ከዳር ቆሞ ለዉጥን መጠበቅ የህልም እንጀራ

ፍስሀ እሸቱ (ዶ/ር)

በሀገራችን ያለዉን ሁኔታ ስንመለከተዉ በጥቂት ቃላት ማጠቃለል የቻላል። ይህም ከድጡ ወደ ማጡ የሚለዉ በጥሩ ሁኔታ የሚገልጸዉ ይመስለኛል። አበዉ ጉልቻ ቢለዋወጥ እንደሚሉ አፈናዉ፤ ስለላዉ፤ እስሩ፤ ግድያዉ፤ ስደቱ፤ ዘረፋዉና፤ ማናለብኝነቱ ሳይቋረጥ ቀጥሏል። አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትርና አጋሮቻቸዉም ደግመዉ ደጋግመዉ አስረግጠዉ እንደተናገሩት ለዉጥ የሚባል ነገር እንደማይታሰብና የነበረዉ ሁኔታ ባለበት እንደሚቀጥል ነዉ። ከዚህ አንጻር የለዉጥ የተስፋ ጭላንጭል እንደሌለ በወሬ ብቻ ሳይሆን በተግባራቸዉም አሳይተዉናል። ምንም መራር ቢሆንም እዉነታዉ ግን ስርአቱ መሪዉን ቢያጣ እንኳን፤ በአላማ፤ በአቅም፤ በድርጅትና፤ በስነልቦና፤ ፍጹም የበላይነቱን ተጎናጽፎ ይገኛል።
አበዉ እንደሚሉት አቅሙን የማያዉቅ ሞቱን አፋጠነ እንደሚሉት በተቃዋሚዉ ባንጻሩ የሚታዉ ደሞ፡
1ኛ. እኛ ከወኔ ወኔ የለን፤ መስእዋትነት ለመክፈል ዝግጁነት የለንም
2ኛ. ከአንድነት አንድነት የለን
3ኛ. ከአቅም አቅም የለን
4ኛ. ነጻነትን በምጽዋት ለማግኘት እንፈልጋለን (በዉጭ ሃይሎች)፤ ሌሎች በታገሉትና መስእዋትነት በከፈሉት ተጠቃሚ መሆን እንፈልጋለን
5ኛ. የስርአቱ አራማጆች ወድቆ መነሳትን ሲችሉበት እኛ ግን የወደቅንበት ቀርተናል፤ ከዚህ በፊት በደረሱብን ሽንፈቶች ለምሳሌ በቅንጅት ሽንፈት ተስፋ ቆርጠን ተበታትነናል
6ኛ. ጠላታችን ማን እንደሆነ ማወቅ ተስኖናል፤ ከስርአቱ ይልቅ እርስ በራሳችን ጦር መማዘዙን መርጠናል
7ኛ. በጭንቅላታችን ሳይሆን በስሜታዊነት የምንመራ ሆነናል፤ በአላማ ሳይሆን በጥላቻ ምንመራ ሆነናል
8ኛ. የረዥም ግዜ ዉጤት ሳይሆን አጭር ዉጤት እንፈልጋለን፤ በዚህም ምክንያት ቶሎ ተስፋ እንቆርጣለን
9ኛ. ሁሉም ፈላስፋ፤ አዋቂ፤ መፍትሄ ሰጪ ሆኖ፤ መደማመጥ ጠፍቷል፤ ሁሉም አዋቂ፤ ተናጋሪ፤ ሆኖ የሚታገለዉ ግን ጥቂት ሆኗል – ወሬ ወሬ ወሬ -ሀሜት ሀሜት ሀሜት – ኩነና ኩነና ኩነና – ተናጋኔ ተናጋሪ ተናጋሪ – አድራጊ ጠፋ (የኢንተርኔት፡ ፓልቶክና ሬድዮ፤ ስብሰባ ታጋዮች ሆነናል)
10ኛ. በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አብዛኛዉ ህብረተሰብ ያለዉን ስርአት በአያገባኝም ወይም በፍራቻ ወይንም በጥቅም ተቀብሎ አሜን ብሌ መገዛቱን መርጧል
11ኛ. ከዚህ በፊት በነበሩን ችግሮቻችን ተተብትበን ወደፊት መራመድ ተስኖናል
12ኛ. ሁሉም ጠያቂና ተሳዳቢ እንጂ ደጋፊ፡ አይዞኝ ባይ፤ አብሮ ታጋይ ጠፍቷል
