉ ሃላፊዎች የህዝብን ሃብት ለመዝረፍ እንዲያመቻቸው አዳዲስ ህጎችን ጭምር ሲያወጡና ሲደነግጉ ይታያሉ። እነዚህና የመሳሰሉ ህጎችን ሲያወጡም የገንዘብና ሌሎች ጥቅሞች ለማግኘት ብቻም ሳይሆን የስልጣን ጥማቸውንም ለማርካት ጭምር ይሆናል። ይህም ከሙስና የሚፈረጅና ሌላው የመከሰቻ መልክ ነው።

ምንም እንኳ ሙስና በጣም በርካታ በሆኑ መልኮች ቢከሰትም፤ በአብዛኛው በስውር የሚፈጸም ነው። ይሁን እንጂ ውሎ አድሮ ገሃድ መውጣቱ ግን አይቀሬ ነው። በተለይ ከሙስና መከሰቻ መልኮች ጉቦ መሰጣጣት በድብቅ የሚደረግ ቢሆንም፤ የጉቦ መስፋፋት ጉዳይ ከቶውንም ከህዝብ ሊሠወር አይችልም። ጉቦ እንዲሰጥ የሚገደደው ራሱ ሕዝብ ነውና!

ሙስና በአንድ አገር ውስጥ መስፋፋቱን መለኪያና መመዘኛ መስፈርቶች ብዙዎች ናቸው፤ ደረጃቸውም እንዲሁ የተለያየ ነው። በመመዘኛ መስፈርቶች አማካኝነትም በሙስና የተዘፈቁ ሃገሮችን በደረጃ መመደብ የሚቻልና የተለመደ ተግባር ነው። በአንድ ዓለማቀፍ ድርጅት አመዳደብ መሠረት ኢትዮጵያ በሙስና በዓለም 139ኛውን ደረጃ ይዛለች። (ከ10 መሥፈርት ወደ 2.4 ብቻ በማግኘት)። የሚገርመው አንዳንድ ተቺዎች ኢትዮጵያ እጅጉን በሙስና የተዘፈቀች አገር ስለሆነች ይህ ደረጃ ያንሳል ሲሉ ይከራከራሉ።

አንዳንድ ጊዜ ሙስና በጣም በተቀናበረ የሌብነት መልኩ ይከሰታል። ይህ በተቀናበረ መልክ የሚከሰት ሌብነት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የአፍሪካ አገሮች በጣም ሥር የሰደደ ሲሆን፤ በሌብነቱም በተለይ በመንግስት አስተዳደር ቁንጮ ላይ የሚገኙ ሰዎች በጋራ (in a group) በዝርፊያው ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ። ይህ ዓይነቱ ዝርፊያ እንደ ናይጀሪያ ባሉ አገሮች ውስጥም በጣም የተስፋፋ ሲሆን የኢትዮጵያን ዘራፊዎች ከሌሎቹ የሚለያቸው ከራሳቸው ቡድን ወጣ ያሉ ሰዎች እንደነሱ መክበር ሲፈልጉ በጣም መናደዳቸውና በሩንም ጥርቅም አድርገው ሲዘጉ መታየታቸው ነው። ይህ የንዴት ባህሪ ደግሞ በቅናት ላይ የተመረኮዘ ስለሆነ በኢትዮጵያችን እንደሚታየው በግድ እገዛሃለሁ ከሚለው አምባገነናዊነት ጋር ይዛመድና ሙስናዉና አገዛዙ መላ ቅጣቸው የጠፋ ይሆናል። አንዳንድ ታዛቢዎች ለዚህ ምሳሌ ሲጠቅሱ፤ ሙስና በኢትዮጵያ በየጊዜው ሥር እየሰደደና እየበዛ ስለሄደ በአንድ በኩል በአቶ መለስ ዜናዊና በቡድኖቹ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በአቶ ታምራት ላይኔና በሌሎቹ ባለስልጣኖች ላይ በብርቱ ሊንጸባረቅ በቅቷል። በሙስናው ተሳታፊዎች መካከል የነበረውና ወደፊትም የሚኖረው ግጭትም ፍጹም በቅናት ላይ የተመረኮዘ ነበር፤ ነውም ይላሉ። ለዚህ ድምዳሜያቸው ከሚሰጧቸው ምክንያቶች ውስጥ እነ ታምራት ላይኔ ተዘፍቀውበት የነበረው የሙስና ጠባይ አሁን ከመጠን ባለፈ መልኩ ይበልጥ እየተስፋፋ መሄዱን ነው። ከሙስናዎቹ መገለጫዎች መካከልም የህዝብ ንብረቶችን ካንድ ክፍለ ሀገር ወደ ሌላውና በተለይም ወደአንድ ከፍለ ሀገር በማዘዋወር መልኩ ተከስቷል። ይህ ዓይነቱ ባህሪና ድርጊት እንደ ናይጄሪያ ባሉ አገሮች ውስጥ ጎልቶ የተከሰተ ቢሆንም በኢትዮጵያችን የተደረገውና በመደረግ ላይ ያለው በጣም ዓይን ያወጣ ሙስና ባለስልጣናቱ የሚያካሂዱትን ዝርፊያ የውጭ ወራሪ ኃይል በወረራ በያዘው አገር ከሚያደርገው የከፋ ዝርፊያ የሚያወዳድሩ ወገኖችም አልጠፉም።

