ድህነት ወይንስ ደህንነት?

አክሎግ ቢራራ (ዶር)

ከሌሎች በፍጥነት እያደጉ ከሚሄዱ አገሮች ጋር ሲነጻጸር፤ በሃገር ቤትም ሆነ በውጭ፤ ባለፉት አርባ አመታት፤ እኛ ኢትዮጵያዊያን፤ የሃገራችን ሕዝብ ችግሮች ለመፍታት፤ በጋራ፤ በመከባበር፤ በመተሳሰብ፤ በጨዋነት፤ ተነጋግረን፤ ተወያይተን አማራጮችንና መፍትሄወችን አቅርበን አናውቅም። ራቅ ብሎ ለሚያየው፤ አሁንም “ጦርነት” የምንሄድ የሚመስል የፖለቲካ ባህል እንከተላለን። በተከታታይ፤ እድሎች የሚያመልጡን ለዚህ ነው። ቅድሚያ የምንሰጠው፤ ለሃገራችንና ለተከታታይ ትውልድ መሻሻል አይደለም፤ ቢሆን ኑሮ፤ አሁን ካለንበት ወጥመድ ባልገባን ነበር። የምንከተለው የፖለቲካ አስተሳሰብ፤ አሰራርና አቅጣጫ አሁንም ወደኋላ የሚጎትት እንጅ ወደፊት የሚያሸጋግር አይደለም። ለዋጭና (Transformative Ideas and Princieples) እና፤ ህብረተሰብን የሚገነባ፤ የሚያድስ መሰረተ ሃሳብ ይዘን፤ በተከታታይ የምንጓዝ በእጅ የምንቆጠር ነን ለማለት ያስደፍራል።ሌላው ቀርቶ፤ በአለም ላይ የህይወት፤ የህብረተሰብ፤ የሃገር ለዋጭ የሆኑ፤ በሌላው አለም የሚታዩ የለውጥ ሃይሎችን (Dynamic and Transformative Social, Ecnomic and Political Forces) በጽሞና ለመገንዘብ አልቻልነም። ችግሩ፤ የግል አይደለም፤ የሃገርና የመላው ሕዝብ ጉዳይ ነው፡፡ “በጭፍን” የሚመራ አገዛዝና ህብረተሰብ፤ ለመድረስ የሚፈልግበትን አላማ ለማወቅና ከግብ ለማድረስ ያስቸግረዋል። ችግሮችን በጋራ ተወያይቶ ለማሸነፍ አያስችልም፤ ገዥው ባህሪና ተግባር “ለኔ” የሚለው እንጅ “ለእኛ፤ ለሃገራችን፤ ለመላው ሕዝባችን” የሚል አይደለም። ይህ ችግሩ፤ የገዥው ፓርቲ ብቻ አይደለም፤ የሁላችንም ነው። ችግሮችን በሌላ ማመሃኘት የተለመደ መሆኑ ሊያሳስበን ይገባል።

አገር ቤትም ሆን ውጭ፤ የተቃዋሚው ሃይል በጋራ ህወሓት/ኢህአዴግ የፈጠረውን፤ የተበላሸ፤ አድሏዊ፤ ጸረ-ፍትህ የኢኮኖሚና የማህበረሰብ ስርአት ሊፈታው አልወሰነም። አስተሳሰቡ ቢለይም፤ አሰራሩ ከገዥው ፓርቲ አልተለየም። አሁንም፤ በጥቃቅን ልዩነቶች ባህር ይዋኛል። ለአንዳንድ ተቃዋሚ ድርጅቶች ይህ ዋና የህይወታቸው መደጎሚያና የግለሰብነታቸው መታወቂያ ሁኖ ቆይቷል። ተተኪ መሪወች ለመፍጠር አልቻሉም። በሃገር ቤት፤ አንዳንድ “ተቃዋሚ ነን” ባይ ግለሰቦች ደሞዝና መደጎሚያ የሚያገኙት “ከገዠው ፓርቲ ነው” የሚሉም አሉ። ይህ አባባል አከራካሪ ቢሆንም፤ ላለው አለመተማመንና ለገዥው ፓርቲ “ከፋፍለህ ግዛው” ስልት ጥንካሬና ህይወት ሰጥቶታል። ከሕዝቡ አንጻር ሲታይ፤ በደሉ ከሁለት ጎን ነው ለማለት ይቻላል፤ ከህወሓት/ኢህአዴግ አምባገነናዊ አገዛዝ፤ ከተቃዋሚው ክፍል ድክመትና መከፋፈል። ይህን የሁለት ጎን ድክመት የሚክዱ ብዙ ናቸው። የሚያስደንቀጠው፤ በሰላም፤ በዲሞክራሳዊ አገሮች፤ በስደት የሚኖረው ተቃዋሚ ይህን የሁለት ዘርፎች ችግር ለመፍታት ከልብ ጥረት አያደርግም። አሁንም፤ በመካከሉ ጎልቶ የሚታየውን ልዩነት፤ ከአርባ አመታት በኋላ ይዞ ይጎተታል።

የመለስ ዜናዊ ከዚህ አለም ማለፍና የሃይለማሪያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚንስትርነት ችግሩን አልፈታውም፤ ሊፈታውም አይችልም። ከህወሓት/ኢህአዴግ ጋር ለመከራከር፤ ለመደራደርና ለመነጋገር፤ የተባበረ፤ ውህደትም ባይኖረው፤ የሚደጋገፍ፤ ወደ አንድ አቅጣጫ የሚራመድ ብሩህ ራእይ ያስፈልገዋል። አለበለዚያ፤ ህወሓት/ኢህአዴግ ተቃዋሚውን እየለያየ ይመታል ወይንም ራሱን ለማቆየት ይደራደራል። በተለይ፤ በሃገር ቤት ያሉት የተቃዋሚ ድርጅቶች ልዩነት ቢፈታ፤ ለሁሉም ተቃዋሚ ጥንክርና ይሰጣል፤ ዲሞክራሳዊ ስርአት ለሚፈልገው ሕዝብ፤ የሞራል ጥንካሬ ያበረክታል።ይህ ከሆነ፤ በውጭ ያለውም ተቃዋሚ አንድ ሃገሪዊ አቅጣጫ ለመያዝ ይገደዳል። አስተዋጾ ያደርጋል።

በአሁኑ ወቅት ፈረንጆች እኛን የሚንቁን በደካማነታችን፤ በመከፋፈላችን፤ ግልጽ የሆነ አገራዊ አቅጣጫ ባለመቅረጻችን (Road Map/Framework)፤ ከሃገር፤ ከወገን ብሶት በላይ የግል ድርጅቶቻችን በማስቀደማችን ነው፤ የመቻቻል ባህልና ተግባር ባለማሳየታችን ነው። የተቃዋሚው ክፍል ይህ ችግር መሆኑን አልተረዳውም። አሁንም፤ የግራ ክንፉ አስተላልፎት የሄደው የእርስ በእርስ መካሰስ፤ መቀዳደም፤ መጠላለፍ፤ ነጻነት ሳይገኝ ስልጣን መመኘት፤ እራስን ሳይመለከቱ ሌላውን መወንጀል፤ ከዲሞክራሲ በፊት፤ ላለፉ ስህተቶች ሂሳብ እንተሳሰብ (Score card and accounting for past crimes)፤ላይ ማተኮር፤ የሚያስቀድመው የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥያቄ አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ አንዃር ጥያቄ የስልጣኑ ባለቤት መሆን ነው። ስለሆነም፤ እውነተኛ ለውጥ ከፈለግን፤ ቀደምትነት የምንሰጠው ለኢትዮጵያና ለመላው ሕዝቧ ችግርና መፍትሄ መሆን ይኖርበታል። ለቡድን፤ ለፓርቲ፤ ለተወሰነ ብሄር ወይንም ለግለሰብ ታሪክ ከሆነ ከህወሓት/ኢህአዴግ አመራር ልንለይ አንችልም። ያለፉ ወንጀሎችን፤ ጥፋቶችን መወራረድ ያለበት የኢትዮጵያ ሕዝብና የመረጡት ተወካዮች ናቸው። የመወራረዱ እድል የሚፈጠረው፤ ወንጀል የሰሩ ሁሉ፤ በፍርድ የሚጠየቁበት፤ አሁን ሳይሆን፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምጽ ተከብሮ፤ ስልጣኑ ከጥቂት ወካይ ነን ባዮች ወደ ሕዝቡ ሲሻገር ብቻ ነው። ደቡብ አፍሪካ፤ ሯዋንዳ፤ ላይበሪያ፤ ቦስኒያና ሌሎች አገሮች የሆነውን ማስታወስ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይጠቅማል።

ለውጥ እጅግ አስፈላጊ ነው፤ ለዚህ ደግሞ ጠንካራ አገራዊ የፖለቲካ ድርጅት፤ ብልህ፤ አⶭቻይ፤ ሁሉን አሳታፊ፤ የዲሞክራሲ ባህልን በስራ የሚያሳይ አመራር ያስፈልጋል። ይህ ክፍተት አሁንም እንዳለ መሆኑን በተከታታይ አሳይቻለሁ። ለውጥ የሚጀምረው ከእኛ መሆኑን አስምሬበታለሁ። በዚህ ትንተና ለማቅረቭ የምፈልገው፤ እኛ ኢትዮጵያዊያን፤ እትብታችን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ነው የምንል፤ ተሰደን ተተኪ ትውልድ የተቀዳጀንና የምንቀዳጅ ሁሉ ማጤን ያለብን በዙሪያችን ያሉትን አደጋወችና ለዋጭ ሂደቶችና አለም አቀፍ ሁኔታወችን ጭምር ነው። እነዚህ በአለም የሚታዩ ለውጦች ለኢትዮጵያና ለመላው ሕዝቧ ወሳኝ ናቸው። “በደሴት” ላይ ስለማንኖር። ሆኖም፤ ለውጥ እንደ ሸቀጥ በገበያ የሚገዛ አይደለም። እንደዚያ ከሆነ፤ ጥልቀትና ሃገራዊነት አይኖረውም፤ ግልባጭ ስለሚሆን። ከሃገር ታሪክ፤ ባህልና ልምዶች ጋር መያያዝ አለበት። አንዳንድ ጊዜ፤ እኛ፤ በውጭ የምንገኝ “የለውጥ ሃዋርያት ነን” ባዮች የምናወራውና ለሕዝብ የምናስተላልፈው ከሃገራችንና ከአለም ሁኔታ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። ዱሮ ማርክስ፤ ሌኒን፤ ማኦ፤ ሆችሚን እንል ነበር፤ አሁን፤ ዲሞክራሲ እንላለለን። የአሜሪካን አይነት? የካናዳን አይነት?የህንድን አይነት? የጋናን አይነት? የቻይናን አይነት? የቬኔዙየላን አይነት? የህወሓት/ኢህአዴግ ዲሞክራሳዊ አብዮት አይነት? የትኛው ይበጃል? የካፒታሊስት የኢኮኖሚ ስርአት አስፈላጊ ነው እንላለን። የካፒታሊስት ስርአት በፈተና ላይ እንዳለ እናያለን። የቻይናን አይነት? የአሜሪካን አይነት? የናይጀሪያን አይነት? የኬንያን አይነት? በንጻ ገብያና በነጻ አሰራር ልዩነቶች አሉ፤ እነዚህን ልዩነተቾች እንዴት እናያቸዋለን፤ የመንግስትና የግል ክፍሉ የተያያዙ ሚናወች አሏቸውን? በነጻነት የምንኖር ሁሉ፤ የተለያዩ የዲሞክራሲና የኢኮኖሚ አመራሮችን፤ ልምዶችን፤ ጥንካሪና ድክመቶች ተንትነን ከሃገራችን ጋር ማገናኘት አለብን፤ ጠቃሚ አማራጮች ለማቅረብ የምንችለው በምኞትና በፍላጐት፤ በስሜትና በጥላቻ ሳይሆን፤ ጥልቀት ባለው፤ ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ በሚጠቅም ትንተናና አማራጭ አቅርቦት ብቻ ነው። ይህን ለማድረግ፤ በመጀመሪያ፤ ከራሳችንና ከድርጅቶቻችን ግምገማ መጀመር አለብን።