13ኛ. ይሀ ሁሉ በእንዲህ እያለ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፤ ከዚህ በፊት ያልነበረ
አዲሱ ፈሊጥ ደሞ አዲሱን ጠቅላይ ሚንነስትር ጊዜ እንስጠዉ የሚለዉ ሆኗል፤ አይ መዘናጋት፤ ራስን ማታለል፤ ሰዉየዉ እንደሆነ ለዉጥ እንደማይኖር እቅጩን ነግረዉናል።
14ኛ. የመቃወም ትርጉሙ ግራ ገብቶናል መቃወም ማለት ሁሉንም የምንቃወምበት በተለይም አዲስ ሀሳብ አዲስ ራእይ የተለየ አካሄድ ይዘዉ ትግሉን የተቀላቀሉትን እንደጠላት ተረባርበን መማዉገዝና፤ እንደ እባብ ጭንቅላታቸዉን ቀጥቅጠን ያለ የሌለ ሀይላቸንን በመጠቀም አንገታቸዉን እናሰደፋለን፡ ሀሳባቸዉን እንዲሞክሩ እንኳን እድሉን አንሰጣቸዉም። በዚህም ድልን ተግናጽፈን ተደስተን እርስ በእርስ እየተጠፋፋን እንገኛለን።
በኛ ካምፕ
ወይ አንታገል
ወይ አናዋጣ
ወይ ዝም አንል
ወይ አንረዳዳ
ነገሩ ሁሉ ግራ ሚያጋባ ዘመን ላይ እንገኛለን።
ሰላማዊ ሰልፍ ለመዉጣት ልመና
ስብሰባ ለመገኘት ልመና
ለክብር፤ ለህሊና፤ ለነጻነት ለመታገል ለምኑኝ ሚባልበት ዘመን ላይ እንገኛለን።
ባንጻሩ ዘመን ተለዉጦ ስለ እዉነት መቆም፤ ለክብር፤ ለህሊና፤ ለነጻነት ለሀገር መታገል ሚያሳፍርበት፤ ስለነጻነት መናገር ጀግና ወንድ፤ የሀገር ልጅ፤ ሀገር ወዳድ ማስባሉ ቀርቶ፤ እንደ ቁምጥና ሚያሳፍርበትና አንገት የሚያስደፋበት፤ ስለ ክብርም መናገር የሚያስኮንንበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡
ዛሬ ያልታደለችዉ ሀገራችን ኢትዮጵያ ልጆችዎ በሁለት ተከፍለዋል
1. በአንድ ወገን ያለዉ ስርአት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እንዲቀጥል አስተዋጽኦ እያደረጉ ያሉ አብላጫዎቹ (99.999%) ሲሆኑ
በዚህ ምድብ፡
1. የስርአቱ ዋና አራማጆች
2. ስርአቱን በመደገፍ በቆራጥነት የቆሙለት
3. ከማያዉቁት መላክ የሚያዉቁት ሴይጣን ይሻላል ብለዉ በፍራቻና አንገት በመድፋት የተቀመጡ፤
4. ስለ ኢትዮጵያ አያገባንም ከራሳችንና ጥቅማችን በላይ ነፋስ ብለዉ ክብራቸዉን፤ ስብእናቸዉንና፤ ህሊናቸዉን ዘግተዉ ምን ያገባናል ብለዉ የተቀመጡ
5. ሌሎቹ ደግሞ መታገል እየፈለጉ ግን በፍራቻና ከዚህ በፊት በደረሰባቸዉ መከራ እምነት በማጣት ትግሉን እርግፍ አድርገዉ ተስፋ ቆርተዉ የተቀመጡ
6. ባፋቸዉ ተቃዎሚ ነን የሚሉ ነገር ግን ለዘመናት ምንም ለትግሉ ስተዋጽኦ ሳያደርጉ ለመታገል የመጣዉን ሁሉ ነገር ግን በነሱ አመለካከት የማያምነዉን፤ ለነሱ ያላጎበደደዉን፤ ሁሉ በመቃወም የትግሉን ጎራ በማዳከም የስርአቱን እድሜ እያራዘሙ ያሉ የሚገኙበት ሲሆን