በሌላ በኩል ሙስና ዓይን ባወጣ ሌብነት ብቻ ሳይሆን በጣም በተቀናጀ መልክ በሚካሄድ የሌብነት መልክም ይከሰታል። ይህም የሚከሰተው በስልጣን ላይ ያሉ ሃላፊዎችን በተቀናጀ መልክ በማግባባት (Lobbying) ሲሆን ይህ ዓይነቱ ሙስና በተለይ በሰለጠኑት አገሮች እጅግ ተስፋፍቶ ይገኛል። ድርጊቱ የወጣለት ዝርፊያ ቢሆንም፤ ሃብትን ከህዝብ ወስዶ ለጥቂት ቡድኖች የሚሰጥ ፍጹም ዓይን ያወጣ እኩይ ተግባር ነው። ከተራው ሙስና ለየት የሚያደርገው አንዱ ጠባዩ ግን “ሕጋዊ” መሆኑ ነው። “ሕጋዊ” ቢመስልም ያው እንደ ተራው ጉቦ አንዱን አራቁቶ ሌላውን የሚያለብስ ስለሆነ ያገርንና የህዝብን ሃብት የሚያባክን ሌብነት ነው።

ሙስና ባጠቃላይ ሲታይ ያንዲት አገር የህግ፤ የኢኮኖሚ፤ የባህልና በተለይም ደግሞ የፖለቲካ ባህል ብልሹነት ነጸብራቅ ነው። ሙስና በሁሉም አገሮች የሚገኝ ሲሆን፤ ጨርሶ ለመቋቋምም ሆነ ለማጥፋት አይቻልም። ሙስና በበዛባቸው አገሮች ውስጥ የፖለቲካና የኤኮኖሚ ተቋማት የተቋቋሙበትን ዋነኛ ተግባር በደንብ እንዳያከናውኑ ያግዳቸዋል። ጉቦ ግለሰቦችንና ቡድኖችን ያላግባብ ቢያበለጽግም፤ ገንዘቡ ወደ መንግስት ካዝና ስለማይገባ ለህዝብ ወይም ለመንግሥትም ጠቃሚ አይደለም። ጉቦ መሰጣጣት ሲበዛ በሰዎች መካከል አለመተማመንን፤ ጥርጣሬንና ግራ መጋባትን ይፈጥራል። ግራ የገባው ግለሰብም ሆነ ቡድን ወይም ድርጅት ጠንከር ብሎ ሥራውን እንዳይሠራ ይፈራል፤ ዕምነትም ያጣል። ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች ሲያወላውሉ፤ ሲፈሩ፤ ሲቸሩና ሲባቡ ምግባረ-ብልሹነት ተባብሶ አገር ወደኋላ ትቀራለች። ሙስና በበዛባቸው አገሮች የመንግሥት መስሪያ ቤቶችና አውታሮች እንዲሁም ጠቅላላው የሲቪል መስክ ባሠራር ማነቆ/ቀይ ጥብጣብ (ቢሮክራሲ) ውጣ-ውረድን የሚያስከትልና የተበላሸ ነው። ሙስና በተስፋፋ ቁጥር ዓይን ያወጣ ሌብነት ይበዛና የአንድን አገር ክቡር ባህል ጭምር መሸርሸር ይጀምራል። ሙስና ክቡር ባህልን ከለወጠ በኋላ ደግሞ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል “ጀርባዬን እከክልኝ፤ እኔም እንዳክልህ” በሚለው አመለካከት ውስጥ እንዲዘፈቅና እንዲጠመድ (entrenched) ያደርገዋል። ሙስና ባህልን ካበላሸ እያደር ለልጅ ልጅም ይተላለፋል። ዛሬ በኢትዮጵያችን በገሃድ እንደሚታየዉ ራስ ወዳዶችና ለሆዳቸው ያደሩ በብዛት የመፈለፈላቸውን ያህል ለዛሬው ሕዝብና ለነገው ትውልድ የሚጨነቁ ባለስልጣናት አልበረከቱም። በአኳያው ሙስናው በሚስጢርና በረቀቀ ዘዴ መበርከቱ ህብረተሰቡንም ጭምር ምስጥረኛ፤ ሽምቀኛ፤ ተንኮለኛና ሃሜተኛ እንዳያደርገው ያስፈራል።

በቅርቡ ኢትዮጵያን ጎብኝተው የሚመለሱ አንዳንድ ግለሰቦች እንደጠቆሙት፤ በርካታ ግለሰቦች በሥልጣን የሚባልጉትን መሪዎች እንደምሳሌ በመቁጠር እንደነሱ በሌብነት ላይ መሣተፍን መርጠዋል፤ “የአባት አገር ሲወረር፤ አብረህ ውረር” መሆኑ ነው መሰል። አንድ ምሣሌ ለመጥቀስ ያህል፤ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ፤ በሌብነት የተሰማሩ ግለሰቦች በአውራ ጎዳናዎች ዳርና ዳር ወይም አቅራቢያ የተዘረጉና በመዘርጋት ላይ ያሉ የብረት ዋልታዎችና የድልድይ ድጋፎች እየሠረቁ በድብቅ በመሸጥ ላይ መሆናቸውንና በዚህ ክፉ ተግባር የተሰማሩ የሕብረተሰቡ ክፍሎች በርካታ በመሆናቸው ስርቆቱን ለመቋቋም አልተቻለም። ይህ የሚያሳየው የማይናቅ ቁጥር ያለው የሕብረተሰባችን ክፍል “ለራሴ” እንጂ “ለአገሬ” የሚል ስሜት እያጣ መሄዱን ነው። ይህም የሙስና መስፋፋትንና የክቡር ባህልን ቀስ በቀስ መለወጥ በጉልህ የሚያሳይ ነው።