ለምሳሌ፤ ዲሞክራሲ ጥሩ አማራጭ ነው ካልን፤ ከሌሎች ጋር በምናደርገው ውይይት ባህሪያችን ሆነ ስራችን ዲሞክራሳዊ የሆነ አሰራር ማሳየት ግዴታ ነው፤ ነገር ግን፤ አሁንም አንደማመጥም፤ አንከባበርም። የዚህን ባህሪ ጎጅነት ለማመን እንቸገራለን፤ ይህን ጽሁፍ “እሱ ማነው የጻፈው፤ እናውቀዋለን” የምንለው ለዚህ ነው። ሌሎችንም ከሃሳቡ ወጥተን የምንከራከረው ለዚህ ነው።ለመስማማት የማንችለው “እሱ፤ እሷ፤ ማነው፤ ማናት” የሚለው ጊዜ ያለፈበት አመለካከት አሁንም ወጥመድ ሁኖ አስተሳሰባችን ካለንበት መጥቀን ነጻ ለመውጣት ስላልቻልን ነው። የገዥው ፓርቲ የበላዮች ይህን ቢያደረጉ አይፈረድባቸውም፤ የሚፈልጉትን በጠበንጃ (ጠመንጃ) ሃይል ስራ ላይ አውለዋል፤ ስልጣን ይዘዋል፤ በጠበናጃ (ጠመንጃ) ሃይል ለመቀጠል ወስነዋል። በእነሱ “የአመለካከት ወጥመድ” እስከሰራን ድረስ የትም አንደርስም። ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት፤ በሕግ የበላይነት፤ በአኩልነት፤ በፍትህ፤ በሕዝብ ስልጣን የሚያምን መንግስትና አመራር ነው። በአለም ያሉትን ለዋጭ ሂደቶች ለማሳየት የምገደደው፤ እኛ ምን ያህል ወደፊት ሊመጣ የሚችለውን ችግርና እድል በማየት፤ ለተከታታይ ትውልዶች ማሰብ እንዳለብን ለማሳየት ነው። ከዚህ ዋናው የሕዝብ የበላይነት ነው።

ቻይና ሆነ ጃፓን፤ ራሽያ ሆነ ብራዚል፤ ደቡብ አፍሪካ ሆነ አሜሪካ፤ ካናዳ ሆነ አርጀንቲና፤ ሳውዲ አረቢያ ሆነ ኬንያ፤ ሃላፊነት የሚሰማቸው መንግስታትና የኅብረተሰቭ ክፍሎች የሚጨነቁባቸው አንኳር ነገሮች አሉ። ዋናው፤ ለህዝባችን ምን አይነት የፖለቲካና የኢኮኖሚ አመራር ያዋጣዋል የሚለው ነው። እነዚህ፤ የአለምን ወሳኝ ተቋሞችና የሃሳብ መሪወች እያነጋገሩ ነው። ካነጋገሩ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ በቀጥታ ይመለከተዋል ማለት ነው። ምክንያቱም፤ የአለም ህብረተሰብ በሁሉ ዘርፍ እየተያያዘ ሂዷል፤ እኛም የዚህ መቆላለፍ ተጠቃሚም ፤ ተጎጅም ሁነናል፤ ወደፊትም እንሆናለን።ስለሆነም፤ እኛ “የበይ ተመልካች” ልንሆን አንችልም ማለት ነው። የሃገራችን ሕዝብ የራሱን እድል እንዲወስን ከተመኘን፤ በሃገራችን አንኳር ጥያቄወች ላይ መነጋገር አለብን፤ ህወሓት/ኢህአዴግ ለዚህ ማነቆ መሆን የለበትም፤ ሁሉም በሃገሩ ያገባዋል የሚለውን መሰረተ ሃሳብ መቀበል አለበት።

ከአንዃር ለውጦች መካከል ወሳኝ የሆነውን አቀርባለሁ፤

ነጻነት ተተኪ የለውም፤

ህይወት ለዋጭ የሆኑ ለውጦች ብዙ ቢሆኑም፤ በዚዝ ክፍል ላይ የማተኩረው፤ ከሁሉም በላይ ወሳኝ በሆነው በነጻነት ሚና ላይ ነው። ለምን? ነጻነት የሌለው ግለሰብ፤ ወይንም ህብረተሰብ፤ ወይንም አገር፤ በራሱ፤ ለራሱ አስቦ የራሱን የወደፊት እድል ሊዳኝና ሊመራ አይችልም። ጥገኛ ሁኖ ይቆያል። በሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን፤ የህይወት ለዋጭ የሆነው በአለም ዝናን ያገኝው ዘመናዊ መሳሪያ፤ የመገናኛ ብዙሃንን ዲሞክራሳዊ ያደረገው፤ ለሰሜን አፍሪካ፤ ለመካከለኛው ምስራቅ፤ ለበርማ፤ ለኬንያ፤ ለሃይቲ፤ ለጋና፤ ለናይጀሪያ፤ ለሩዋንዳ፤ ለተከፋፈለችውና እርጋታ ለሌላት ለሶማልያ ወዘተ ህብረተሳባዊ ለውጥ ያስገኘው ዘመናዊ የመገናኛ ቴክኖሎጅ መሰራጨት (ዲሞክራሳዊ መሆን) ነው። ይህ ቴክኖሎጅ ኢንተርኔት፤ ሞባይል፤ ዩቱብ፤ ትዊተር፤ ቴሌቪዥን የመሳሰሉትን የህይወት ለዋጮች ይጨምራል። እነዚህን የሰው ህይወት ለዋጭ የሆኑ መገናኛ ብዙሃን ያለ ገደቭ የሚፈቅድ ሃገርና መንግስት የእድል እኩልነትን ሜዳ ያስፋፋል፤ የግለሰቦችን አቅምና ተሳትፎ ያጠናክራል፤ የሰው መብትና ነጻነት ያረጋግጣል፤ ተቋማዊና ሕጋዊ ያደርጋል፤ ዘመናዊ እውቀት ያለ ገደብ እንዲሰራጭ ይፈቅዳል። ባጭሩ፤ ራስ መቻል ለህብረተሰቡ አስተዋጾ እንደሚያደርግ ይቀበላል። ይህ የዘመናዊ ቴክኖሎጅ አጠቃቀም አለመኖር ኢትዮጵያን ከሌሎች በፍጥነት ከሚያድጉ አገሮች ይለያታል። የህወሓት/ኢህአዴግ አምባገነናዊ አገዛዝ አፋኝነት በግልጽ የሚታየው በዚህ ነው።

በ 2010 የተካሄደ የተባበሩት መንግስታት ጥናት ያሳየው፤ የእጅ ስልክ፤ (የሞባየል) መሰራጨት “በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ባልታየ ደረጃ፤ የብዙ ሚሊዮን ድሃወችን ኑሮ አሻሽሏል” የሚል ነው። ማለትም፤ ድሆችን “ከዝቅተኛ ገቢ ወደ ተሻለ ገቢ” እንዲሸጋገሩ ረድቷል። ለምሳሌ፤ “በሃይቲ፤ ዱሮ ከባንኮች ብድር ለማግኘት ምንም ተስፋ ያልነብራቸው ድሃ ግለሰቦች ከባንክ ውጭ የገንዘብ እርዳታ፤ ብድር፤ ገቢ እንዲያገኙ እድል ከፍቶላቸዋል”። በኢትዮጵያ፤ መገነኛ ብዙሃን በአንድ ፓርቲ ቁጥጥር ስር ስለሆነ፤ ለኢኮኖሚ እድል መሰላል (Pillar) ሊሆን አልቻለም። እንዲያውም፤ የአፈና ዋና መሳሪያ ሁኗል። ብድርን፤ ቁጠባን ስናይ የዘመናዊ መገናኛ አጠቃቀምና ስርጭት እንዴት አድሏዊና አፋኝ እንደሆነ እናያለን። የኢትዮጵያ መንግስት የቴክኖሎጅ እድልን ለኢትዮጵያ ወጣት ትውልድ አግቧል። በማገቡ የመሻሻል እድሉን አጥቦታል።

ብድር የፖለቲካ መሳሪያ መሆኑ፤

በኢትዮጵያ ያለው የብድር አሰጣጥ ሲታይ፤ ድሃው ከባንኮች የመበደር እድሉ ዜሮ ነው ለማለት ያስችላል።ድሃው መያዣ የለውም፤ የፖለቲካ ስልጣን የለውም። ጎጆውን፤ በሬውን፤ ፍየሉን፤ እርሻውን መያዣ አድርጎ ለመበደር አይችልም። አቅም የለውም ማለት ነው። አብዛኛው ድሃ፤ ከዘመናዊው ኢኮኖሚ ውጭ ነው ለማለት ያስደፍራል፤ ጥሬ እቃ ለመሸጥ ካልሆነ በስተቀር። አቅም ከሌለው አበዳሪው አያምነውም።በአንጻሩ፤ ብዙ ቢሊዮን ዶላር ሃብት ያለው፤ ለምሳሌ፤ ሸክ አላሙዲ ከባንኮች ብዙ መቶ ሚሊዮን ብር ለመበደር ይችላል፤ ሸራተንን የሰራው በራሱ ካፒታል ሳይሆን፤ ከኢትዮጵያ ሕዝብ በተሰበሰበ፤ ከኢትዮጵያ ባንኮች በተገኘ ብድር ነው። ሌሎችም ምንም የታወቀ ካፒታል የሌላቸው በፖለቲካ ግንኙንት ብቻ ብድር አግኝተዋል፤ ኑሯቸውን ቀይረዋል። “ላለው ይጨመርለታል” የሚለው አባባል እውነት መሆኑን በኢትዮጵያ እያየን ነው። የፖለቲካ ስልጣን ካላቸው ጋር የጠነከረ ግንኙነት ያለው ግለሰብ፤ ድርጅት ይከብራል፤ ስልጣን ያለው ራሱ ከብሮ ደጋፊወች ያከብራል። ድሃው እንዳለ በድህነቱ ይቀጥላል ማለት ነው። የኢትዮጵያ ባንኮች በአሁኑ ወቅት ዲሞክራሳዊ የሆነ፤ ሚዛናዊ የሆነ ሚና ሊጫወቱ አልቻሉም፤ አይችሉም። የፖለቲካ መሳሪያ ናቸው። የሚሰሩት፤ በፖለቲካ ቁጥጥር ነው። ባንግላደሽን፤ ሃይቲንና ሌሎችን ስናይ፤ ለድሃው የቆመላቸው ወገን እናገኛለን፤ መንግስታትም ማነቆ አይሆኑም። ለባንግላደሽ ሞሃመድ ዩኑስ የተባለ በጎ አድራጊ አለ፤ የድሃውን ህይወት ለውጦታል፤ ወደ መካከለኛ መደብ አሸጋግሮታል። አሁን፤ የሃገሩን ድሃ ከረዳ በኋላ ወደ ሃይቲ ዙሯል፤ ድህነት “ለአለም ህዝብ በሙሉ አሳፋሪና አደገኛ ነው” ይላል።