2. በሌላ ጎራ ደሞ ቁጥራቸዉ እጅግ አናሳ ቢሆንም ስርአቱን ሌት ተቀን በመታገል በሀገር ቤትና በዉጭ በአላማ ጽናት፤ በወኔ በመታገልና መስእዋትነት እየከፈሉ ያሉ የቁርጥ ቀን ወገኖች ሲሆኑ ዛሬ ቁጥራቸዉ አናሳ ቢሆንም ዉለዉ አድረዉ ግን ማሸነፋቸዉ አይቀሬ ነዉ። ምክንያቱም እዉነት ከነሱ ጋር ናትና። እነዚህም ዛሬ በየጫካዉ ለኛ ነጻነት እየተዋጉ፤ ለኛ ክብር ወህኒ ቤቶች ተወርዉረዉ የሚገኙ፡ ለኛ ክብር ባሉበት ቦታ ሁሉ ለሃገራቸዉ እየታገሉ ያሉትን ጀግና ዜጎች ሁሉ ያካትታል።
እነዚህ ዜጎች ሀገራቸዉን በቁርጥ ቀን ያልከዱ፤ ለእዉነት በመቆማቸዉ ህሊናቸዉን የማይቆረቁራቸዉ፤ ነገ ስማቸዉና ታሪካቸዉ ዘላለማዊ የሆነ፡ ነገ የልጅ ለጆቻችን የሚዘክሩላቸዉ ብርቅዬ ወገኖቻችን ናቸዉ።
ለሀገር የሚያኮራ ስራ ሰርቶ ስምና ዝና አትርፎ ከማለፍ በላይ ምን የሚያስደስት ነገር ይኖራል። ኖሮ ኖሮ በልቶ፤ ተኝቶ፤ ማለፍማ እንኳን ሰዉ ተብዬዉ እንስሳም ያደርገዉ
የለም። ዋናዉ ጥያቄ ግን እያንዳንዳችን የትኛዉ ምድብ ዉስጥ ነን የሚለዉ ሲሆን የህሊናዉን ሙግት ለናነተዉ እተዎለሁኝ።
ከላይ ያለዉን ተጨባጭ ሁኔታ በዝርዝር ካስቀመጥኩኝ ለዉጥ ከልባችን የምንፈልግ ከሆነ መፍትሄዉ ምንድን ነዉ ወደሚለዉ ሁላችንም ወደ ምንጠይቀዉ ጥያቄ እመጣለሁኝ።
1. ለዉጥ ከልባችን እንፈልጋለን ወይ? ? ? የሚለዉ ጥያቄ በእያንዳንዳችን እዉነትኛ ህሊና መልስ ማግኘት አለበት? በእዉነት ለዉጥ እንፈልጋለን ወይ? ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም እንደሚባለዉ – ለዉጥን ከልቡ በጽናት የሚፈልግ ፍላጎቱን ለሟሟላት የማይፈነቅለዉ ድንጋይ ስለማይኖር ዉጤት ማግኘቱ አይቀሬ ነዉ
2. የትግሉን ክብደትና ጥልቀት ማወቅ ይጠበቅብናል በዚያዉም ልክ የአቅማችንን መጠን ማወቅ አለብን – ንቀታችንና ጥላቻችን የትም አላደረሰንም
3. ዉጤት የምንፈልግና አቅማችንን የምናዉቅ ከሆነ ከሆነ ለዉጤቱ የሚፈለግብንን ሁሉ ሳናመነታ ኢንቨስት ማድረግ አለብን፤ ጊዜ፤ገንዘብ፤ጉልበት፤እዉቀት፤ሞራል ወዘተ – ነጻነት በምጽዋት አይመጣም – መሄድ የሚገባንን መንገድ ሁሉ መሄድ ይጠበቅብናል
4. ትግሉ የማንም እንዳልሆነ መገንዘብ ይጠበቅብናል (የእያንዳንዳችን ሃላፊነት ነዉ – ምክንያት ድርደራ የትም አላደረሰንም – ስለትግሉ አዲሱ ፈሊጥ
– እኔ ፖለቲካ ዉስጥ የለሁበትም – ጀግንነት ሆኗል
– የምናምናቸዉ ሰዎች የሉም – እገሌ ማነዉ እሱ
– ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች አይረቡም
– ዉጭ ያለዉ ሐይል ምንም አያደርግም
– ሀገር ቤት ያለዉ ካልተነሳ የትም አንደርስም

ሁሉም ጣቱን ሲጠቋቆም – ትግሉ ግን እያንዳንዳችን ትከሻ ልይ መሆኑን ዘንግተናል። ስለዚህ
– መሪዎቹንና ድርጅቶቹን ካላመናችሁ ግቡና አስተካክሉ
