ወያኔ የጋበዛቸዉ የኮሪያ ኤክሰፐርቶች ያለ ባህር በር ማደግ አስቸጋሪ ነዉ አሉ

ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረግ ሽግግርና የባህር በር አለመኖር ፈተና

 

በ   |  ሪፖርተር ጋዜጣ

April 16, 2014

ደቡብ ኮሪያ ከ30 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ አሁን በምትኝበት የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ትገኝ እንደነበር ይነገራል፡፡ ሆኖም የአምስት ዓመት የኢኮኖሚ ልማት ፕሮግራም በመንደፍ በፍጥነት ከድሆች ተርታ በመውጣት በዓለም ላይ ግዙፍ ከሚባሉ ኢኮኖሚዎች አንዷ ለመሆን በቃች፡፡ 

የጀቡቲ ወደብ።    ወያኔ አሰብና ምጥዋን  ለኤርትራ ካስረከበ በኃላ እጅና እግሩ ታስረዋል።
የጀቡቲ ወደብ።  ወደብ አያስፍልግም ባዩ ወያኔ  አሰብና  ምጥዋን  ለኤርትራ  ካስረከበ  በኃላ  እጅና  እግሩ ታስረዋል።

 

ይህንን የሚያውቁ የኢትዮጵያ ሹማምንትም በተለይ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን በኢትዮጵያ መተግበር በጀመሩ ማግስት፣ ደቡብ ኮሪያውያንን ከልማት መንገዳቸው ልምዳቸውን እንዲያጋሩና ዕውቀታቸውን እንዲያካፍሉ ይጠይቃሉ፡፡ በዚህም መሠረት በርካታ የኮርያ ምሁራን ከአራት ዓመት ወዲህ በአዲስ አበባ ከትመው ጥናት ሲያካሂዱና ምክር ሲሰጡ ከርመዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ ደግሞ የኮሪያ ዕውቀት ማካፈል ፕሮግራም ተብሎ የሚጠራው ተቋም አንዱ ነው፡፡ ይህ ተቋም ላለፉት ሁለት ዓመታት ምሁራኑን በኢትዮጵያ የልማት ዕቅዶች ላይ ጥናት እንዲያደርጉ ሲያተጋ ቆይቷል፡፡ በንግድ ሥራ ፈጠራ፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በኢንተርኔት የተደገፈ አገልግሎት አተገባበርና ተጠቃሚነት፣ በግብርና ምርቶች ኤክስፖርት መስፋፋትና በቆዳ ኢንዱስትሪው ላይ በማተኮር ከአንድ ዓመት በላይ ያጠናውን ውጤት በሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡

በንግድ ሥራ ፈጠራ ረገድ ጥናት ያደረጉትና መንግሥትን ሲያማክሩ የቆዩት ሱንግ ዩን ኦህ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ኢትዮጵያ የባህር በር አልባ በመሆኗ ምክንያት በኢንዱስትሪ ለማደግ አልቻለችም፡፡ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች ከባህር ዳርቻ ትይዩ መመሥረት፣ ከማጓጓዣ ወጪ አኳያ ብቻም ሳይሆን በቀላሉ ለማምረት ካለው ምቹነት አኳያም እንደሚታይ ተናግረዋል፡፡ ኦህ እንደሚገልጹት፣ ኢትዮጵያ የባህር በር የሌላት በመሆኑ ምክንያት የወጪና ገቢ ንግዱን በቀላሉ ኢንዱስትሪ መር ለማድረግ ከባድ አድርጎታል፡፡ ‹‹የባህር በር ስለሌላችሁ አዝናለሁ፤›› በማለት ስሜታቸው የገለጹት ኦህ፣ አገራቸው ኮሪያ እ.ኤ.አ. በ1907ዎቹ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎችን ስትመሠረት፣ ማዕከል ያደረገችው የባህር ዳርቻዎቿን እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ምንም የተፈጥሮ ሀብት የሌላት ደቡብ ኮሪያ ከሌሎች አገሮች በምታስገባቸው ጥሬ ዕቃዎች ላይ ጥገኛ ለመሆን ትገደዳለች፡፡ ይህ በመሆኑ ከውጭ በብዛት የምታገባውን ጥሬ ዕቃ ከባህር ዳርቻዎቿ ሳይርቅ በማቀነባበር የወጪ ንግዷን ለማቀላጠፍ የሚያችሉ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎችን በመፍጠር በአሁኑ ወቅት ዓለምን ከሚመሩ 16 ግዙፍ ኢኮኖሚዎች ውስጥ አንዷ ለመሆን በቅታለች፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የሚበጃት መንገድ ከቀላል ኢንዱስትሪ መጀመር እንደሆነ የሚመክሩት ኦህ፣ በቀላሉ ጥሩ ደረጃ ላይ ሊያደርሱ የሚችሉ እንደሞልድ የመሳሰሉ ቀላል ኢንዱስትሪዎችንም ዋቢ አድርገዋል፡፡

