ለዚህ መንግሥት ታላቅ ክብር አለኝ — ሻለቃ ሃይሌ ገ/ሥላሴ

By Goolgule.com

July 24, 2013

haile-gebreselasse

 

የዛሬ 10 ወር የሻለቃ ሃይሌ ገ/ሥላሴ ወደ ፖለቲካ የመምጣት ሁኔታን አስመልክቶ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ሃተታ አቅርቦ ነበር፡፡ (እዚህ ላይ ይመልከቱት) ሰሞኑን አትሌቱ ወደ ፖለቲካው የመግባት ፍላጎቱንና “በምርጫ” ለመወዳደር መፈለጉ ብዙ እየተባለበት ይገኛል፡፡ ከዚህ አንጻር አሁን ላለው ሁኔታ ግንዛቤ ይሰጣል በማለት ከዚህ በፊት ያቀረብነውን ሃተታ በድጋሚ አትመነዋል፡፡


“ለኢትዮጵያ የጥምር መንግስት ያስፈልጋታል” በማለት በ1997 ምርጫ አጥብቆ ሲከራከር የነበረውና በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ደረጃ ኢንቨስትመንት ውስጥ የገባው ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ በኢትዮጵያ ቀደም ሲል ከነበሩት መንግስታትና ትውልዶች ይልቅ አሁን ላለው ትውልድ ከበሬታ እንዳለው በመግለጽ አስተያየቱን ሰነዘረ። የክብር ሪኮርዶቹን በሙሉ ለቀነኒሳ ያስረከበው ሃይሌ በእጁ የሚገኘውን ብቸኛ ሃብቱን (የህዝብ ክብር) እያሟጠጠ መሆኑ እየተገለጸ ነው።

ሃይሌ ይህንን የተናገረው መስከረም 12 ቀን 2004 ዓ ም ከተለያዩ አስተያየት ሰጪዎች ጋር በመንግስት ቴሌቪዥን (ኢቲቪ) አስተያየት በሰጠበት ወቅት ነበር። የቀድሞውን ስርዓትና ትውልድ “ድንጋይ ዳቦ በነበረበት፣ ፍራፍሬ ከጫካ ያለምንም ድካም ከሚሰበሰብበት” ዘመን ጋር ያወዳደረው ሃይሌ፣ “የአሁኑ ትውልድ” በማለት ያሞካሸውን ስርዓት ከተፈጥሮ ጋር ጦርነት በማካሄድ ለውጥ ማስመዝገበ መቻላቸውን አስምሮበታል።

“የባለ ራዕዩ መሪ” አቶ መለስ ገድል ለመዘከር በተዘጋጀ ቅንብር ላይ  በተደጋጋሚ አስተያየት ሲሰጥ የታየው ሃይሌ “አሁን የት ነው ያለነው?” በማለት ጠይቆ “አሜሪካ ኤምባሲ ቪዛ ለማግኘት ነው የምንጋፋው? አውሮፓ ሄደን እዛው ለመቅረት ነው…” በማለት ስደትን መርጠው ከአገራቸው የሚወጡትን ሸርድዶ አልፏል። አሁን ባለው የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ለስደት የሚዳርግ ጉዳይ የለም ወደ ማለት አዝምሞ ተናግሯል። ሃይሌ ይህን ይበል እንጂ በተቃራኒው እስረኞች እንዲፈቱና የፖለቲካ እርቅ እንዲሰፍን እሰራለሁ ከሚሉት ፕሮፌሰር ይስሃቅ ጋር በሽምግልና እያገለገለ መሆኑ በአገሪቱ ውስጥ የሚታው እስርና እንግልት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚጠቅሱ አስተያየት ሰጪዎች የሃይሌን አስተያየት “ለንብረት ዋስትና የሚከፈል የንግግር ቫት” በማለት አጣጥለውታል።

ከኤርትራ ጋር ከተደረገው በቀር በኢትዮጵያ ይህ ነው የሚባል ጦርነት እንዳልተካሔደ ኢህአዴግን የሰላም አባት አስመስሎ ሃይሌ አመልክቷል። በዚሁም ምክንያት ቀደም ሲል ለጦርነት ይውል የነበረው የአገሪቱ በጀት ሙሉ በሙሉ ወደ ልማት ዞሯል ብሏል። የኢህአዴግ ተወካይ መስሎ አስተያየት የሰጠው ሃይሌ “ይህ አሁን የታየው ለውጥ በአስርና አስራ አንድ ዓመት ውስጥ የታየ ነው። አሁን ባለው አካሄድ ከአስር ዓመት በኋላ እንደርሳለን?” ሲል የራሱን ትንቢት አስቀምጧል።