– ወይንም የራሳችሁን ጠንካራ የተሻለ መንገድ አምጡ- ብቻ በዚህም በዚያም ትግሉን ተቀላቀሉ – አማራጩ ሽንፈትን በጸጋ ተቀብለን – አቅማችንን አዉቀን እየታገሉ ያሉትን ትተን አርፈን መቀመጥ ይኖርብናል – እባካችሁ ባንደግፋቸዉ አናዳክማቸዉ
5. የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ሁኔታ የዶሮና የእንቁላል ሆኗል። ህዝቡ ፖለቲካ ድርጅቶች ካልተጠናከሩ ዉጤት ካላሳዩን አንደግፍም ብሎ አኩርፎ ተቀምጧል። እነሱ ደሞ ሊጠናከሩ የሚችሉት ህዝቡ ሲደግፋቸዉ ነዉ። ግራ የሚያጋባ ሁኔታ። ይህ ካልተቀየረና ህዝቡ በተሳትፎ ካላጠናከራቸዉ የትም አይደረስም።
6. ሌላዉ ሁሉም ፖለቲካ ድርጅቶች አንድ ይሁኑ የሚለዉ ለሀያ አመት የተሞከረዉ ፈሊጥ መቼም አይሰራም – አግባብነት የለዉም – ልዩነት የጥንካሬ መሰረት ነዉ – ዋናዉ ቁም ነገር እርስ በእርስ በመጨራረስ የስርአቱን እድሜ አለማራዘም ነዉ። ስርአቱ እጁን አጣምሮ ደስ ሲለዉም የቤት ስራ እየሰጠን የእርስ በእርስ ሽኩቻ ድራማችንን እያየ ይገናል – መፍትሄዉ ቢቻል ተባብረን ካልተቻለም እርስ በእርስ ሽኩቻችንን አቁመን፤ የተሻሉ ናቸዉ የምንላቸዉን በሙሉ ሀይላችን መደገፍ የትግል አቅማቸዉን ማሳደግ ይኖርብናል – በዚያዉም ልክ ማናቸዉንም ተቃዋሚ ሀይሎችን የሚቃወምን ሁሉ ባለ በሌለ ሃይላችን በጋራ ማዉገዝና መዋጋት ይኖርብናል
7. ትግሉ ጊዜ የሚጠይቅ መሆኑን መረዳት በሂደትም መዉደቅና መነሳት መኖሩን መገንዘብ የኖርብናል፤ (ቅንጅት ቅንጅተ እያልን መቀመጡ የት አደረሰን)? አየር ባየር ዉጤት ፈላጊነት የትም አላደረሰንም፤ ዋናዉ ቁምነገር የፈጀዉን ጊዜ ይፍጅ ካላማችን ንቅንቀቀቅ ማለት የለብንም – የኩርፍያ ትግል የትም አላደረሰንም – ያላማ ጽናት ከሌለን አርፈን እንቀመጥ

በዚህ ጉዳይ ብዙ መናገር ለማጠቃለል ያክል ወደድንም ጠላንም
ዉጤት ያለ አዉነተኛ ፍላጎት
ዉጤት ያለ አቅም
ዉጤት ያለ መስእዋትነት
ዉጤት ያለ ጊዜ
በፍጹም አይገኝም፤
ፍላጎት አቅምና መስእዋትነት ሳይከፍሉ ዉጤትን መጠበቅ የዋህነት ነዉ። ይህንንም የያዝነዉን ፈሊጥና ባህል እንካልቀየርን ድረስ ስርአቱም በአሸናፊነቱ መቀጠሉ አይቀሬ ነዉ። የብዙዎቻችን ችግር የትግሉ ድል መፍትሄ በእጅችን ላይ መሆኑን መቀበል አለመፈለጋችን ወይም አለማወቃችን ነዉ። የወደቅነዉ መፍትሄ ከሌላ ቦታ መፈለጋችን ነዉ። ይህ እስካልተወጠ ድረስ ስርአቱ ለዘመናት መግዛቱን እንደማያቆም በእርግጠንነት ላረጋግጥላችሁ። ለዉጥ እንዲመጣ የሚፈልግ ዛሬ ነገ እያለ በቀጠሮ ሳይሆን ከልቡ ለዉጥን የሚፈልግ ከሆነ ዛሬ ካሁኗ ደቂቃ ጀምሮ ለራሱ ለህሊናዉ ለሀገሩ ለወገኑ ቃል መግባት ይኖርበታል። ስለሌላዉ ማሰባችንን ትተን ስለራሳችን እናስብ። በድርጅቶች ችግር አለ ብለን ካሰብን ገብተን እናሻሽላቸዉ፤ አሊያም የኛ አማራጭ የተሻለ ነዉ የምንል ከሆነ የተሻለ ድርጅት መስርተን ትግሉን እንቀላቀል። በዚህም በዚያም ገብተን እንታገል። የትም እንፍጨዉ ዉጤቱን እናምጣዉ።