ስር የሰደደ ሙስና እያደር ከልጅ ልጅ የመተላለፉ ጉዳይ በባህላዊና በስነ ልቦናዊ መልክ ብቻ አይወሰንም። ለምሳሌ የግል ድርጅቶች፤ የፍጆታና ቁሣቁስ አምራች ኩባንያዎች አየሩን እንዲበክሉ ያደርጋል፤ በዚህም የተነሣ ብዙው የህበረተሰብ ክፍል የአስም በሽታ ተጠቂ እንዲሆን ያደርገዋል። የሣምባ ነቀርሳ ሰለባም ያደርገዋል። በነዚህ ዓይነት በሽታዎች በበለጠ የሚጎዱት ሕፃናት ስለሆኑም፤ ያገሪቱ አበባዎች ሲረግፉና በሽተኞች ሲሆኑ አገሪቱ አምራች ልጆቿን አጣች ማለት ነው። ለዚህ አልታደልንም እንጂ በበሽታው የተለከፈውን የህብረተሰብ ክፍል ጤንነት ለመንከባከብ አገሪቱ ንብረቷን እንድታባክን ትገደዳለች። በሙስና የተዘፈቁ ድርጅቶችና ኩባንያዎች ለጤናና ለሌላም ወጪ የሚጨነቁ አይደሉምና ለጥቅማቸው ሲሉ በሚያደርጉት ተግባር ወንዞችና የውሀ ማመንጫዎች በኬሚካል ሊበከሉ ይችላሉ። የዚህ ውጤቱም ህብረተሰቡን በንፁህ ውሀ እንዳይጠቀም ብሎም በሽተኛ ያደርገዋል። ኬሚካሉም ወደ መሬት ይሰርግና (አሁን እንደ ቻይና ባሉት አገሮች እንደሚከሰተው) የውሀ ማመንጫዎችን በመበከል ቀጣይ ትውልድን በሚያጠፋ መልኩ ለብዙ ዘመን በብክለት ይቀራል።

ኢትዮጵያ ወደዚህ ዓይነቱ የሙስና ገጽታ እያመራች እንደሆነ ብዙዎች ታዛቢዎች በበቂ ማስረጃ በመግለጽ ላይ ናቸው። ሙስና “ባህል” ከሆነባቸው ሁለት አገሮች ታይላንድንና ናይጀሪያን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያችን የተንሰራፋው ሙስና ከነዚህ አገሮች የሚተናነስ አይደለም። እንደሚታወቀው ናይጀሪያ ከእንግሊዝ ነፃ ከወጣች በኋላ በተደጋጋሚ በሙስና የተዘፈቁ ወታደራዊ አስተዳደሮች የተለዋውጡባት አገር ናት። እነዚህ በስልጣን የባለጉ መሪዎች ለተራው ዜጋ ያሰተማሩት፤ ጠብ-መንጃ ያለው ብዙ ሃብት ማካበት መቻሉን፤ በሙስና ተግባር በመክበር አንዱ ወንበዴ በሌላው እየተተካ ይኸው መፈራረቁን፤ በህጋዊ መልክ ኑሮን ለመግፋት ማቃቱንና በጉልበትና በውንብድና ካልሆነ በስተቀር ሌላው አማራጭ ጨለማ መሆኑን ነው። በዚህ ዓይነት ያንድ ሃገር ዜጋ ተስፋ ሲቆርጥና በመንግሥቱም ዕምነት ሲያጣ ራሱም በሌብነቱና በዝርፊያው ላይ መሰማራቱ አይቀሬ ይሆናል። አንዳንድ የናይጀሪያ ምሁራን ይህንን ጉዳይ በማስረጃነት ሲጠቅሱ “ያገሪቱ ዋና ከተማ ከነበረችው ሌጎስ ተስፋፍቶ የነበረውና አሁንም ያልጠፋው በጠራራ ጸሀይ የሚካሄድ የመኪና እና የባንክ ዝርፊያ ወደ ሌሎቹም አነስተኛ ከተሞች መስፋፋቱ የባህል መለወጥ ውጤት ነው” ይላሉ። ጠብ-መንጃ ያለው ወታደር ሀብታም ሲሆን፤ ህዝብም በተራው ጠብ-መንጃውን ይዞ በዝርፊያው እንዲሠማራ ተማረ ማለት ነው። ታይላንድ በምትባለው ወርቃማ አገርም ሙስና እንደባህል ሆኖ አንዳንድ ጊዜም እያንዳንዱ ዜጋ በሙስና ካልተሳተፈ ቅር የሚለው ይመስላል። በእጽ እንደሠከረ ሰው የሱስም ያህል ሆኗል። ይህችን ቆንጆ አገር ሁለት ጊዜ ስጎበኝም ሆነ የዚች አገር ተወላጅ ጓደኞቼ በመካከላቸው የሚያደርጉትን ቅጥ ያጣ የፍጆታና ያገልግሎት መለዋወጥ ስመለከት የዚያች አገር ባህል እንዴት እንደተበላሸ ተግንዝቤያለሁ፡፡
ሙስና የተስፋፋባቸውን አገሮች በጥልቀት ስንመለከት የሚከተሉትን የጋራ ጠባያት የሚጋሩ ሆነው እናገኛቸዋለን። አብዛኛዎቹ 1) ሕዝባቸው በድህነት አረንቋ የሚዳክር መሆኑ፤ 2) አገዛዛቸው ሶሻሊስትና የሶሻሊስት ፍልስፍና አራማጆች መሆናቸው፤ 3) አስተዳደራቸው ኢዴሞክራሲዊ የሆኑ፤ 4) በኤኮኖሚ መስክም አገሮቹ ህዝቦቻቸው በነፃ ከቦታ ወደ ቦታ ንግድ ለማካሄድ እቀባ የተደረገባቸው፤ 5) ከውጭ አገሮች ጋር ብዙም የነፃ ንግድ ልውውጥ የማያደርጉ፤ 6) ባለስልጣኖቻቸው በሕዝብ ሙሉ ተሳትፎ ምርጫ ያልተመረጡ፤ 6) ባለስልጣኖቹ ወይም ረዳቶቻቸው በራሳቸውም ሆነ በህዝባቸው ላይ እምነት የሌላቸው፤ 7) ለሥልጣን የተበቃባቸው መንገዶች ጉልበትና ጠብ-መንጃ የሆኑባቸው፤ 7) መሪ ተብዬዎቻቸው በኋላ ቀር አስተሳሰብ፤ በአምባገነንነት፤ በእብሪተኝነትና በተንኮል የተጠመዱ መሆናቸው እንዲሁም 8) አገራዊ አንድነት ሳይሆን ክፍፍል ዓይነተኛ ባህሪያቸው የሆኑ ናቸው።