ተቆራርጦ በሚቀርበው አስተያየት እነ ፕሮፌሰር እንድሪያስን በማጀብ ሃይሌ  በመዝገበ ቃላት ላይ ኢትዮጵያን “ረሃብ” በማለት የሚተረጉማት ቃል እንደሚቀየር በልበ ሙሉነት ተናግሯል። “ከሃያ ዓመት በኋላ” አለ ሃይሌ “በመዝገበ ቃላት ላይ የኢትዮጵያ ውርስ ትርጉም ሃብታም በሚል ይቀየራል” ብሏል።

“ድሮ ትረዱን ነበር፤ እናመሰግናለን። አሁን ደግሞ እንረዳችሀዋለን እንላቸዋለን” ሲል አውሮፓና አሜሪካን የመሳሰሉ ታላላቅ አገሮች የኢትዮጵያን እጅ እንደሚናፍቁ ሃይሌ ከምኞት ባለፈ ስሜት ውስጥ ሆኖ ተናግሯል። አገሪቱን ለሃያ አንድ ዓመታት ሲመሩ የነበሩት አቶ መለስ ባልገለጹበት ሁኔታ ሃይሌ ከአስር እስከ ሃያ ዓመት ኢትዮጵያ ሃብታም አገር እንደምትሆን መናገሩ ከምን የመነጨ እንደሆነ ሊገባቸው እንዳልቻለ ብዙዎች እየገለጹ ነው።

“ሙስና ከፍተኛ ደረጃ ደርሷል” ሲል ኢህአዴግን የመከረው ሃይሌ የበታች ባለስልጣናት መንግስትን እንዳያሰድቡ መክሯል። “መንግስት ይህንን አድርጉ ላይል ይችላል” የሚለው ሃይሌ የበታች ባለስልጣኖች የሚፈጽሙት ሙስና “መንግስትን ያስወቅሰዋል” በሚል ተቆርቋሪነቱን በይፋ አስታውቋል። ዋናዎቹን የሙስና ተዋናዮች ነጻ በማውጣት የታች ባለስልጣኖችን “እያንገዋለለ” አሳጥቷቸዋል።

“… ለህሊናቸው ሲሉ እንደ መንግስት በማሰብ መስራት አለባቸው” ሲል ትዕዛዝ አዘል ምክርና ማሳሰቢያ ለበታች ባለስልጣናት ያስተላለፈው ሃይሌ የአስተያየቱ መነሻ ከኢህአዴግ ጋር የፈጠረው ዝምድና ውጤት እንደሆነ እየተነገረ ነው። አንድ አስተያየት ሰጪ “ሃይሌ ሃብቱ እየበዛ ሲሄድና የተበደረው ገንዘብ ሲጨምር ኢህአዴግን ወክሎ መናገር ጀመረ” ብለዋል።

አትሌቶችን ሰብስቦ የአቶ መለሰን ሃዘን ሳግ በያዘው ድምጽ እያለቀሰ የገለጸው ሃይሌ ነፍሳቸውን ይማረውና በአቶ መለስ አይወደድም ነበር። በህይወት እያሉም በተደጋጋሚ ያናንቁት ነበር። ሃይሌን እንደሚያደንቁት ተጠይቀው አርቲስት ቻቺን በማሞገስ ጭራሹኑ እንደማያወቁት ዘለውት አልፈውት ነበር። ኢህአዴግ በተለይም ህወሃት ለሃይሌ ቁብ እንደሌላቸው የሚያውቀው ሃይሌ ከአንድ ማስታወቂያ ሰራተኛ ልቆ በፕሮፓጋንዳ ተግባር ላይ መሰማራቱ በቅርብ ጓደኞቹና በአድናቂዎቹ ዘንድ መነጋገሪያ አድርጎታል።

በአዳማው የኢህአዴግ ጉባኤ ላይ በመገኘት ውድ ሽልማቱን ለሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር በማበርከት የመንግስት ቴሌቪዥን ላይ የታየው ሃይሌ፤ በዚያው ጉባኤ ላይ አቶ መለስንና ኢህአዴግን ማሞገሱ በወቅቱ በርካታ አስተያየት እንዲሰነዘርበት ምክንያት መሆኑ አይዘነጋም። የጎልጉል የአዲስ አበባ መረጃ አቀባይ ያነጋገራቸው እንዳሉት ሃይሌ ወደ ፖለቲካው መንደር በፍጥነት እየተንደረደረ መሆኑን በማስረዳት የሚያውቁትንም ተናግረዋል።