እኔ ይህንን ስናገር የሽግግር ም/ቤቱ ግቡ ብዬ አይደለም፡ ለእናንተ ትግል ዉስጥ መግባት የድርጅቶች ጥንካሬ ቅድመ ሁኔታ አይደለም ወሳኙ። የራሳችሁ የህሊና ዉሳኔ ነዉ። ያንን የዉሳኔ ደረጃ ካለፋችሁና ለራሳችሁ ቃል ከገባችሁና ያለማወላወል ወደተግባር ከለወጣችሁ ሌላዉ ሁሉ ይስተካከላል። የተገላቢጦሹን ከፈለጋችሁ ግን ምን አለ በሉኝ ምንም ለዉጥ እንደማይመጣ በድጋሚ አረጋግጣለሁ።
ስለዚህ ብቸኛዉ ያለን የአካሄድ ቀመር በግልጽ እንዲህ ነዉ
1. እያንዳንድችን ዛሬ ትግሉን በቆራጥነት መቀላቀልና ሚከፈለዉን መስዋትነት ሁሉ መክፈል፤ በተጨማሪም ትግሉ የወሰደዉን ጊዜም ቢወስድ በቁርጠኝነት ለመታገል መዘጋጀት
2. በግል የትም ለመድረስ ስለማይቻል ያሉትን ድርጅቶች መርምሮ የተሻለ ነዉ የምንለዉን ዛሬዉኑ ተቀላቅሎ በሙሉ ሀይል መግባትና መታገል
ስለዚህ እመኑኝ የድሉ ቁልፍ እያንዳንዳችሁ ናችሁ። ሌላ ምንም አማራጭ የላችሁም።
ይህንን ለማድረግ ከፈቀድንና ለራሳችን በእዉነተኝነት ቃል ከገባን ምንገነባዉ አቅም የምንመኘዉን ዉጤት ይዞልን ይመጣል። ስለዚህ
የፍላጎት አቅም
የዉሳኔ አቅም
የሞራል አቅም
የአላማ ጽናት አቅም
የማቴርያል አቅም
የድርጅት አቅም
ለድላችን ወሳኝ መሆኑን ተረድተን ዛሬ ነግ ሳንል ትግሉን እንቀላቀል። በኛ በኩል እዉነቱን መራራም ቢሆን ተናግረናል፤ ለህሊናችን የሚቆጨን ነገር የለም፡ የህሊና ትግሉን ለናነት ትተናል።

እኛ በራሳችን በኩል የተሻለ ነዉ ያልነዉን አማራጭ አቅርበን ትግላችንን ተያይዘነዋል። በማናቸዉም መንገድ ለማንም ሳንል፤ ለእዉነት ብቻ ብለን፤ ለክብራችን ብለን፤ ለነጻነታችን ብለን፡ ትግሉ ጊዜ እንደማይሰጥ ተረድተን ቀጠሮ ሳንሰጥ የድሉን ጽዋ እስክንጎነጭ፤ ማንም ምንም የበል ምን፤ በቁርጠኝነት እየታገልን እንገኛለን። ልዩነቱ የህሊና እርካታ፤ የመንፈስ የማንነት ጽናትን ሰጥቶናል። ወርቅ በእሳት እንደሚፈተነዉ ችግርና መከራን ለመጋፈጥ ትግሉን በቆራጥነትና በኩራት እያከናወንን እንገኛለን። በስራችንም ኩሩ ኢትዮጵያዉያን እንደምንሆን አንጠራጠርም፤ ለእዉነት በመቆማችንና አምላክም ከቅኖች ጋር በመሆኑ አሸናፊዎች እንደምንሆን ሙሉ እምነት አለን። ከዚህ በላይ ታዲያ ምን የሚያስቀና ነገር ይኖራል።
ሀገራችን ክብራችን፤ የማንነታችን መለያ፤ የነጻነታችን ምልክት ናት። ማንም ይህንን ሊነጥቀን አይገባዉም፤ በትግላችንም የተነጠቅነዉን ማንነታችንን ያለጥርጥር እናስመልሳለን!!!