በኢትዮጵያ የንግድ ሥራ ፈጠራ የሚገኝበትን ደረጃ የገመገሙት ኦህ፣ በአገራቸው ከ3.2 ሚሊዮን በላይ ጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ከ76 በመቶ ያላነሰ ሠራተኛ በመቅጠር አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ አብራርተዋል፡፡ በኢትዮጵያ በአንፃሩ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሥራ ዕድል መፈጠሩን አስታውሰው፣ ይህ ግን ጊዜዊና በኮንስትራክሽን ዘርፉ የተፈጠረ ዕድል በመሆኑ ለዘላቂነቱ፣ ከንግድ ሥራ መጀመር አንስቶ እስከ ዘላቂው ድረስ ለሥራ ፈጣሪዎች የሚሰጥ የሥልጠናና የመነሻ ካፒታል አቅርቦት በአግባቡ ሊዘረጋ እንደሚገባ በጥናታቸው መክረዋል፡፡

የኮርያ መንግሥት ለንግድ ሥራ ፈጣሪዎች ልዩ የሥልጠና ፕሮግራም አለው፡፡ በፖሊሲ ተደግፎ የሚተገበው ይህ ሥልጠና ከመነሻው የንግድ ሥራ ፈጠራ አካዴሚ የሚል መጠሪያ ያለው ነው፡፡ ምንም እንኳ መደበኛውን የአካዴሚ ቅርፅና ይዘት ባይከተልም፣ ወጣት ጀማሪዎችን ለአንድ ዓመት ያህል በንግድ ሥራ ፈጠራ ዙሪያ እያሠለጠነና ዓመታዊ በጀት እየበጀተ ለሥራ ፈጣሪዎቹ ምቹ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ከአራት ዓመት በፊት ደቡብ ኮሪያ የንግድ ሥራ ፈጣሪዎችን ለምታሠለጥንበት አካዴሚ በዓመት 18 ሚሊዮን ዶላር በጀት ፈሰስ ታደርግ ነበር፡፡ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ለዚህ ተቋም ከ25 ሚሊዮን ዶላር በመመደብ የወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን እያሠለጠነች ትገኛለች፡፡ ከዚህ ባሻገር የንግድ ሥራ ለመጀመር ጫፍ የደረሱ ወጣቶች የመነሻ ጥናትና መሰል ወጪዎችን እንዲሸፍኑበት እስከ 83 ሺሕ ዶላር የሚጠጋ ድጋፍ ትሰጣቸዋለች፡፡

ደቡብ ኮሪያ ተግባራዊ የክህሎት ሥልጠናውን ከቦታ አቅርቦትና በባለሙያዎች በተደገፈ የልምምድ ዕገዛ እንዲሁም ከመንግሥት ብድርና የገበያ ማመቻቸት እንዲደረግላቸው በማድረግ፣ የወጣቶቿን ምናባዊ የንግድ ሥራ ሐሳቦች ተግባር ላይ እንዲውሉ ታደርጋለች፡፡  በዚህ መልኩ ከጅምሩ እንዳይቀጩ ድጋፍ የሚደረግላቸው የኮሪያ ወጣቶች፣ ከመንግሥት ፈንድ እስክ 3.5 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ በብድር እየተመቻቸላቸው የንግድ ሥራቸውን ለገበያ እንዲያቀርቡ ይደረጋል፡፡ በዚህም ሳያበቃ ለዋስትና ከመንግሥት በኩል እስከ 57 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የዋስትና ድጋፍ ለወጣት የንግድ ሥራ ፈጣሪዎች ይሰጣቸዋል፤ በከፍተኛ ኩባንያዎች የገበያ ጫና እንዳይደርስባቸውም ከለላ ይሰጣቸዋል፡፡

በዚህ መልኩ ጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶቿን የምትደግፈው ኮሪያ በኢኮኖሚው ላይ እስከ 50 በመቶ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉላት አስታውቃለች፡፡ እ.ኤ.አ. በ1953 ጠቅላላ ብሔራዊ ገቢዋ 67 ዶላር የነበረ ሲሆን እ.ኤ.አ. በ2012 ግን 22,708 ዶላር መድረሱን ይፋ አድርጋለች፡፡ ኢኮኖሚዋ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ከ300 ዕጥፍ በላይ ተመንድጓል፡፡ ለዚህ ዕድገት ሁነኛ ድርሻ ካላቸው ዘርፎች መካከል የንግድ ሥራ ፈጠራ ፕሮግራም እንደሆነ ተነግሯል፡፡