ሙስና ከሚያጠቃቸው አገሮች አንዳንዶቹም እንደነዳጅ ዘይትና ወርቅ የመሳሰሉ ውድ የተፈጥሮ ህብቶች ያሏቸው ናቸው። እነዚህን የመሳሰሉ ውድ ሃብቶች የሃገር ጌጥ ከመሆን ባለስልጣኖችን ለሙስና ዳርገው ህዝብን ለመከራ ስላበቁ እንደሃገር መከበሪያ ከመቆጠር ይልቅ “እርግማኖች” የሚል ስያሜ አትርፈዋል። ይህን ክፉ አጋጣሚ የማይጋሩት ኖርዌይና ቦትስዋና ብቻ ሲሆኑ አንጻራዊ በሆነ አባባል እነዚህ ሁለት አገሮች ሃብታቸውን በተገቢው እየተጠቀሙበት ነው ማለት ይቻላል።

ለ) የሙስና መስፋፋት በኤኮኖሚ፤ በፖለቲካና በማህበራዊ ኑሮ ዘርፍ የሚያስከትለው ችግር፤

1.ኤኮኖሚን በሚመለከት – በከፊል፤
የሙስና መስፋፋት በአንድ አገር ውስጥ በጥቅም ላይ ሊውል የሚገባውን መዋዕለ-ንዋይ (Investment) ይሸረሽረዋል። የውጭ አገር ከበርቴዎችንም ቢሆን በዚያ ሃገር የመዋዕለ-ንዋይ (Foreign Investment) ተግባር እንዳይሳተፉ ተጽዕኖ ያሳድራል። በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ጥናቶች ያደረጉ ተመራማሪዎች ሲገልጹ “አንዳንድ ባለሃብቶች ወደ አንዳንድ አገሮች፤ በተለይም ወደ አፍሪካ አገሮች ውስጥ ከሚያስገቡት የውጭ ምንዛሬና መዋዕለ-ንዋይ ይልቅ ከነዚህ አገሮች ወደ ሀብታም አገሮች በስርቆት መልክ የሚወጣው የውጭ ምንዛሬ ይበልጣል” ይላሉ። አንዳንድ አበዳሪዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ “ያገር መሪዎች የሃገራቸውን ሃብት ወደውጭ የሚያሸሹ ከሆነ እኛ ምን ቸግሮን ነው ወደነዚህ አገሮች መዋዕለ-ንዋያችንን የምናስገባው?” የሚል ጥያቄ ያነሳሉ። ለአብነት ለመጥቀስ ያህል በ1997 ዓ/ም በኢትዮጵያ የተካሄደው ምርጫ በህወሓት/ኢሕአዴግ ከከሽፈ በኋላ ከኢትዮጵያ ወደ እንግሊዝ አገር የጎረፉት ሃብቶች በጣም በዝተው እንደነበር አንዳንድ የእንግሊዝ የዜና ማሰራጫዎች አጋልጠዋል። በዚያው ሰሞን ሰሚ ያጡ አቤቱታዎች ከተለያዩ አቅጣጫዎች መነሳታቸው አልቀረም። ሙስና እንደ ተጨማሪ ታክስም ስለሆነ የግል ተቋሞችና ኩባንያዎች እንዳያድጉ ያደርጋል። ሙስና በግል ተቋማትና በግለሰቦች መካከል መኖር የሚገባውን ጠቃሚ ውድድር ይቀንሳል፤ ያጫጫል።

ሙስና በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ብቻ ካለመጠን እንዲከብሩ ያደርግና በሃብታምና በድሆች መካከል ልዩነቶችና ቅራኔዎች ያስነሳል። ቅራኔው ሲገፋም ሀብታሞች ሕጋዊ ባልሆነ መልክ ያካበቷቸውን ሃብቶች ወደ ሌላ አገር እንዲያሸሹ ይገፋፋል። ይኸው ድርጊት በበኩሉ አገር ያራቁታል። ለምሳሌ የዛዬሩ ሞቡቱ ሴሴኮና የፊሊፒኑ ፈርድናንድ ማርቆስ በሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ያካበቷቸውና በውጭ አገር ባንኮች ያስቀመጧቸው ንብረቶች በብዙ ቢሊዮን ዶላር ይቆጠሩ ስለነበር ዛዬርም ሆነች ፊሊፒንስ ለብዙ ዓመታት የተከማቸባቸውን የውጭ ብድር በገዛ መሪዎቻቸው የተሰረቀው ገንዘብ ብድራቸውን ሁሉ ከፍሎ ከዕዳ ነጻ ሊያደርጋቸው እንደሚቸል ተዘግቧል።