ጣና ሃይቅ ዳርቻ ከልማት ባንክ በአርባ ሚሊዮን ብር የገዛውን ሆቴል ከሁለት ወር በኋላ ሼኽ መሃመድ አላሙዲ በትዕዛዝ እንደነጠቁት በታላቅ ቅሬታ ለህዝብ አስታውቆ የነበረው ሃይሌ የባህር ዳርን ቤተ መንግስት የመጠቅለል ታላቅ ፍላጎት እንዳለው ነው የቅርብ ወዳጁ ለመረጃ አቀባያችን የተናገሩት።

በኦሜድላ ስፖርት ክለብ ውስጥ ሰራተኛ የነበሩትና ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የሃይሌ ቅርብ ሰው “ሃይሌ ቤተመንግስትን ይወዳል። ኢትዮጵያንም የመምራት ህልም አለው” በማለት ጭራሽ ተሰምቶ በማያውቀው ጉዳይ አስተያየታቸውን ይጀምራሉ።

የአማራ ክልል መንግስት ለሲድኒ ኦሊምፒክ ጀግኖች ግብዣ ባደረገበት ወቅት የባህር ዳር ቤተ መንግስት ጎብኝተው እንደነበር አስተያየት ሰጪው ያስታውሳሉ። ሃይሌ የጃንሆይን መኝታ ክፍል ከተመለከተ በኋላ አሰበ። ከአፍታ በኋላ አልጋቸው ላይ ተቀመጠ። አልጋውን ወደ ላይ ወደታች ካወዛወዘው በኋላ “… ይህንን ቤተ መንግስት…” በማለት እንደሚኖርበት መዛቱን አስታውሰው ተናግረዋል።

ሃይሌ ዝም ብሎ እንደማይናገር ያወሱት እኚሁ በቅርብ የሚያውቁት ሰው ሃይሌ ይህንኑ ህልሙን ተግባራዊ ለማድረግ ዘመቻ የጀመረ እንደሚመስላቸው አስታውቀዋል። በቀጣዩ 2005 ምርጫ ሃይሌ እንደሚሳተፍ በርግጠኛነት ተናግረዋል። ሃይሌ ሁለት ጊዜ በግል ፓርላማ ለመግባት እንደሚወዳደር ካስታወቀ በኋላ ባልታወቀ ምክንያት ራሱን ከምርጫ ዘመቻ ማግለሉን መግለጹ ይታዋሳል።

ሃይሌ ፖለቲከኛ የመሆን የኖረ ህልም እንዳለው ያወሱት ባልደረባው ከተናገሩት በተቃራኒ ሃይሌ የፈለገውን መሆንና ማድረግ የግል ውሳኔው እንደሆነ የሚከራከሩለት አልጠፉም። ሃይሌ ሃብት አለው፣ ከፍተኛ ዝና ገንብቷል። ኢትዮጵያዊያን የማይረዱት እውቅናና ክብር በውጪው ዓለም እንዳለው የሚገልጹት ተከራካሪዎች “አንድ ሰው በተናገረ ቁጥር ለንግግሩ ቀንድና ጭራ መቀጠል ነውር ነው። ሰዎች የመሰላቸውን እንዳይናገሩም የሚገድብ ክፉ ልምድ ነው” ባይ ናቸው። “አያይዘውም ሃይሌ የኢህአዴግ አባል ቢሆን እንኳ አስገራሚ አይሆንም” በማለት ጠርዝ ደርሰው ይሟገታሉ።

በርካታ አትሌቶች የኦህዴድ አባላት እንደሆኑ የሚጠቁሙት እነዚህ የሃይሌ ተከራካሪዎች “ሃይሌ ኢህአዴግን ቢቀላቀል መነጋገሪያ የሚሆነው ጉዳይ ብአዴን ወይስ ኦህዴድ ይሆናል የሚለው ነው” ብለዋል። አርሲ የተወለደው ሃይሌ በሩጫ ከተሳካለት በኋላ በተለያዩ ጉዳዮችና መጠነኛ ግንባታ ወደ ባህር ዳር መጠጋጋቱ በትውልድ አካባቢው ተወላጆች ቅሬታ እንዳስነሳበት በተለያዩ ጊዚያቶች መዘገቡ የሚታወስ ነው።