የሃይቲ ድሃወች የመበደር አቅም እየተሻሻለ ነው፤ እንዴት? ልክ እንደ ኢትዮጵያ፣ አብዛኛው የሃይቲ ህዝብ ድሃ ነው። ይሰደዳል፤ ሃያ በመቶ (20 percent of Haiti’s income) የሚሆነው የሃይቲ ገቢ የሚመጣው ከውጭ የሃይቲ ተወላጆች ከሚልኩት የውጭ ምንዛሬ ነው። እኛ ኢትዮጵያዊያን በአመት፤ ቢያንስ US$ 3.5 billion ወደ ኢትዮጵያ እንልካለን። ቢያንስ፤ አስር በመቶ (10 percent of Ethiopia’s national income comes from remittances sent through official channels) የሚሆነው ብሄራዊ ገቢ የሚገኘው ከውጭ ስደተኞች ከሚልኩት ገንዘብ ነው። ሆኖም፤ ይህ ገንዘብ የድሃውን ራስ የመቻል አቅም የዚህን ያህል አልለወጠውም። የወቅቱን ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር ለቁጠባ፤ አዲስ የንግድ ስራ ለመክፈት ወዘተ የሚውለው ዝቅተኛ ነው። በባንክ ሆነ በሌላ የሚላከው የውጭ ምንዛሬ ወደ ባንክ ይገባል ወይንም ከህግ ውጭ ወደ ሌላ ሃገር ይሄዳል። ለምሳሌ፤ ለመደበቅ እንዲያመች ብዙ “መቶ ሚልዮን ዶላር ወደ ማላየዚያ፤ ሆንግ ኮንግና ሌሎች የምስራቅ ኤዥያ አገሮች ባንኮች” መግባቱ ይነገራል። ሃገር ውስጥ የሚቀረው የውጭ ምንዛሬ የሚገባው ባንክ ነው። ባንኮች ገንዘቡን ወደ ብር ለውጠው ያበድሩታል። የሚያነጋግረው፤ ማበደራቸው ሳይሆን፤ ተበዳሪው ማነው የሚለው ነው። አላሙዲ ሆነ ሌላ ችሎታ፤ መያዣ፤ የፖለቲካ ስልጣን፤ የመንግስት ተባባሪ ባለስልጣን ወዳጅ ያለው ተበዳሪ የሚጠቀም መሆኑን የሚያሳዩ ብዙ ማስረጃወች አሉ፤ ተጠቃሚው ድሃውና መካከለኛ ገቢ ያለው ኢትዮጵያዊ ሳይሆን፤ ስልጣን ያላቸው፤ ከባለስጣኖች ጋር ቁርኘት ያላቸው ናቸው ለማለት እንችላለን። ስለሆነም፤ ብድርና የፖለቲካ ስልጣን የተያያዙ ናቸው። ስርአቱ እንደዚህ አድሏዊ ከሆነ፤ድሃውስ ብድር ከየት ያገኛል?

በባንግላደሽ፤ ሞሃመድ ዩኑስ የፈጠረው “የድሆች ባንክ”፤ በተለይ፤ ለባንግላደሽ ድሃ ሴቶች ብድር፤ ያለምንም መያዣ (Collateral) በመስጠት የብዙ ሚሊዮኖችን ህይወት ለውጦታል፤ ለዚህ ነው ዩኑስ፤ የታወቀውን የኖቤል የሰላም ሽልማት ያገኘው። ሁሉም ድሃ አገሮች እንደ ሃገር ወዳዱ ዩኑስ ተቆርቋሪ የላቸውም፤ ቢኖራቸውም መንግስቱ አምባገነን ከሆነ፤ ማነቆወችን ዘርግቶ አያሰራቸውም። የሃይቲ ድሃወች ከታላቁ የመሬት መንቀጥቀጥ በኋላ፤ እንደ ፕረዝደንት ክሊንተን ያሉ ተደማጭነት ያላቸው ወዳጆች አትርፏል። ስላተረፈም፤ የሃይቲ ባንኮች ለድሃወች አገልግሎት አለመስጠታቸውን የሚያውቀው፤ የአየርላንድ ተወላጅና ዲጅሴል የተባለው ኩባንያ ሊቀመንበር ስኮችያ የተባለውን የካናዳ ባንክ በመጠየቅ የሃይቲ ተወላጆች፤ ሞባይል ብቻ በመጠቀም ገንዘብ ከውጭ በቀጥታ ለሃይቲ ተወላጆች፤ በተልይ፤ ድሃወች እንዲልኩ አድርጓል። በማድረጉ፤ ድሃወችን ከባንኮችና ከመንግስት ቁጥጥር ነጻ አወጣቸው። በማህል ያለውን ደላላ አስወገደ። እንዳልኩት፤ የሃይቲ መንግስት ለሞባየል አጠቃቀም ፈቃድ ሰጥቷል፤ የኢትዮጵያ መንግስት፤ ይህ ከውጭ የሚላክ የገንዘብ ስርጭት ድሃውን ሊረዳ ቢችልም፤ ቁጥጥሩን ለማንሳት ፈቃደኛ መሆኑ ያጠራጥራል። ማንኛውንም የገንዘብ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ይሞክራል። ሆኖም፤ ሃይቲ የህይወት ለዋጭ የሆነው የቴክኖሎጅ አጠቃቅም፤ ኢትዮጵያም መሞከር አለበት። ድህነትን ለመቀነስ ያለው ጥቅም፤ በጣም የሚያበረታታ ነው።

በሃይቲ፤ በአንድ አመት ብቻ (2011) ስድስት ሚሊዮን የገንዘብ ዝውውር አገልግሎት ተካሂዷል፤ ተጠቃሚወች፤ ራሳቸውን የሚያስችሉ፤ መለስተኛ የአገግሎት፤ የምርት ስራወችን ማንቀሳቀስ ጀምረዋል። ቤት ለመስራት፤ ንጹህ ውሃ፤ ኤለክትሪክ፤ መጸዳጃ ለመግዛት አስችሏቸዋል። ከርስ በእርስ የመበዳደርን አቅም አጠንክሯል። የዩኑስ ወደ ሃይቲ ገብቶ አገልግሎት መስጠት ይህን ራስን የመቻል አቅም ግንባታ ያጠናክረዋል የሚል ግምት አለ።

የመበደር አቅምን ጥቅም ለማጤን፤ የነፍስ ወከፍ ገቢን ብቻ ማየት ይበቃል። ዘጠና በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የቀን ገቢው US$2:00 ነው፤ ኦክስፎርድ ዩንቨርስቲ ያወጣውን የ 2010-2011 ዘገባ ብንጠቀም፤ ስድሳ በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የቀን ገቢው በነፍስ ወከፍ ከUS$1.25 ያነሰ ነው። የአለም ባንክና ሌሎች ድርጅቶች ዘገባ የሚያሳየው የኢትዮጵያ የነፍስ ወከፍ ገቢ በአመት US $360-US$365 ደርሷል። ይህን ማወዳደር የምንችለው ከቦትስዋና ( በ1966 $70 የነበረው፤ በ 2011-2012 $14,00 የሆነው፤ ወይንም ከችሌ (2010-2011 $15,00 የሆነው)–እነዚህ አገሮች መካከለኛ ገቢ ደረጃ ላይ ደርሰዋል–ጋር ሳይሆን፤ ከሌሎች የሳሃራ በታች አፍሪካ አገሮች ጋር ነው። የእነዚህ አገሮች አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢ በአመት US$1,070 ደርሷል። ገቢው ዝቅተኛ ስለሆነ፤ አብዛኛው የኢትዮጵያ ድሃ ሕዝብ በባንክ የሚያስቀምጠው ገንዘብ የለውም። ኑሮው “ከእጅ ወደ አፍ” ስለሆነ፤ የሚጣጣረው የእለት ጉርሱን ለማግኘት እንጅ፤ ከገቢየ ቆጥቤ ወይንም ከባንክ ተበድሪ ኑሮየን አሻሽላለሁ የሚያሰኝ አይደለም። ለዚህ ነው፤ የሃይቲ ወይንም ተመሳሳይ የቁጠባና ከወለድ ነጻ የሆነ፤ ቢበዛ፤ ወለዱ ዝቅተኛ የሆነ የብድር ዘዴ የሚያስፈልገው። ልክ እንደ ሃይቲ፤ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ገቢያቸው ዝቅተኛ የሆነ ኢትዮጵያዊያን ሞባየል አላቸው።

መንግስት ቁጥጥር ባያደርግበት፤ ይህ ዘመናዊ የመገናኛ መሳሪያ እድል ከፋች ነው። በገጠር የሚኖሩ ምርት ያላቸው ገበሬወች የአየር ጠባይ፤ የምርት ዋጋ የሚከታተሉበት መሳሪያ እየሆነ ሂዷል። በአጠቃቀም ላይ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ክትትል ያደርግበታል፡፡ ይህ ቁጥጥር ከሃይቲ ይለየዋል። ልክ እንደ ኢትዮጵያ፤ የሃይቲ መንግስት በሙስና የተበከለ ቢሆንም፤ በመገናኛ ብዙሃን ላይ ገደብ አያደርግም። የኢትዮጵያ መንግስት በመገናኛ ብዙሃን፤ በተለይ በዘመናዊ መገናኛ ቴክኖሎጅ ላይ የሚያደርገው ስለላ፤ ቁጥጥርና ጫና የሚጎዳው ተቃዋሚ ድርጅቶችን ብቻ ሳይሆን፤ ድሃውንና ወጣቱን ትውልድ ነው። ይህ በደል፤ የሰብአዊ መብቶች፤ የኢኮኖሚና የማህረሰብ መብቶች አቀባ ፍጹም መሆኑን ያመለክታል። የሃገሪቱን ህገመንግስት፤ የተባበሩት መንግስታትን ደንቦች፤ የአፍሪካ አንድነትን መመሪያወችና ስምምነቶች በሙሉ ይጥሳል።