ሙስና በአንዲት አገር ውስጥ የሚገኝን ሕጋዊና ትክክለኛ የንግድ ተግባር ያዛባል። የፍጆታ ዕቃዎች ትክክለኛ ዋጋ በተስተካከለ መልክ እንዳይተመን ያደርጋል። የሸቀጥ እቃዎች እንዲያንሱ ወይም እንዲጠፉ፤ ብሎም በጓዳ በር እንዲሸጡ መንገድ ይከፍታል። ዋጋቸው እንዲንር ያደርጋል፤ ቀስ በቀስም የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ በጣም ከፍ ይልና ህዝብን ያስቆጣል። በመንግስትና በነጋዴዎች መካከል አስፈላጊ ያልሆነ ጠብ እንዲፈጠር ያደርጋል። ባገራችንም ሆነ በሌሎች አገሮች እንደተከሰተው፤ መንግስት ነኝ ባዩ የራሱ መመሪያና ተግባር በፈጠረው ችግር ነጋዴዎች እንዲከሰሱና እንዲቀጡም ያደርጋል። በዚህ ምክንያት እንግልት፣ እስርና ግድያ ሊከተል ይችላል። የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋዎች ከፍ ሲሉ የፍጆታ ዕቃዎቹን ሊያገኙ የሚችሉ ሃብታሞችና ከነሱ ጋር ግንኙነት ያላቸው እንዲሁም ከሻጮች ጋር ዝምድና ያላቸው ብቻ ናቸው። ለዘመድና ለጓደኛ ብቻ መሸጥ ይመጣል። ሻጮች ዋጋ ከፍ አድርገው ለዘመዶቻቸውና ለጓደኞቻቸው ብቻ የመሸጣቸው ምክንያትም ለመንግስት አያጋልጡንም በሚል አስተሳሰብ ነው። ተራው ዜጋ በተለይም ድሀው የሕብረተሰብ ክፍል ግን ቁሳቁሶቹን እንዳያገኝ የገንዘብ አቅሙ የማይፈቅድለት በመሆኑ እንዲሁም ከሀብታሙም ሆነ ከሻጩ የሕብረተሰብ ከፍል ጋር የጠበቀ ግንኙነት ስለማይኖረው ሁሌም ተጎጂ ነው። እኒህን ዓይነት የሙስና ገጽታዎች በኢትዮጵያችን በጣም የተንሠራፉ ስለሆኑ ባንዳንድ ሰዎች አገላለጽ “በአገሪቱ ውስጥ ዛሬ የሚካሄደው ንግድ ከማፍያ ድርጊት የማይተናነስ ነው”። በማፍያ መልክ የሚሰራው ወንጀላዊ የንግድ አሠራር ከመብዛቱም የተነሣ በድብቅ መነገድና የጥቂቶች ብቻ መጠቃቀም ባህል ይሆናል፤ ኮንትሮባንድ ይስፋፋል፤ ዝርፊያ ይጧጧፋል፤ ወንበዴዎች ይፈጠራሉ፤ ይባስ ብለውም ወንበዴዎች የራሣቸውን ኬላ ይፈጥራሉ፤ እንዳሻቸው ይዘርፋሉ። የሚያሳዝነው ግን እነዚህን የመሰሉ ክስተቶች በአገራችን በሰፊው እየታዩ መሆናቸው ነው።

ሙስና ሰዎች በትጋት ሰርተው ሃብታቸውን እንዳያዳብሩ፤ ቤታቸውን እንዳያቀኑና አገራቸውን እንዳይገነቡ ያደርጋል። ዜጎች ለምርት ያላቸውን ዝግጁነት ይቀንሳል (It distorts incentives)። ይህ የሚሆንበት ምክንያቱ ብዙ ነው። ለምሳሌ በበርካታ አገሮች ውስጥ እንደታየውና እንደተከሰተው፤ ከሙስና ጋር የተሳሰሩ ድርጅቶችና የንግድ ተቋማት በመልካም መንገድ ሰርቶ መክበር አይችሉም። ሁሌም በሙስና መክበርን የሚመርጡ ናቸውና። ይህ ደግሞ ባኳያው በትክክልና በመልካም መንገድ ሥራቸውንና ሃብታቸውን ለማቃናት የሚጥሩትን ተስፋ ያስቆርጣል። ቀስ በቀስም በመልካም መንገድ የሚያካሂዱትን ሥራቸውን ለቀው ወደመጥፎ ጎዳና እንዲገፉ ይገደዳሉ፤ ብሎም እነሱም እንደሌሎቹ ጥቂት ገፋፊዎች በሙስናው እንዲሳተፉ ይገፋፋሉ። ይህ የስነ-ልቦና ለውጥ እያደር ለእንያንዳንዱ ዜጋ ይደርሰውና ቀስ በቀስ አገርና ዜጎች በሙስና ይጠመዳሉ።

ቀደም ሲል ለመጠቆም እንደተሞከረው በታዳጊ አገሮች ብዙ መዋዕለ ንዋይ የለም፤ ይባስ ብሎ ያሉትም ሲዘረፉ ደግሞ አገሮቹ ለበለጠ ድህነት ይዳረጋሉ። ያገሮቹ ጥቂት ሃብቶች ወደተወስኑ ግለሰቦችና ድርጅቶች ወይም ቡድኖች ሲገቡ ደግሞ ያላግባብ በከበሩ ቡድኖችና በተራው ዜጋ መካከል መቃቃር ከመከተሉም በላይ የሀብቱ ልዩነት ይራራቅና ለግጭትና ለብጥብጥ ይዳርጋል። ይህ ሲሆን በሙስናና በብልጣብልጥነት የከበሩት አላግባብ መክበራቸውን ስለሚያውቁ አንደኛ ሃብታቸውን ሁለተኛ ራሳቸውንም ወደ ውጭ ማሸሽ ይከተላል። ይህ ተግባር በብዙ አገሮች ውስጥ የተከሰተና በኢትዮጵያችንም እያቆጠቆጠ ያለ አስፈሪ ክስተት ነው፤ መባባሱም አያጠራጥርም።