ድርጅታችንን በለመለከተ ግን አቋማችን ንጥር ያለና ግልጽ ነዉ
1. የማንም ኢትዮጵያዊ ክብርና፤ ነጻነት፤ በማናቸዉም ሁኔታ ሳይሸራረፍ መረጋገጥ ይኖርበታል እንላለን። አምላካችን የሰጠንን መብት ለማንም አሳልፈን አንሰጥም። ስርአቱ የሚሰራዉን ግፍ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እስካላቆመ ድረስ በፍጹም አለማመንታት መቀየር አለበት በሚለዉ አቋማችን ጸንተን ትግላችንን እንቀጥላለን – ይህም ስርአት ሁሉን ኢትዮጵያዊ አካላትን ባካተተ የሽግግር መንግስት እስኪተካ ትግላችንን በጽናት እንቀጥላለን
2. ህዝባዊ የለዉጥ እንቅስቃሴ በመፍጠር ስርአቱን በህዝባዊ ትግል ለመገርሰስና ትግሉን በድል ለማጠናቀቅ ህዝቡ ትግሉን እንዲቀላቀል ትግላችንን ሌት ተቀን እንቀጥላለን
3. ስርአቱም ሲገረሰስ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቅረፍ ቀድሞ መሰናዳት የተሻለና ብልህነትን የተላበሰ ማራጭ መሆኑን ስለምናምን የሽግግር ሂደቱ ምን መምሰል እንደሚኖርበት ቅድመ ዝግጅቶችን እንደርጋለን
4. ይንንኑም ለማከናወን የሚያስችል ድርጅታዊ አቅም እንገነባለን በዚህም አካሄድ ያለማወላወል እንቀጥላለን።
5. ከሌሎች ሁሉም አሁንም እደግመዋለሁ ከሁሉም የተቃዋሚ ሀይሎች ጋር በጋራ እንሰራለን፤ ተቃዋሚ ሀይሎችም በጋራ እንዲሰሩ ማናቸዉንም ሁኔታዎች እናመቻቻለን
ስለዚህ የድርጅታች የነጠረና ግልጽ ያለ አማራጭን ያቀረበ ሲሆን፡ ይሻላል ብላችሁ ካመናችሁ ተቀላቀሉን። አለበለዚያ ሌላ የተሻለዉን ድርጅት ዛሬዉኑ ተቀላቀሉ። አንድ ነገር ላረጋግጥላችሁ ትግሉ ይቀጥላል። ተጠናክሮ ይቀጥላል። ባቡሩን በጊዜ ተቀላቅሎ የለዉጡን ሂደት ማፋጠኑ የናንተ ሀላፊነት ነዉ። በታሪክ ተጠያቂነት ምርጫዉን ለናንተ እተዋለሁ። የሚሻለዉን የጽናት መንገድም አምላክ ያሳያችሁ ዘንድ ሁሌም እጸልያለሁ።

ሀገራችንን ኢትዮጵያን አምላክ ይባርክ!!!