ገዥው ፓርቲ፤ በመገናኛ ቴክኖሎጅ ስርጭትና አጠቃቀም ላይ ስለላ፤ ቁጥጥር፤ ጫና እያደረገ፤ በውጭ የሚኖረውን አገር ወዳድ፤ “ገንዘብክን ላክ፤ ቤት ስራ” ፤ ወዘተ፤ ሌላ ውስጥ፤ በተለይ፤ መብቶችን ከሚመለከት፤ ጣልቃ አትግባ ይላል። የውጭ ምንዛሬውን እንጅ፤ ሃሳቡን፤ እውቀቱን አይፈልግም። የኢትዮጵያ ስደተኞች ለራሳቸው ጥቅም ከሚያውሉት በላይ፤ ለምሳሌ፤ ቤት መስራት። ከሁሉም የማይናቀው፤ አምስት ሚሊዮን ድሃ የነበሩ ወገናቸውን ከድህነት ነጻ አውጥተዋል፤ ድሃ የነበሩ፤ በልተው ያድራሉ፤ በመንግስት ወይንም በውጭ እርዳታ አይመኩም ፤ሰባ በመቶ የሚሆኑት ሞባይል አላቸው የሚል ግምት አለ። ሌሎች ሲደመሩበት፤ ብዙ ሚሊዪን የሚሆነው የከተማና የገጠር ድሃ ሞባይል አለው ማለት ነው። በ2012 አምሳ በመቶ የሚሆነው ከሳሃራ በታች የሚኖረው የአፍሪካ ህዝብ ሞባይል (Cell Phone) እንዳለው ይነገራል። የኢትዮጵያን ሕዝብ በሚመለከት፤ አስተማማኝ የሆነ ማስረጃ የለም፤ ግን ከሌሎች ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው የአፍሪካ አገሮች ጋር አይወዳደርም ለማለት ያስደፍራል።

አሳፋሪ፤ ጎታች፤ ኋላ ቀር የቴክኖሎጅ አመራር፤

የኢትዮጵያ መንግስት ዘመናዊ የመገናኛ ቴክኖሎጅ ያስገባው በአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ነበር። በዚያ ጊዜ ሁሉም የአፍሪካ አገሮች፤ ከላይበሪያ በስተቀር፤ የቅኝ ግዛቶች ነበሩ። የኢትዮጵያ የቴሌኮሙኒኬሽን መስሪያ ቤት ዘመናዊ ከሚባሉት ተቋሞች አንዱ ነበር። ዛሬ፤ በቅኝ ይገዙ የነበሩ፤ እንደ ኬንያ፤ እንደ ጋና፤ እንደ፤ እንደ ዛምቢያ፤ እንደ ናይጀሪያ ያሉ አገሮች ከኢትዮጵያ ቀድመው ሂደዋል። ይህ ሁኔታ፤ የህወሓት/ኢህአዴግን አመራር ሊያሳፍረው ይገባል። ዘመናዊ የመገናኛ ቴክኖሎጅ ከቻይና ገዝቶ፤ ለልማት፤ለአቅም ግንባታ በማድረግ ፋንታ፤ ለስለላ አውሎታል፤ ሌላው ቀርቶ የራሱን የፓርቲ አባላት ይሰልልበታል፤ ቴክኖሎጅው ከኢትዮጵያዊያን ቁጥጥር ውጭ አንዲሆን አድርጎታል፤ ኢትዮጵያዊያን ኑሯቸውን እንዳያሻሽሉበት፤ በአለም የማይታይ ጫና ያደርግበታል። እንደዚህ ያለ የቴክኖሎጅ አጠቃቀም፤ ለግለሰብ፤ ለህብረተሰብ ኑሮ ማሻሻያ ካልሆነ አገሪቱና ህብረተሰቡ ይጎዳሉ፤ የሌሎች አፍሪካዊያን መሳቂያ መሳለቂያ ሁነን እንቆያለን ማለት ነው።

በኢንተርኔት ስርጭት ሲታይ፤ አራት በመቶ የሚሆኑ የአፍሪካ ቤተሰቦች ኢንተርኔት አላቸው፤ የኢትዮጵያ ከአንድ ግማሽ በመቶ (.5%) በታች ነው። ጫና ያለበት አገዛዝ ውጤቱ እንደዚህ ነው። ይህ፤ ለህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ ሌላ አሳፋሪ መለኪያ ነው ለማለት ያስደፍራል። ሆኖም፤ የሞባይል ስርጭት አጠቃቀምን እንጅ፤ እድገትን ሊገታው አይችልም። በግልጽ የሚታየው፤ የጎንደር ጫማ አጽጅ (ጠራጊ)ሞባየል አለው፤ ታክሲ ነጆች፤ ገበሬወች፤ የጥቃቅን ሱቅ ባለቤቶች አላቸው፤ ብዙ የቤት ሰራተኞችም እንደዚሁ። ስለዚህ፤ ይህ የአቅም ግንባታ መሳሪያ እየተሰራጨ ነው ማለት ነው። ይህን የዘመናዊ ቴክኖሎጅ ስርጭት ገዥው ፓርቲ ሊቆጣጠረው አልቻለም።

እኛ ውጭ ያለነው መጠየቅ ያለብን፤ ዘመናዊ ቴክኖሎጅ ለነጻነት፤ ለእኩልነት፤ ለዲሞክራሲ፤ ለእድል ከፋችነት ጠቃሚ መሆኑን ከተረዳን፤ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው፤ ለድሃወች፤ ለወጣቶች፤ ምን አይነት የገንዘብ ቁጠባ፤ የብድር አሰራር ዘዴ ልናቀርብ እንችላለን የሚለውን ነው። ጠቃሚ የሆኑ፤ ድሃውን ከድህነት ነጻ የሚያወጡ ተግባሮችን መስራት ያለብን ለዚህ ጭምር ነው። በነጻነት፤ በዲሞክርሳዊ አገሮች የምንኖር ተቆርቋሪወች “እድገታዊ መንግስት” ያላደረገውን ለማድረግ መድፈር ተግባራችን መሆን አለበት፤ የኢትዮጵያ በመገናኛና ሌላ ተክኖሎጅ ወደኋላ መቅረት፤ ለሁላችንም ሃፍረት ነው። የኬንያንና የሃይቲን ምሳሌ ለማቅረብ የፈለግሁት ለዚህ ነው።

ኬንያ ድህነት ሲቀንስ ኢትዮጵያ አልቀነሰም፤

ሩቅ ሳንሄድ በኬንያ ሲካሄድ የቆየው የዘመናዊ መገናኛ ብዙሃን (The Economist calls it, a “technological boom”) እድገትና መስፋፋት የጀመረው በሞባየል ስርጭት ነው። ከኢትዮጵያ ጋር ሲወዳደር፤ በኬንያ የሞባየል ስርጭት 74 ሞባየል ለ100 ሰወች ሲሆን የቀረው የአፍሪካ አገሮች አማካይ 65 ለ100 ሰወች ነው፤ የኢትዮጵያ ከዚህ በጣም ዝቅ ይላል። የሚያስደንቀው፤ በሞባየል እድገትና ስርጭት፤ ኬንያ ከቻይና ስድሳ ዘጠኝ በመቶ ትበልጣለች። ሆኖም፤ ቻይና ያላትን የመሰለያ ቴክኖሎጅ ለህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት አቅርባለች። ኬንያ ከኢትዮጵያ የምትበልጥበት ምክንያት ግልጽ ነው። ለምን? በኢትዮጵያ፤ ስርጭቱን የሚቆጣጠረው መንግስት ስለሆነ፤ አስመጭና ላኪው በሞኖፖል (በጥቂት የህወሓት ደጋፊወች) ስለተያዘ፤ መንግስት ስርጭቱን ስለሚፈራው፤ የድሃው ገቢ ዝቅተኛ ስለሆነ፤ ወጣቱ ቴክኖሎጅ የማሻሻል እድሉ የተወስነ ስለሆነ ጭምር ነው። በኬንያ፤ የዚህ አይነት ቁጥጥር የለም። ስለዚህ ነው፤ በቴክኖሎጅ መሻሻል ኢትዮጵያ ከአለም አገሮች ዝቅተኛ የሆነችው። የኢትዮጵያ መንግስት ቴክኖሎጅን ይፈራል። ቴክኖሎጅ ካልተሻሻል፤ ከሃገሪቱ ባህልና የመፍጠር ችሎታ ጋር ካልተያያዘ፤ ቀጅና ሸማች እንጅ ፈጣሪና አሻሻይ (Innovator) ለመሆን አይቻልም። ለምን፤ የቴክኖሎጅ ፈጣሪና አሻሻይ ለመሆን ነጻነት ያስፈልጋል። የኬንያ ህዝብ፤ በተለይ ወጣቱ፤ ሞባየልን ለኢንተርኔት ስርጭትና ጥቅም አውሎታል። መንግስት አላገደውም፤ እንዲያውም ያበረታታዋል። ዘጠና ዘጠኝ በመቶ (99%) የሚሆነው የኢንተርኔት ተጠቃሚ አገልግሎት የሚያገኘው ከሞባይል ነው። ከአርባ ሚሊዮን ህዝብ፤ አስራ ሁለት ሚሊዮን በላይ ኢንተርኔት ይጠቀማል፤ መንግስት “ምን አየህ” ብሎ አይቆጣጠረውም። የዲሞክራሲ፤ የነጻነት ጥቅም እንደዚህ ይመስላል፤ ሁሉም በሃገሩ፤ ለሃገሩ ያገባዋል። ሁሉም በሃገሩ ይጠቀማል።

በኬንያ፤ ሁለቱን ዘመናዊ የቴክኖሎጅ ስርጭቶች (ሞባይልና ኢንተርኔት) አያይዟቸዋል፤ ስለሆነም፤ ዋጋውን ቀንሶታል ማለት ነው። ዋጋ ሲቀንስ፤ ስርጭት ይስፋፋል፤ ድሃው ይጠቀማል፤ ገቢው ያድጋል። የመካከለኛ መደቡ እየጨመረ ይሄዳል፤ አገር ፍትሃዊ ይሆናል። ይህ በኬንያ የሚሆነው ህይወት ለዋጭ የሆነ የቴክኖሎጅ አብዮት ለምን በኢትዮጵያ አይካሄድም? የህወሓት/ኢህአዴግ የበላዮች የዘመናዊ ቴክኖልጅን፤ በተለይ፤ የመገናኛ ብዙሃንን ስርጭት እንደ ካንሰር ይፈሩታል፤ ነጻነት ስለሚሰጥ፤ እውቀት ስለሚያሰራጭ። መንግስት የሚያየው ከፖለቲካ ስልጣን፤ ከጸረ-ግልጽነት፤ ከጸረ የህግ የበላይነት አንጻር እንጅ፤ ከእድገት፤ ከወጣቱ ትውልድ ፍላጎት፤ የመፍጠር ችሎታ አንጻር አይደለም። አልፎ አልፎ ለመረጣቸው ድጋፍ ቢሰጥም፤ በቁጥጥር እንጅ በግልጽ፤ በውድድር አይደለም። ቁጥጥር ያለበት ኢኮኖሚ ፍትሃዊ የማይሆነው ለዚህ ነው። ማን መጠቀም፤ ማን መጎዳት አለበት የሚለውን ከላይ እየመረጠ፤ “እየገመገመ” ስለሚወስን።