በስልጣን የሚባልጉ ባለስልጣናትና የሙስና ተባባሪዎቻቸው ሃብት የሚያካብቱት ባቋራጭና በፍጥነት ስለሆነ፤ በፋሲካ የተዳረች ሁሌም ፋሲካ ይመስላታል ነውና፤ ሃብት ሁሉ በዚሁ መልክ የሚገኝና ምንጊዜም ሊተካ የሚችል አድርገው ስለሚቆጥሩ በፈጠነ መልክ ሃብታቸውን እንዲያባክኑ ይገፋፋሉ፤ ይታለላሉ። ባጭር ጊዜ ውስጥ ያገር ሃብት የሚወድምበት አጋጣሚ ተፈጥሮም ሃገርና ዜጋ ያለረዳት ይቀራሉ።

ብዙውን ጊዜ በሙስና የተበከሉ ሰዎች በሕገ-ወጥ መልክ ያካበቱትን ሀብት የሚያውሉት በድሎትና በቅምጥል (luxury) ዕቃዎች ላይ ነው። ከሚገዟቸው ቁሳቁሶች መካከልም፤ ውድ የሆኑ መኪኖች፤ ጌጣጌጦች፤ የቤት ማስጌጫዎች፤ መጠጥና ልብሶች ተጠቃሾች ናቸው። እንደነዚህ ያሉ እቃዎችም ባንድ በኩል አላቂና ግላዊ ስለሆኑ ላገር የሚያስገኙት ጥቅም እጅጉን ውሱን ነው። የቁሳቁሶቹ ዋጋ ከሌሎች ቁሳቁሶች ጋር ሲወዳደር ከፍ ስለሚልም የተገዙበት ንዋይ ተቀማጭ ወይም ታሳሪ እንጂ ተንቀሳቃሽ ወይም በሃገር ኢኮኖሚ ውስጥ ተዘዋውሮ ተነግዶበት ለትርፍ የሚያበቃ አይደለም። በሌላ በኩል ይህ የተወሰነው የሙስና ተስታፊ የህብረተሰብ ከፍል ብዙውን ጊዜ በውድ ቁሳቁሶችና ጌጣጌጦች በማሸብረቅ ፉክክር ተጠምዶ ስለሚቀር ለአጓጉል ባህል መጸነስ ምንጭ መሆንም ይንጸባረቅበታል።

2.ፖለቲካንና መንግስታዊ አስተዳደርን በሚመለከት (በከፊል)

ሙስና እየገነነ ሲመጣ በሃገር ዕድገት መስክ ጉልህ ሚና የሌላቸው በጣም ጥቂቶች እየከበሩ ይመጡና የመንግስትና የሕዝብ መገልገያ በሆኑ መሥሪያ ቤቶች በመስራት ብዙ ልምድ ያካበቱና ታማኝ የሆኑ፤ እንዲሁም ብቃት ያላቸው የቢሮ ሰራቶኞችን ሥራቸውን ለቀው እንዲወጡና ቀስ በቀስ ብቃት የሌላቸው በቦታው እንዲተኩ በር ይከፍታል። ይህም በሕዝብ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ መልካም ባህርይና ችሎታ ያላቸው መሪዎች እንዳይበቅሉ ያደርጋል፤ የሃገርን የብቁ ዜጋ ቋት ያራቁታል። መድረሻ የለንም የሚሉ ቢኖሩ እንኳ ታታሪና ታማኝ ሰራተኞች ሳይሆኑ ለጋሚዎች ነው የሚሆኑ።

ሙስና ላገራቸውና ለህዝባቸው ተግተው የሚሰሩ ዜጎችንና ከፍተኛ የሙያ ትምህርት የቀሰሙ ባለዕውቀቶችን የአገልግሎት ፍላጎት የሚቀንስ ነው። እየበረታ ሲሄድም የመንግስት ሥራን እየለቀቁ ለግል ጉዳይ ትኩረት መስጠት ቀዳሚ መሆን ይገዝፋል። ብዙዎች ባልሰለጠኑበት ሙያ እንዲሰማሩ እንደሚያስገድድም በብዙ አገሮች ውስጥ ታይቷል። እያደር ተስፋ እየተሟጠጠ አገራቸውን ጥልው እንዲሸሹ የሚገፉ ብዙዎች ለመሆናቸውም ጥርጥር የለውም። ይህ እየበረከተ ሲሄድ ደግሞ አገር ምሁር አልባ ይሆናል። ብዙ ሃብት ጠፍቶ የሰለጠኑ ምሁራን ለሀብታም አገሮች ሲሳይ (brain-drain) ይሆናሉ። ድሃ አገሮች ደክመው ያሰለጠኑት አዕምሮ እየሸሻቸው ያሳደጉትን መሳም ያልቻሉ ደካሞች ሆነው እንዲታዩም ምክንያት ይሆናል። ኢትዮጵያና ጋና በዚህ ረገድ ቀዳሚ ተጠቃሽ ናቸው። ቀጥተኛ የሆነ የፖለቲካ ችግር ተጨምሮበት አገራችን ዛሬ ማቆሚያ በሌለው መልክ የሰለጠነ የአእምሮ ሃብቷ እየተራቆተ ነው።

በሌላ በኩል በሙስና ምክንያት ችሎታና ብቃት ያላቸው ባለሙያዎች ከመንግስታዊ መዋቅሮች ሲለቁ ቦታው ብቁ ችሎታ በሌላቸው ሰዎች እንዲሞላ ግድ ይሆናል። ይህም እየቆየ የመንግስት መሥሪያ ቤቶች እንዲጠሉ ያደርግና ቀስ በቀስ የመንግስት ትእዛዞች እንዳይከብሩ፤ ብሎም መንግስት ራሱ እንዲጠላ የራሱ አሉታዊ ሚና ይጫወታል። በህዝብ የሚጠላ መንግስት ደግሞ ሕዝባዊ ችግሮችን ሊፈታ የሚችል አይሆንም።