ኢኮኖሚስት (August, 2012) ባወጣው ትንተና፤ የኬንያ ወጣት ሴቶችና ወንዶች ለአንድ የቴክኖሎጅ እድገት ጅምር (Start Up) ቦታ ለማግኘት ሁለት መቶ ቡድኖች ተወዳድረዋል። ይህን ግልጽነት ያለው ውድድር ለማካሄድ ያስቻሉት ሶስት አንኳር ጉዳዮች አሉ። አንደኛ “የመንግስት ድጋፍ፤ ሁለተኛ፤ ከ2007 ጀምሮ የተካሄደው ሞባየል ተጠቅሞ ገንዘብ የማንቀስቀስ አገራዊ ለውጥ፤ (ኬንያ ከሃይቲ በፊት ጀምራ ነበር ማለት ነው)፤ሶስተኛ፤ መንግስት የፈቀደው፤ የውጭ ድርጅቶች የደገፉት፤ ከ2010 ጀምሮ ለምርምር፤ ሃሳብ ለመለዋወጥ፤ የቴክኖሎጅ አማራጮችን ለመፍጠር የተቋቋመው የቴክኖሎጅ ማእከል” መኖሩ ናቸው። የኬንያ ወጣቶችና መካከለኛ መደብ አባላት፤ ሞባየል ተጠቀመው ቁጠባ፤ ብድር፤ የትምህርት ቤት ክፍያ ወዘተ አገልግሎቶችን ከማስፋፋታቸው ባሻገር፤ አሁን በጋራና በግለሰብ፤ በሃገራቸው ኢንቬስት የማድረግ አቅምን አስፋፍተዋል። የኬንያን የቴክኖሎጅ አማራጭ ከሌሎች አገሮች የሚለየው፤ የመጀመሪያ ትኩረቱ የሃገሪቱን ጊዜአዊ ችግሮች ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ነው። ለምሳሌ፤ አገልግሎቱ የዶሮ አርቢወች ምርታቸውን በዘመናዊ ዘዴ እንዲከታተሉ፤ ለገበያ እንዲያቀርቡ ያደርጋል፤ የማሳይ (በኬንያ የታወቁ ብሄረሰብ አባላት) ከብት አርቢወች የዚህ ቴክኖሎጅ ተጠቃሚወች ሁነዋል። ሞባይል በመጠቀም ከሸማቾች ጋር በቀጥታ ይገናኛሉ፤ እርስ በርሳቸው ሰለ አየር ጠባይ፤ ሰለምርት፤ ሰለ ገበያ እወቀት ያግኛሉ፤ ስለኑሮ ይወያያሉ። የኦሞ ሸለቆ፤ ወይንም የአፋር ዘላን ይህን ለማድረግ አልቻለም።

በፖለቲካና በባህል ያለው ለውጥ አስደናቂ ነው። ኬንያ በብሄር፤ ብሄረሰብ ልዩነቶች፤ በአድሎና በሙስና የታወቀች ቢሆንም፤ የቴክኖሎጅ ለውጥ ያለውን ልዩነት እያጠፋው ነው። ወጣቱ ትውልድ ያተኮረው ዘላቂነትና ፍትሃዊ ከሆነ እድገት ላይ ነው። ቴክኖሎጅው የፖለቲካውን፤ የኢኮኖሚውን፤ የማህበረሰቡን የጨዋታ ሜዳ እያሰፋፋው፤ እኩልነትን ጥልቀት እየሰጠው፤ ልዩነቶችን እያጠበባቸው፤ አገራዊነትን (ኬንያዊነትን) እያጠናከረው ነው። ቶክኖሎጅው “አንተ ማሳይ ወይንም ሉኦ ነህ” አይልም። ለሁሉም ይቀርባል፤ ሁሉን ተሳታፊ ያደርጋል። ኬንያዊያን ወጣቶች “እኔ ኪኩዩ፤ እኔ ሉኦ፤ እኔ ማሳይ” ከማለት ተሻግረው፤ “እኛ ኬንያዊያን ወደ ማለት” እየደረሱ ነው። ረጅም ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ ወደኋላ እየተጎተተች ነው። የወደፊቱ እድል የሚወሰነው እንደዚህ ባለ እኩልነትን፤ ፍትህን በሚያስተናግድ የቴክኖሎጅ አብዮት መሆኑን እያሳዩ ነው። በጋራ እየሰሩ፤ የጋራ ችግሮችን እየፈቱ ነው። ይህ የኬንያዊያን በሃገር ላይ የማተኮር ጥረት፤ ከጥገኝነት ያድናል የሚል ግምት አለኝ። ለቴክኖጅው መስፋፋት ዋና አስተዋጾ ያደረገው የመገናኛ ብዙሃን ሚና ነው።

እንደገና የፕሪስ ነጻነት ወሳኝነት፤

የኢትዮጵያን ሁኔታ ከኬንያና ከሃይቲ ለየት የሚያደርገው፤ የገዥው ፓርቲ በመገናኛ ብዙሃን ቴክኖሎጅ፤ ስርጭትና አጠቃቀም ላይ የሚያደርገው ፍጽማዊ ቁጥጥር ነው። ገዥው ፓርቲ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባለቤትና ዋና ተቆጣጣሪ በመሆኑ፤ ስርጭትን ያግባል፤ በተጠቃሚው ላይ ስለላ ያካሂዳል፤ ከውጭ የሚመጣውን ሁሉ ግንኙነት ይከታተላ፤ ኬንያና ሃይቲ የዚህ አይነት ችግር የለም። ይህ ከድህነት ነጻ ለማውጣት የሚያስችል ቴክኖሎጅ ቁጥጥር፤ በአሁኑ ዘመን ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም እያልን፤ ለአለም ህብረተሰብ፤ በተለይ፤ ለአበዳሪ ድርጅቶች፤ ለክሊንቶን፤ ለቢል ጌትስ፤ ጆርጅ ለሶሮስ፤ ለበጎ አድራጊ ድርጅቶች፤ ለአሜሪካ፤ ለእንግሊዝ፤ ለአውሮፓ የጋራ ገበያ፤ ለጃፓን፤ ለአውስትራሊያ፤ ወዘተ መንግስታት ማስረዳት ያለብን እኛው ነን። ቴክኖሎጅው በኬንያ ዘላቂነትና ፍትሃዊ የሆኑ ለውጦችን ለአሁኑና ለወደፊቱ ትውልድ እያበረከተ ከሄደ፤ በኢትዮጵያ መታገዱ፤ ለህብረተሰቡ በሙሉ፤ በተለይ ለወጣቱና ለድሃው ማነቆ ሁኗል ማለት ይኖርብናል። ዘመናዊ የመገናኛ ቴክኖሎጅ ስርጭት የሀብረተሰቡን ህይወት የሚለውጠው መሆኑን አሳይቻለሁ። (It is the single most important game changer today)። ከላይ ወደታች የሆነውን የህወሓት/ኢህአዴግ የቁጥጥር ኢኮኖሚ አመራር ለግለስብና ለህብረተሰቡ ለማድረግ የማይችለውን ያደርጋል። ገበያውን ዲሞክራዊ፤ ተሳታፏዊ ያደርገዋል። ቀስ በቀስ፤ አገራዊነትን ያጠናክራል፤ ገበያውን ተወዳዳሪ ያደርገዋል፤ ያልነበሩ አድሎችን ይከፍታል። ሃላፊነትን፤ ባለቤትነትን ያጠናክራል። የሴቶችን እኩልነት እውን ያደርጋል። ስደትን ይቀንሳል፤ ውድድርን ያጠነክራል።

በኬንያ እንዳየነው፤ የሞባየል ቴሌፎን፤ የኢንተርኔት፤ የዩቱብ፤ የትዊተር (Social Media) ስርጭትና አጠቃቀም በቀጥታ ከፕሬስ ነጻነት ጋር ግንኙነት አለው። ኬንያ፤ የመንግስት ቁጥጥርን ችግር ፈታለች። በኢትዮጵያ መጀመሪያ መፈታት ያለበት ችግር የመገናኛ ብዙሃን ሙሉ ቁጥጥር ማነቆነት መወገድ ነው። ገደቡ የሚጎዳው የዲሞክራሳዊ ስርአት ግንባታን ብቻ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያ ድሃወች፤ወጣቶች፤ የገንዘብ ቁጠባ፤ የብድር፤ ወዘተ ጥቅም እንዳያገኙ ማድረጉ ነው ብለን ማስረዳት አለብን። አበዳሪወች ይህን አያውቁም ማለቴ አይደለም፤ ያውቃሉ። መንግስቱን ለማስቀየም ስለማይፈልጉ፤ ገደባውን በግልጽ “አያወግዙም።” ከብዙ ቢሊዮን ብድርና እርዳታ የበለጠ ወጣቱን፤ ድሃውን ለማጎልመስ፤ ራሱን የሚችልበትን ዘመናዊ ዘዴ መፍቀድ፤ ማቅረብ፤ ማስተማር፤ አስፈላጊ መሆኑን ማሳመን አለብን፤ ፈቃደኛ ከሆንን፤ እንችላለን። የኢትዮጵያ መንግስት ድህነትን ለማጥፋት ወስኛለሁ ብሎ ካመነ፤ የቴክኖሎጅ ስርጭት ማገቡን በአስቸኳይ ማቆም አለበት። የማገቡ ትርጉም ቀላል ነው፤ ከዘላቂነትና ፍትሃዊ እድገት የበለጠ፤ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነትን መርጧል ማለት ነው።

የኢትዮጵያ ድህነትና የቴክኖሎጅ ኋላ ቀርነት በቀጥታ የአገዛዙ መጥፎነት፤ አድሏዊነትና ተቆጣጣሪነት መጸብራቅ ናቸው። የፕሬስ ነጻነት ከኢኮኖሚው ኢ-ፍትሃዊነት ጋር ተያይዞ ሲቀርብ አደጋው እንዴት እየባሰ እንደሄደ ያሳያል። ይህ ሁኔታ ከቀጠለ፤ ሰላም አይኖርም። ድህነት ህገወጥነት፤ ሽብርተኝነት፤ ስደት፤ ተስፋ ቢስነት፤ የባህል መበላሸት፤ ሙስና፤ የገንዘብ ሽሽት ይቀጥላሉ። ኑሮው አስቸጋሪ ስለሆነ፤ ግለሰቡ፤ ለሃገር ማሰብ ቀርቶ፤ ለቅርብ ቤተሰብና ዘመድ ለማሰብ እይችልም። ለመንግስት የሚሰራው፤ “እንጀራ ለመብላት” እንጅ ሃገርን፤ ወገንን በቅንነት ለማገልገል አይሆንም። ተቀጣሪው ይህች እንጀራ እንዳትቀርበት ከፈለገ፤ ሰጥ ለበጥ ብሎ ይገዛል፤ ውጣ ሲሉት ይወጣል፤ ግባ ሲሉት ይገባል፤ ተሰድድ ሲሉት ይሰደዳል፡፡ የዚህን የተዛባ የህብረተሳባዊና የኢኮኖሚ አሰራር ውጤት ለማጤን፤ አንባቢወች ከዚህ በታች የቀረቡትን የሂሳብ ማስረጃወች በአእምሯቸው እንዲቀርጹልኝ እጠይቃለሁ።

ሙስና “ነቀርሳ” ሁኗል፤

ማስረጃወቹ ያስፈለጉበት ምክንያት፤ ከሌሎች በፍጥነት እድገት ከሚያሳዩ የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲወዳደር፤ የኢትዮጵያ እድገት የተዛባ መሆኑን፤ አድሏዊይነት የኑሮ ልዩነትን የሰማይና የምድር ያህል እያስፋፋው መሄዱን ለማሳየት ነው። የመዛባቱ ዋና መነሻ፤ የአንድ ፓርቲ የበላይነት ለኪራይ ሰብሳቢነት እንዴት እንደጠቀመ ለማሳየት ጭምር ነው። የተዛባው የእድገት ውጤት እንዴት አደገኛና ለአደጋ የተዳረገ ህብረተሰብ እነደፈጠረ ያመለክታል። ከሁሉም በላይ አደጋውን የሚገልጸው፤ በአጭር ጊዜ፤ ከዜሮ ተነስተው የፓርቲው የበላዮች፤ ቤተሰቦች፤ የቅርብ ወዳጆችና ደጋፊወች በአለም ተወዳዳሪ የሌለው ከፖለቲካ ስልጣን ጋር በቀጥታ የተያያዘ ሃቭት ማከማቸታቸው ነው። የፖለቲካ ስልጣን መቆየት እንዴት ትርፍ እንደሚያስገኝ አመልካች ነው። በአንጻሩ፤ የመካከለኛ መደቡና ዘጠና በመቶ የሚሆነው ኢትዮጵያዊ የእለት ጉርስ ለማግኘት ጉዞው የማይወጣ ተራራ ሁኖበታል። የህወሓት/ኢህአዴግ “አስደናቂ እድገታዊ መንግስት” የነፍስ ወከፍ ገቢን የድህነት ኑሮን ለዋጭ ወደሚያደርስ ደረጃ አላሸጋገረውም፡፡ ራቅ ብሎ ለሚመለከተው፤ የመንግስቱ የበላዮች “ድህነት ለቁጥጥር ያመቻል” ብለው የወሰኑ ይመስላል፤ ከኬንያ ጋር ያወዳደርኩት ለዚህ ነው። በቅኝ ግዛት የነበሩ፤ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊያን ይደነቁ የነበሩ አገሮች ኢትዮጵያን የቀደሙ መሆናቸውን በኬንያ ምሳሌ አቅርቤዋለሁ። ወደፊትም በማስረጃ የተደገፉ ተከታታይ ፖሊሲ ነክ ትንተናወችን አቀርባለሁ።

የውጭ እርዳታው የት እየሄደ ነው?

እትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች ከፍተኛውን እርዳታ የምታገኝ ከሆነ– አሁን በአመት አራት ቢሊዮን ዶላር ደርሷል–እርዳታው የድሃውን ህይወት ለመለወጥ አልቻለም ማለት ነው። ይህ አያስገርምም። ቴክኖሎጅ ካለመስፋፋቱና የፕሬስ ነጻነት ከመከልከሉ በላይ፤ ሙስና፤ ከህግ ውጭ አገር ለቆ የሚሸሸው ገንዘብ አገሪቱን እያደማት ነው። Transparency International እና፤ Global Financial Integrity (GFI) በተደጋጋሚ ባደረጉት ዘገባ፤ ኢትዮጵያ ሙስና ከበከሏቸው አገሮች መካከል ከፍተኛ ደረጃ ይዛ ትጓዛለች። GFI ባደረገው ጥናት በ2009 ብቻ፤ $3.26 billion ከህግ ውጭ እንደጠፋ ያሳያል። ከ2000-2009 የተሰረቀና ከህግ ውጭ ከኢትዮጵያ የወጣው ወደ $12 billion ተገምቷል። በሙስና የሚሰረቀው እያደገ ሂዶ፤ በ2009 ከእጥፍ በላይ አድጓል፤ አሁንም እያደገ መሄዱን የውስጥና የውጭ ተመልካቾች ይናገራሉ። በእርዳታም ሆነ በንግድ የሚገኘው ገንዘብ ከተሰረቀና ከሃገር ከወጣ ለኢትዮጵያ እድገት አያገለግልም። የድሃውን ህይወት አይቀይርም። ከአፍሪካ አገሮች ጋር ሲመዛዘን የኢትዮጵያ የነፍስ ወከፍ ገቢ ዝቅተኛነት ለመንግስቱ አሳፋሪ የሚሆነው በዚህ ጭምር ነው። ማስረጃው እንደሚያሳየው፤ በአሁኑ ወቅት፤ የኢትዮጵያ የነፍስ ወከፍ ገቢ $350 ሲሆን፤ የቀሩት የአፍሪካ አገሮች አማካይ አመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ$1,070 ነው። ከሶስት ጊዜ በላይ ይበልጣል ማለት ነው። አይ ኤም ኤፍ ባወጣው ዘገቫ፤ የኬንያ የነፍስ ወከፍ ገቢ$1,700. ከዚህ ለመድረስ፤ በኢትዮጵያ፤ የሕዝብ ተሳትፎ፤ የግል ክፍሉ እድገት አስፈላጊ መሆኑን ያሳያል።

ገቢካላደገ፤ጤና ይታወካል፤ የወጣቶች የትምህርት እድል ይወሰናል፤ በልቶ ማደር ብርቅ ይሆናል። ክብር ይገፈፋል። ወጣት ሴቶች ወደማይፈልጉት ተግባር እንዲያመሩ ያስገድዳል። ወጣቶች ለማኝ፤ ሌባ፤ ነፍሰ ገዳይ፤ ወዘተ የሚሆኑት ወደው፤ መርጠው ሳይሆን የመኖር፤አለመኖር ጉዳይ ስላስገደዳቸው ነው።መንግስት፤ አማራጮችን አላቀረበም ወይንም ሌሎች እንዲያቀርቡ አልፈቀደም። ይህን ጎታች የፖሊሲ ቅርጽና ባህሪይ፤ በብራዚል፤ በቬኔዙየላ፤ በሃይቲ፤ በጃማካ፤ በድቡብ አፍሪካ አይቸዋለሁ። አሁን በኬንያ እንደሚታየው፤ ጥሩ የህይወት ለዋጭ አማራጭ ካላቸው፤ ወጣቶች፤ የመጀመሪያ ምርጫቸው ራሳቸውን መቻል ነው፤ እንደኛ ለመሆን ይችላሉ። የእስልምና ተከታይ ሶማሌ ወጣቶች፤ በባህር ላይ ዘረፋ (Piracy) የሚመርጡት፤ በሃገራቸው አል ሸባብን የሚደግፉት፤ሌላ የህይወት ለዋጭ አማራጭ ስለሌላቸው ጭምር ነው። የኢትዮጵያ ገዥ ፓርቲ ለማየት ያልቻለው ይህን የችግሮች ምንጭ ነው። በቅርቡ፤ በኤርትርያ ላይ የሚደረጉ ዘገባወችም የሚያሳዩት ተመሳሳይ ሁኔታወችን ነው። ኩሩ ኢትዮጵያንና ኤርትራዊያን ልጃገረዶች የሱዳን፤ የሳውዲ፤ የግብጽና ሌሎች ቱሪስቶች ፍላጎትን ለማሟላት የሚገደዱት መርጠው አይደለም። አዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች የሚጎበኝ ግለሰብ የሚያየው አሰቃቂ፤ ክብር ገፋፊ የጾታ ንግድና ግንኙነት ሸራቶን፤ ሂልቶን፤ ወዘተ የሚካሄደው ድህነት፤ ተስፋ መቁረጥ ስላለ ነው። ኩሩ ወጣት ሴቶችን ለዚህ የዳረጋቸው አገዛዙ ሌላ አማራጭ ለማቅረብ ስላልቻለ ነው።

እኩልነት፤ የህግ የበላይነት በሌለበት አገዛዝ፤ ሴቶች መብታቸውን ለማስከበር አይችሉም። ሌላው ቀርቶ፤ ለመብታቸው ጥያቄም ለማቀረብ አይችሉም። ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረገ ህልም ነው። ከውጭ የሚመጣ ገንዘብ ተጠቅመው፤ እንደልባቸው፤ ጉቦ ሳይከፍሉ፤ ራሳቸውን የሚችሉበት ተቋም ለማቋቋም አይችሉም። ከላይ “እንባ ጠባቂ” ወገን ያስፈልጋል፤ የኢኮኖሚው መሥክ ዝግ የሆነ፤ ከላይ ወደታች የሚወሰን አገዛዝ ውጤቱ እንደዚህ ነው። ታማኝነት፤ አጎብዳጅነት፤ የፓርቲ ወይንም የብሄር አባልነት/ታማኝነት ይጠይቃል። የኢኮኖሚው ስርአት ዲሞክራሳዊይና ተሳትፏዊይ አይደለም የምለው ለዚህ ነው። አድሎውን የሚያሳዩ ብዙ ምሳሌወች ለመስጠት ይቻላል። ታማኝ የሆነ የትግራይ ተወላጅና የህወሓት ደጋፊ ጎንደር እንደልቡ የትርፍ ስራ ይሰረል፤ ጎንደሬው መቀሌ ልስራ፤ ልወዳደር ቢል “የታባትህ” ይባላል። አመራሩ የሚያመጣውን መቃቃር ፈጽሞ ረስቶታል፤ ወይንም፤ ንቆታል። እንደዚህ አድሏዊ በሆነ ስርአት የነፍስ ወከፍ ገቢ እንደ ኤሊ ይጎተታል፤ እንደ ምስራቅ ኤስያ፤ እንደ ቦትስውና በፍጥነት ለማደግ አይችልም። በሁለተኛው ሰንጠረጅ እንደሚታየው ገቢና ሃብት የተጠራቀመው (Concentration of wealth and incomes) ከላይ ነው። አሳፋሪ የሆነ የነፍስ ወከፍ ገቢ ልዩነት የሚታየውም የእድል መስኩ ዝግ ስለሆነ ነው። ገቢ ያደገው ከላይ ላሉ ባልስልጣኖች፤ ቤተሰቦቻቸው፤ የቅርብ ወዳጆችና ደጋፊወቻቸ መሆኑ በምንም አያጠራጥርም። እድገቱ ለማን እንደሆነ፤ ካልተለወጠ ለማን እንድሚሆን ያሳያል።ይህ ሲባል፤ ከህወሓት/ኢህአዴግ ውጭ ሙስና፤ ስርቆት፤ ከህግ ውጭ የገንዘብ ሽሽት የለም ማለቴ አይደለም፤ አለ። ለዚህ የስግብግብነት፤ የዘራፊነት፤ የስርቆት፤ የጮሌነት፤ የሙስና ባህል ዋናው ተጠያቂ ህብረተሰቡ አይደለም፤ የህወሓት/ኢህአዴግ ባለስልጣኖች ናቸው። በቅርቡ፤ የስዊትዘርላንድ መንግስትና ባንኮች፤ በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚታሰብ ገንዘብ ለቱኒዥያ፤ ለግብጽ፤ ለሊብያ ህዝብ፤ ከዚህ በፊት ለፔሩ፤ ለፊሊፒንስ፤ ለሜክሲኮ፤ ለካዛኪስታን፤ ለናይጀሪያ የመለሱት፤ በስልጣን ብልግና የተገኘ መሆኑን ስላወቁ ነው።