በሙስና ምክንያት ሌብነት በዝቶ ድህነት ሲስፋፋ እያደር ዴሞክራሲም ደብዛው ይጠፋል። ደሞክራሲ ሲጠፋም በኤኮኖሚ የማደግ እድል ይቀንሳል። ድህነትንም ያንሰራፋል። የሰብዓዊና ሌሎችም ዴሞክራሲዊ መብቶች መታጣት በበኩሉ ለእርስ በርስ ጥልና ንክሻ ምክንያት ይሆናል። ይህ የሚንጸባረቅበት ህብረተሰብ ችግርና መከራ እንደ አዙሪት እየተሽከረከሩበት (vicious circle) ለመኖር ይገደዳል። ካዙሪቱም መውጣት አስቸጋሪ ይሆናል።

ሙስና ሲስፋፋ በሥልጣን ላይ ያሉ ግለሰቦች በሙስናው ይሰክሩና ያጋልጡናል ብለው የሚፈሯቸውን ለምሳሌ እንደ ነፃ ፕሬስና ሌሎችም የሕዝብ መገናኛ ዘዴዎች ባለሙያዎችን እንዲሁም ንቁ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማፈንና ማሳደድን ስራዬ ብለው ይይዛሉ። አፋኝ የሆኑ አዳዲስ ሕጎችን እያወጡ ነጻ አሰራሮችን ያግዳሉ፤ ጋዜጠኞችን ያስራሉ፤ ያሰቃያሉ፤ ያዋክባሉ። በዚህም የተነሳ ነጻው ፕሬስና የሕዝብ መገናኛው መድረክ ሁሉ እያደር እየተዳከመ ልፍስፍስ ይሆናል። ይኸው ድርጊት ጠቅላላው ሕብረተሰብ እንዳያውቅ እንዳይማርና እንዳይጠይቅ ሆኖ የሰጡትን ብቻ ተቀባይ እንዲሆን ያደርጋል። በኢትዮጵያችን ይህ እየሆነ ያለ ክስተት ይሁን እንጂ ህዝቡ ይባስ ብሎ ከመንግሥት ለሚተላለፉ መመሪያዎችም ሆነ ዜናዎች ጆሮ ዳባ ለበስ ካለ ዓመታት ተቆጥረዋል። ይልቁንም ዕውነትን ፍለጋ በውጭ መገናኛ ብዙሃን ዘርፎች ለመጠቀም ተገዷል። ሕዝቡ መንግሥት ተብዬው ለሚያወጣቸው መመሪያዎች ቁብ የለውም፤ እንዲለግም የተገደደበት ሁኔታ ነው የሚታየው። በዚህ ዓይነትም ፖሊሲዎች በወረቀት ላይ ብቻ ይቀራሉ። ሕዝብና መንግስትም ሆድና ጀርባ እንደሆኑ ይቀራሉ።

3.ማህበረሰባዊ ኑሮን በሚመለከት (በከፊል)

ተደጋግሞ እንደተገለጸው ሙስና እጅጉን ሲስፋፋ በመንግስት መዋቅሮች ውስጥ የሚሰሩ በተለይም በንቃት ሃገራቸውን ሊያገለግሉ የተዘጋጁና ለስልጠናቸው ብዙ የተደከመባቸው ወገኖች አእምሯቸው እንዲላሽቅ ይሆናል።

ሙስና በትምህርት፤ በሥራ ልምድና በታታሪነት ኑሮን ከማዳበር ይልቅ፤ በጓዳና ባቋራጭ መንገድ የመክበር ፍላጎትንና፡ ስግብግብነትን የሚያበረታታ ስለሆነ ተጎጂው ሁሌም ንቁውና ሃገሩን ወዳዱ ክፍል ነው። ሙስና ሁሉም ሊከብርና ኑሮውን ሊያቃና የሚችልበት ሳይሆን ጥቂቶች ያላግባብ የሚበለጽጉበት በመሆኑ “እድሉ” ያላጋጠመው አብዛኛው ሁሌም ብስጭት ላይ ይወድቃል። ኑሮውን ያማርራል፤ ተስፋ የቆረጠ የህብረተሰብ አባልን ይበረክታል። ተስፋ በቆረጠ ዜጋ ሃገር ሊያድግ ከቶውንም አይችልም። ሙስና በተለይ ድሆችን ጎጅ ነው፤ ድሆች እንኳን ጉቦ የሚከፍሉት ሊኖራቸው ቀርቶ ለራሳቸውም የሚበቃ ሃብት የላቸውምና!

በሃይማኖት በኩልም ቢሆን፤ ሙስና ከሀጢዓት (መቅሰፍት) የሚቆጠር እንጂ የሚበረታታ አይደለም። በጉቦ የተለከፈ ሕብረተሰብ ብርቱ ሞራልና የወደፊት የረጅም ጊዜ የኑሮ ዕቅድ የለውም – የዛሬን የከብሮ ማደር ብቻ ቀዳሚ ዓላማው ነውና። በሙስና የተጠመዱ ሰዎች አእምሯቸው ሁሌም የተረበሸና በጥቅም የተበረዘ በመሆኑ ቀስ በቀስ እንደተላላፊ በሽታ ሌሎቹንም የሚበክሉ ናቸው። ለዚህም ነው ሙስና እኩይ ወጥመድ ነው የሚባለው። በሙስና የተለከፉ ዜጎች ርህራሄ የጎደላቸውና ከምንም በላይ ጥቅማቸውን የሚያስቀድሙ በመሆናቸው የጋራ ሃገር ዕድገት እንቅፋቶች ናቸው። በሙስና የተጠመዱ ሰዎች ሁሉንም ለማግበስበስ በሚያደርጉት ሩጫ በተለይ ድሃው የህበረተሰብ ክፍል በመንግስት የዕለት ተዕለት አገልግሎቶች እንኳ ሳይቀር ተጠቃሚ እንዳይሆን የሚያደርጉ ጨካኞች ናቸው። ሙስና ራሱ ሃጢዓተኛ ነው የሚባለውም ለዚህ ነው።