የነፍስ ወከፍ ገቢ ዝቅተኛነት የሆነበት አንዱ ምክንያት ፤ የገቢና ሃብት ክምችት፤ መንሰኤና ስርጭት በጥቂቶች ከላይ ስለተያዘ ነው። በአይን ቢታይ ኖሮ፤ ስርጭቱ የአክሱምን የኦብሊስክ ሃውልት ወይንም የግብጽን ፒራሚድ ይመስላል። ስለሆነም፤ የኢትዮጵያን የገቢና የሃቭት ስብስብና ክምችት የፒራሚድ ካፒታሊዝም ብሎ መጥራት ያስችላል። የፖለቲካ ስልጣን ያለው ገቢውን በተለያየ መንገድ የሚያሳድግበት ዘዴ እንዳፈር ነው። ከዚህ በፊት በማስረጃ አቅርቤዋለሁ።

የዚህ ፒራሚድ ካፒታሊዝም አሰራር ቱኒዚያ፤ ሊብያ፤ ግብጽ፤ የመን፤ ሶሪያ፤ ፊሊፒንስ (በማርቆስ ጊዜ)፤ ናይጀሪያ ለብዙ አስርት አመታት፤ አንጎላ፤ ኬንያ (በተለይ በፕሪዝደንት ሞይ ጊዜ) ወዘተ ታይቷል። ብዙ ተመራማሪወች በጽሁፍ አቅርበውታል። የኢትዮጵያው ከእነዚህ አይለይም፤ የሚለይበት ቢኖር፤ የሚሸሸው ገንዘብ እረቂቅነት፤ ወደ ምስራቅ ኤዥያ መላኩ ወዘተ ናቸው።

ፒራሚድ ካፒታሊዝም በተግባር

ፒራሚድ ካፒታሊዝም ያልኩበትን ምክንያቶች ላቅርብ። የፖለቲካ ስልጣን ለገቢና ለሃብት ማካበት መሳሪያ ነው። የአፍሪካ አገሮች ታሪክ ይህን በግልጽ ያሳይ ነበር፤ አንዳንድ አገሮች ለውጥ እያሳዩ ነው፤ አብዝኛወቹ አሁንም የፖለቲካ ስልጣንን ለግል፤ ለቤተሰብ፤ ለወዳጅ፤ ለደጋፊ የሃብት ክምችትና ሽሽት ይጠቀሙበታል። ኢትዮጵያ ዋና ምስክር ናት። የአምባገነን አገዛዝ አድሏዊ መሆኑን ታሳያለች። በአጠቃላይ፤ ስርአቱ ለአድሎ፤ ለማጭበርበር፤ ለሙስና አመች መሆኑን ያሳያል፤ ችግሮቹን ለማጠቃለል፤

አንደኛ፤ የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት አዲስ ዝና ያገኘው “እድገታዊ” የተባለውን አገዛዝ ለኪራይ ሰብሳቢነት በግልጽና በድብቅ መጠቀሙ ነው። ለዚህ ዋና ምሳሌ፤ የኢኮኖሚውን የበላይነት (Pillars of the National Economy) የያዘው ማን እንደሆነ ማየት ነው። ከፒራሚዱ ቁንጮ ላይ ቁብ ያለው፤ በብዙ ቢልዮን የሚታሰብ ብርና የውጭ ምንዛሬ የሚያሽከረክረው ድሃው፤ ወጣቱ፤ መካከለኛ መደብ አይደለም። አድሏዊ ካፒታሊዝም (Crony Capitalism)፤ የፖለቲካ ስልጣንን ተጠቅሞ በአለፉት ሃያ አንድ አመታት ያከማቸው የሃብትና የገቢ ምልክት ነው። ተጠቃሜወች፤ በትምህርት ቤት፤ በፖለቲካ ትምህርት፤ በልዩ ልዩ የመንግስትና የግል ተቋሞች የጠነከረ ግንኙነት እየፈጠሩ፤ “ጀርባየን እከክልኝ፤ የአንተንም አክልሃልሁ፤ ምስጢራችን አታውጣ፤ ያንተን ምስጢር እጠብቃለሁ” በሚል በተያያዘ የጥቅም ግንኙነት የተፈጠረ የሃቭት ክምችት ነው። የፓርቲው ትምህርት ቤት የሚያጠናክረው ይህን አመለካከት ነው። ግምገማ ተብሎ የሚካሄደውም፤ በውስጡ ታማኞችን ለመገምገም፤ ጸረ- ህወሓት/ኢሃአዴግ የሆኑትን ለማስወጣት ነው። በዚህ ግምገማ፤ ዋጋ የሚሰጠው ለችሎታ፤ ሃገርንና ሕዝብን በቅንነት ለማገልገል ሳይሆን፤ ለፓርቲና ለብሄር ታማኝነትን ነው። ለግል ጥቅም ነው። ሃገሪቱን በወሳኝነት ለማስተዳደር የሚመረጡት በህወሓት/ኢህአዴግ የበላዮች ሲሆን፤ ተደጋጋፊ የጥቅም ግንኙነት (formal networking) ባህል፤ ልምድና አሰራር ከታች ወደላይ፤ ከጎን፤ ከላይ ወደታች (Integrated and Complementary) በሆነ ብልሃት ነው። ስለሆነም፤ ስርአቱ ከጅምሩ አድሉዊ ነው። እድገት በችሎታ የማይሆንበት ለዚህ ነው። ልክ የቻይናን አገዛዝ ይመስላል። የቻይና ኢኮኖሚ ማደጉ አያከራክርም፤ ሆኖም፤ ግልጽነት፤ ሃላፊነት አያጠናክርም። ቻይናወች የዚህን መሰል በጥቅም የተመሰረተ አመራር ጓአንክሲ(guanxi) ይሉታል፤ “የእርስ በእርስ ጥቅም መከፋፈል፤ ውለታ፤ እድገት፤ ብድር፤ ወዘተ የማግኘት መዋቅር” ማለት ነው። ከህግ ውጭ፤ ያለብዙ ድካምና ጥረት በጉቦ፤ በሙስና ሃቭት የሚገኘው በዚህ ዘዴ ነው። ህወሓት/ኢህአዴግ ጥሩ ተማሪ ሁኖ ይጠቀምበታል።

ሁለተኛ፤ አምባ ገነናዊ የፖለቲካ ስርአት ለመንግስትና ለፓርቲው የኢኮኖሚ አመራር የበላይነት ይሰጣል፤ ውድድርን ያግባል። ሙስና እኒዲወገድ አይፈልግም። የመንግስትና የግል የኢኮኖሚ ግንኙነትን በግልጽ አያስቀምጥም። አምባገነናዊ የፖለቲካ አገዛዝ፤ አምባገነናዊ ኢኮኖሚ የሚፈጥረው ለዘላቂና ፍትሃዊ እድገት የማይሆንበት ዋና ምክንያት ለዚህ ነው። የሚፈልገው ግንኙነት የበላይነትና የበታችነት፤ አዛዥና ታዛዥ የሆነ ነው። እንደዚህ ከሆነ፤ ተራው ህዝብ ቀርቶ፤ የተማረውና መካከለኛው መደብ በውሳኔ ላይ (Policy and Decision-making) ምንም ሚና የላቸውም። የመሰረተ ልማት ስራ ለመተግበር፤ ማን ጨረታ እንደሚያገኝ፤ ማን እንደሚገደብ የሚወሰነው የፖለቲካው አካል ነው። ለምን ብንል፤ የሚገኘው የግል ትርፍ (ኪራይ ሰብሳቢነትና ጉቦ) ያየለ፤ አመች፤ ስለሆነ ስለሆነ፤ የውጭ ምንዛሬ በድብቅ ለማውጣት ለማውጣት አያስቸግርም። ለሃገሪቱና ሕዝቧ ተቆርቋሪ የለም ማለት ነው። በብድርም በኩል ሲታይ፤ ወሳኙ አካል የፖለቲካው ነው እንጅ ገበያውና የተበዳሪው ፍላጎት አይደለም። የፖለቲካ አካሉ፤ ድጎማ የሚሰጠው፤ በአንዱ ላይ ታክስ ጨምሮ በሌላው ቀለል የሚያደርግው፤ ከፈለገ ፈጽሞ የግል ሃቭት የለህም ለማለት የሚችለው፤ መሬት ለምርጥ ደጋፊወች የሚለግሰው፤ አንዳንድ ግለሰቦችና ድርጅቶች ፈጽሞ ከጉምሩክ ፍተሻና ቀረጥ ነጻ የሚሆኑት ሁሉ የፖለቲካ ውሳኔ ነው። አድሎ የሚጠናከረው ለዚህ ነው። መገናኛ ብዙሃንን ማገብ እውነተኛው ዜና ለሕዝቡ እንዳይደርስ ይረዳል።

ሶስተኛ፤ ህወሓት/ኢህአዴግ ላለፉት ሃያ አንድ አመታት፤ የፖለቲካ ስልጣን የበላይነትን ተጠቅሞ፤ የመንግስት፤ የፓርቲ፤ በፓርቲው የተፈጠሩ የመንግስት ያልሆኑ ድርጅቶችን፤ ምርጥና ታማኝ ግለሰቦችን የኢኮኖሚ የበላይ ማድረግ ጉዳቱ እጅግ የሚያስፈራ መሆኑን የፒራሚድ ካፒታሊዝም አቀራረብ ይገልጸዋል። በደሉ ከዚህ በላይ መሆኑን በልዩ ልዩ ትንተናወች ላይ አሳይቻለሁ። በዚህ ክፍል የማቀርበው፤ የኢኮኖሚው አመራርና አሰራር በግልጽ አድሏዊ (Unfair and non-transparent regulatory framework) መሆኑን፤ የሃብት ክምችት ከላይ ያለውን እያጠነከረ መሄዱን፤ አገር ውስጥ ሊወዳደሩ የሚችሉ ግለሰቦች፤ በጫናው የሚሰቃዩ መሆኑን፤ ጥቃቅን የሆኑ፤ በኢትዮጵያዊያን የተቋቋሙ የአምራች ሆነ የአገልግሎት ድርጅቶች የበላይነት ካላቸው ጋር (State, Party, Endowment and favored individual monopolies) ለመወዳደር የማይችሉ መሆናቸን ነው። የአሁኑ ስርአት ከቀጠለ፤ ሚዛነ ቢስ (Uneven and Unbalanced) ሁኖ ይቆያል፤ የነፍስ ወከፍ ገቢ በሚጠበቀው ደረጃ ሊያድግ አይችልም፤ የስራ እድል ለብዙ ሚሊዮን ወጣቶች ለመክፈት ህልም ይሆናል፤ የመካከለኛው መደብ ከማደግ ይልቅ በዋጋ ግፍሸት፤ እየቆረቆዘ ይሄዳል። ብድር፤ መሬትና ሌሎች ግብአቶች (Inputs) ለማግኘት ያለው ችግር ይባባሳል። ስርቆት፤ ሙስና፤ አድሎ፤ ይቀጥላል። ስለሆነም፤ ይህን የበላይነት የያዙት ተቋሞች ለግል ዘርፉ ኢኮኖሚው እድገት ማነቆ ሁነዋል።
አራተኛ፤ የፈለገው ያህል ብድር፤ ርዳታና ሌላ ድጎማ ቢቀጥል፤ ችግሮቹ አይፈቱም። ህወሓት/ኢህአዴግ ርዳታውን ለፖለቲካ ጫና መሳሪያ፤ ለኪራይ መሰብሰቢያ፤ ለግል ጥቅም አድርጎታል፤ አሁንም ያደርገዋል። ከምርጫ ዘጠና ሰባት በኋላ፤ አለም ባንክ በብድርና በስጦታ የሚገኝ ድጋፍ ለድሃው ህብረተሰብ እንዲውል የመሰረተ አገልግሎት ፕሮግራም (Protection of Basic Services, conceived by my good friend James Adams, Vice President) ፈጠረ። ከግቡ ለመድረስ፤ ሌሎች አበዳሪወችንና ለጋሶችን በዚህ ፕሮግራም እንዲሳተፉ ተደረገ። ከአስራ ሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ለፕሮግራሙ ተመደበ፤ አለም ባንክ የሰጠው ሁለት ቢሊዮን ዶላር ነው። ይህ ፕሮግራም በቀጥታ ለህዝቡ አገልግሎቶ ቢሰጥ ኖሮ ድህነት ይቀንስ ነበር፤ አልሆነም፤ ለፖለቲካ ለበላይነት ግን አገልግሏል። ከመንግስት ቁጥጥር ነጻ የሆነ( Independent Oversight) ተቋም ስለሌለ፤ እንደ ሌላው ርዳታ፤ ጥቅሙ ምን እንደሆነ፤ ጉዳቱ ምን እንደሆነ፤ ምን ያህል ገንዘብ በሙስና እንደጠፋ፤ ርዳታው የተባለውን ውጤት እንዳስገኘ ወይን እንዳላስገኘ አይታወቅም። የነጻ ፕሬስ፤ የነጻ ማህረሰብ ተቋም አለመኖሩ ጉዳዩን አባብሶታል።

ምንም እንኳን Transparency International and Global Financial Integrity የተባሉት የመንግስት ያልሆኑ ድርጅቶች በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ያለውን ሙስናና ከህግ ውጭ የሚጎርፍ ብዙ ቢሊዮን ዶላር አደጋ ቢያመለክቱም፤ አበዳሪ ድርጅቶች አያገባንም ሲሉ ቆይተዋል። ሆኖም፤ የሙስንውና ከህግ ውጭ የሚጎርፈው ገንዘብ ብዛት በተደጋጋሚ ለአለም ህብረተሰብ እየተሰራጨ ሲሄድ መከታተልና መመራመር ይጀምራሉ። ለራሳቸው ዝና ይፈራሉ (Reputational Risk) ። በቅርቡ፤ “ሁሉን አቀፍ ኢንተርናሽናል” የተባለ ቲንክ ታንክ፤ በአኟክ ህብረተሰብ አባላት ቀስቃሽነት ያደረገው እንቅስቃሴ የሚያበረታታ ነው።

ሙስና “ካንሰር” ነው ብለው የሰየሙት የዱሮው የአለም ባንክ ፕረዝደንት፤ ጀምስ ውልፈንሶህን፤ ካቋቋሟቸው ከአለም ባንክ ባለስልጣኖች ቁጥጥር ነጻ ከሆኑ ድርጅቶች መካከል የምርምሩ ኢንስፔክሽን ፓነል (Inspection Panel) ዋናው ነው። ይህ ድርጅት፤ በአለም የታወቁ ባለሙያወች ያሉበት፤ በትንተናውና ዘገባው እንከን የሌለበት መሆኑን የታወቁ ምሁራን ጽፈውበታል፤ ግን ቀስቃሽ ያስፈልገዋል። በአኝዋክ ህብረተሰብ አባላት አማካኝነት፤ ሁሉን አቀፍ ኢንተርናሽናል ለኢንስፔክሽን ፓነሉ ያቀረበው አቤቱታ፤ በጋምቤላ ውስጥ የሚካሄደው የህወሓት/ኢህአዴግ የመሬት ነጠቃና፤ አስገድዶ ሰፈራ፤ የነዋሪውን ሕዝብ መብቶች ገፏል፤ ስደተኞችን ፈጥሯል፤ ሰላማዊውን ህዝብ፤ ከመሬቱ አሳዷል፤ በአዲስ መንደሮች እንዲኖሩ አድርጓል፤ ለዚህ አለም ባንክ የለገሰው፤ በዚህ አመት ቦርዱ ያጸደቀው ስድስት መቶ ሚሊዮን ዶላር “ለህዝቡ ኑሮ ማሻሻያ አልዋለም”፤ ገንዘቡ የት እንደደረሰም አይታወቅም የሚል አቤቱታ ነው። በOctober 9, 2012፣ ፓነሉ አቤቱታውን ተቀብሎ የምርምር ዘገባውን እንደሚጀምር ገልጿል፤ ምርምሩ፤ የመጀመሪያ ሲሆን፤ የመጨረሻ እንደማይሆን እገምታለሁ። በውጭ የምንገኝ ተቆርቋሪወች የአኝዋኮችን አርአያነት፤ ከተባለው ቲንክ ታንክና ከሌሎች ጋር ተባብረን አበዳሪወችና ለጋሶች ሃላፊነት እንዲወስዱ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ተጠያቂ እንዲሆን ለማድረግ መወሰን አለብን። ሙስናና ከህግ ውጭ ገንዘብ ማሸሽ ከልማት አላማ ጋር አይጓዙም ብለን ማሳየት ያለብን፤ ለርዳታ የሚጎርፈው ብዙ ቢሊዮን ዶላር የት እንደ ገባ መጠየቅ አለብን።

አምስተኛ፤ ሁሉን አቀፍ ያልሆነ፤ ለሁሉም እድል የማይሰጥ፤ ውድድርን፤ ነጻነትን፤ መብትን የሚያግድ የፖለቲካ አገዛዝ የሚወልደው ጸረ-ፍትህ፤ ጸረ-ተሳትፎ የሆነ ማህበረሰብንና ኢኮኖሚን ነው። በአንጻሩ ደግሞ፤ ሑሉን አቀፍ የሆነ የፖለቲካ አገዛዝ፤ ፍትሃዊ፤ ተሳትፏዊ፤ ዘላቂነት ያለው ህብረተሰብን፤ እኮኖሚን ይወልዳል። ስለሆነም፤ መጀመሪያ መፈታት ያለበት የፖለቲካው ማነቆ ነው። የግሉን ክፍል እንይ፤

የግሉ ዘርፍ በፍጥነት ካላደገ፤ ፍትህ ከሌለ፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚመስለው፤ በአሁኑ ወቅት የአሜሪካን ህብረተሰብ የሚያነጋግር “አንድ በመቶ versus ዘጠና ዘጠኝ በመቶ” ተብሎ የሚጠራውን በገቢ ታይቶ የማይታወቅ ልዩነት ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ አየጎላ የሚታየው የገቢና የሃብት ልዩነት፤“አንድ በመቶው አብዛኛውን ገቢና ሃብት ይዞታል፤ ዘጠና ዘጠኝ በመቶ የሚሆነው የአሜሪካ ህዝብ ድሃ እየሆነ ነው” ተብሎ የሚነገርለትን የካፒታሊስት መዲና የፈጠረውን ልዩነት አይደለም። የሚመስለው፤ በህዝብ አመጽ፤ በተለይ፤ በወጣቱ ትውልድ አነሳሽነት የተካሄደውንና የተለወጠውን የቱኒሽያን፤ የግብጽን፤ የሊቢያን፤ የየመንን፤ አሁን ደግሞ የሶሪያን፤ የህዝብ ማእበል የሚያመጣ አይነት ነው። ፒራሚዱን ለማሰወገድ፤ አንጡራ ሃብቱን ከውጭ ለማስመለስ፤ የኢትዮጱያ ሕዝብ የስልጣኑ ባለቤት መሆን አለበት።

የወጣቱን ትውልድ እድል ሊያመጣ፤ ሊከፍት፤ ሊያበረታታ የሚችለውን የመገናኛ ቴክኖሎጅ እድል መከልከል በዚህና በተከታታይ ትውልድ ላይ በታሪክ የማይረሳ በደል መፈጸም ነው። ነጻነት፤ ተሳታፎ፤ ተወካይ የሌለበት አገር ዘረፋ ይበዛበታል። ከህግ ውጭ ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ የሚጎርፈው የውጭ ምንዛሪ (ተከታዩ ሰንጠረጅ)፤ ለኢትዪጵያ ወጣት ትውልድ ማጎልመሻ፤ ለመካከለኛው መደብ መልካም ኑሮ ማደሻ፤ ድህነትን ለማጥፋት ለሚደረገው ጉዞ መደጎሚያ፤ ባጭሩ፤ ለሃገራችን እድገት፤ ለሰላምና ርጋታ ሊውል የሚችለው ሃብት ተሰረቀ ማለት ነው። ስርቆቱ፤ሽሽቱ፤ ከቀጠለ፤ ከፒራሚዱ ቁንጮ ያሉትና ወራሾቻቸው ሚሊየኔርና ቢሊየኔር እየሆኑ ይሄዳሉ፤ ሌላው ይህን ዝርፊያ እያየ መቸ ይቆም ይሆን እያለ ይጨነቃል፤ ከጭንቀቱ ተነስቶ ፍትህ መምጣት አለበት፤ ዘረፋ መቆም አለበት የሚልበት ጊዜ እንደሚመጣ ለመጠራጠር ያስቸግራል።

*2009- $3.26 billion፤ 2000-2009 $12 billion፤ በአመት አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር የሚገመተው የገንዘብ ሽሽት፤ በአንድ አመት ከእጥፍ በላይ ሆነ።

ይቀጥላል—October 17, 2012