ሙስና የህብረተሰብ የእድገት መስኮችን ሁሉ ገቺና ወደፊት የማያራምድ ማነቆ ነው። ዕድገትን ሳይሆን ዝቅጠትን የሚያስከትል አደገኛ የህዝብና የሃገር ነቀርሳ ነው።

ሙስና ወንጀለኞችን ያበራክታል፤ ብዙ ጊዜም ድሆች ዜጎች በሕይወታቸው ደስተኝነትን በማጣት ሳቢያ ህይወታቸውን እንዲያጠፉ ጭምር የሚገፋፋ ነው።
ሙስና በሰፈነበት አገር የኢኮኖምም፤ የፖለቲካም የማህበራዊ ኑሮም አዳዲስ ግኝቶችና ሀሳቦች ማፍለቅ የሚበረታታበት መድረክ ጎልቶ አይታይም። ስለሆነም ሙስና የማህበረሰባዊ ዕድገት ጠንቅ ነው።

ሐ) መደምደሚያና ማሳሰቢያ

እንደሚታወቀው ባገራችን በኢትዮጵያ (በየክፍለ ሃገሩ፤ በየከተማው፤ በየንመደሩ፤ በልዩ ልዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች፤ ዱሮ በመንግስት ሥር በነበሩት አሁን ግን “ለግል ባለ ሀብቶች” በርካሽ በተቸረቸሩት ተቋማት መካካእል፤ በግል ሀብቶች መስክ፤ ….ወዘተ) ከሙስና ጋር የተያያዘው ችግርና የሚደረገው ደባ ተዘርዝሮ አያልቅም። በጠመንጃ ሃይል ለስልጣን የበቃው መንግስት ተብዬ ለስልጣን ሳይበቃ ገና ከጥንት ጀምሮ የቤተ-ክርስቲያን ቅርሶቻችንን ጭምር ወደ ጎረቤት አግሮች እያወጣ ይቸረችር የነበረና በሙስና እጅጉን የተጨማለቀ ስርዓት ነው። ሥልጣንን ከተቆናጠጠም በኋላ በተለይ ሕዝባዊ ተቋማትን በመመዝበርና በማዳከም ተግባር በግላጭ የተሳተፈ አገዛዝ ነው። ለምሳሌ የመብራት ሃይል ምሰሶዎችን በመንቀል ተግባር የተሰማሩ ሌቦች መልሰው ለህወሓት/ኢሕአዴግ በርካሽ መቸርቸራቸው አገዛዙ ምን ያህል እንደዘቀጠ የሚያመለክት ጉልህ ተግባር ነው። ሕዝባዊ መንግስት የለንምና በአገዛዙና በዘራፊ ወንበዴዎች በየቦታው የደረሱት በደሎች በቀጣይነት መዘገብና መጋለጥ አለባቸው።

አገር ወዳድ ግለሰቦች ይህን ከፍተኛ ሃላፊነት ለመውሰድና ድርሻችንን ለማበርከት የተዘጋጀን ሲሆን ሌሎች ደግሞ የዜግነት ግዴታችሁን መወጣት ይጠበቅባችኋል። በተለይም በቅርቡ በሃገራችን በሙስና ተግባር በመሰማራት የተደረጉ ብሔራዊ ወንጀሎችን ለመመዝገብ የሚያስችሉ መጠይቆችን የያዘ አንድ መረጃ ማሰባሰቢያ ሰነድ በማዘጋጀት ላይ ስለሆንን ዕርዳታችሁን እንሻለን። ዓላማችን የምትልኳቸውን መረጃዎች መልክ አስይዘንና፤ የራሳችንንም መረጃ አክለን ለናንተም ለቀሪው ኢትዮጵያዊ ወገናችንም ብሎም ለመላው ሰላምና ዴሞክራሲ ወዳድ የዓለማችን ክፍል የዘረኛውን የአሸባሪውንና የአምባገነኑን የህወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ገበና ለማጋለጥና በመደረግ ላይ ያለውን የጋራ ሕዝባዊ ትግል ለማገዝ ነው። ይህንን ጉዳይ በሚመለከት ያዘጋጀነውን የመረጃ መሰብሰቢያ ሰነድ በቅርቡ ይፋ እንደምናደርግ ቃል እንገባለን።

የሰነድና የመረጃ መለዋወጫ (መላላኪያ)፤ ከናንተ የምንቀበልበት አድራሻችን [email protected] ሲሆን፤ ይህንንና የመሳሰሉትን በሚመለከት ጥሪውንም ጭምር ወደፊት እናቀርባለን።

ምስጋና፤ አ.አ. እና መ.ተ. እኔ ያውተረተርኩትን ያማርኛ ጽሁፍ በደንብ ጠግነውና አስተካክለው ስላቀረቡልኝ ትልቁ ምስጋናየ ይደረሳቸው።

Dr. Seid Hassan- Professor of Economics
Department of Economics and Finance
Murray State University
[email protected]

ጥቂት ዋቢ መጻሕፍትና ጽሁፎች

Abed, George T. and Sanjeev Gubta (2002): Governance, Corruption, and Economic Performance. International Monetary Fund, Washington, D.C.

Svenssson, Jakob, (2005): “Eight Questions about Corruption.” Journal of Economic Perspectives, Volume 19, No. 3, (Summer), pp. 19-42.

The Global Programme Against Corruption: Un-Anti-Corruption toolkit, 3rd edition, Vienna, September 2004. To be found at: http://www.unodc.org/pdf/corruption/publications_toolkit_sep04.pdf