በዚህ የዕድገት ጉዞ እንድትጓዝ ለኢትዮጵያ ምክር የሚለግሱት ኦህ፣ በመፍትሔ ሐሳብነት ካቀረቧቸው ውስጥ በኢትዮጵያ የሥራ ፈጠራ ሥልጠና ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሮ መሰጠጥ አለበት የሚለው ይገኝበታል፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ተማሪዎች ምርጫቸው በሆነው የሥራ መስክ ላይ እንዲሰማሩ ማድረግ እንደሚበጅ ይመክራሉ፡፡ ይህ የመፍትሔ ሐሳብ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲተገበር ማድረግ ቀላል እንደማይሆን የሚገልጹ ሙያተኞች፣ አንዱ ችግር አገሪቱ የምትከተለው የትምህርት ፖሊሲ እንቅፋት ይሆናል ይላሉ፡፡ መንግሥት 70/30 በሚለው የትምህርት መርህ መሠረት 70 ከመቶ የሳይንስ 30 ከመቶ ደግሞ የማኅበራዊ ሳይንስ የሚል ቀመር በማስቀመጡ ምክንያት የሥራ ፈጠራ ዕድሉንና የሙያ ምርጫ ሜዳውን አጥብቦታል ይላሉ፡፡ ከቀረቡት ሌሎች የመፍትሔ ሐሳቦች መካከል፣ የጎዳና ላይ የሥራ ፈጠራ ትርዒቶችንና የሥራ ፈጠራ የቢዝነስ ዕቅድ ውድድሮችን ማካሄድ ዘርፉን ሊያስፋፋው እንደሚችል ኦህ ይገልጻሉ፡፡

በኮሪያ የአነስተኛና መካከለኛ የንግድ ኮርፖሬሽን መንግሥታዊ ተቋም ውስጥ ለ28 ዓመታት ማገልገላቸውን የተናገሩት ኦህ፣ ከኢትዮጵያ አማካሪ ኩባንያ ጋር በመሆን ያቀረቡት ጥናት አንድ አስገራሚ ውጤትም ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ ይኸውም በአገሪቱ ኢኮኖሚው እያደገ ቢሆንም በአንፃሩ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት የዕድገት መጠን እቀነሰ መምጣቱን ማመላከታቸው ነው፡፡ ይህ ውጤት ምናልባት ከመረጃ አለመሟላት ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ግን ሥጋት አላቸው፡፡ በሌላ በኩል ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ በ2002/2003 ዓ.ም. ባደረገው ዳሰሳዊ ጥናት መሠረት በአገሪቱ የሚገኙት ጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች ብዛት 51,376 ነው፡፡ ሆኖም ከእነዚህ ውስጥ 82 ከመቶው ከአቅማቸው በታች ለመሥራት የተገደዱ ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ የፋይናንስ፣ የገበያ፣ የቴክኖሎጂ፣ የሥልጠናና ሌሎችም ችግሮች አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

በሌላ በኩል በግብርና ውጤቶች ኤክስፖርት ዘርፍም ላይ ኢትዮጵያ ችግሮች አሉባት፡፡ ኢኮኖሚው ከሚገባው በላይ በጥቂት የግብርና ውጤቶች ላይ ጥገኛ መሆኗ አንዱ ችግር ነው፡፡ በተለይ ቡናና የቅባት እህሎች ዋናዎቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ምርቶች ወደውጭ የሚላኩበት የጥራት ደረጃ ዝቅተኛ ነው ያሉት በኮሪያ የገጠር ኢኮኖሚ ኢንስቲትዩትን በመወከል ኢትዮጵያ ላይ ጥናት ያካሄዱት ኤዎር ምዮንግ ኪውን ናቸው፡፡ ኪውን እንደሚያሳስቡት፣ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለውጭ የምታቀርባቸው የግብርና ውጤቶችን በጥሬው ከመላክ ይልቅ ማቀነባበር መቻል እንዳለባት ይመክራሉ፡፡ ኢትዮጵያ በኤክስፖርት ዘርፉ ላይ ተገቢ ዓለም አቀፍ የገበያ መረጃ ስለሌላት የመደራደር ኃይሏን ደካማ አድርጎታል ብለዋል፡፡ በአንፃሩ ደቡብ ኮሪያ የግብርና ውጤቶች የሆኑ የምግብ ምርቶችን ወደ ውጭ ከመላክ እየተቆጠበች እንደምትገኝ ያስታወቁት ኪውን፣ እ.ኤ.አ. በ1970ዎቹ 20 ከመቶ የወጪ ንግድ ድርሻ የነበረው ይህ ዘርፍ፣ በአሁኑ ወቅት አንድ በመቶ ብቻ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይህንን በሚቃረን መልኩ ኮሪያ ለውጭ ገበያ የምታቀርበው የተቀነባበረ ግብርና ነክ የምግብ ውጤት 60 ከመቶ ላይ ይገኛል፡፡ የተቀነባበረ የቀንድ ከብት ሥጋ፣ የዓሳና የስኳር፣ የመጠጥ፣ የሲጋራ ምርቶችን ጨምሮ 12 ያህል የታወቁ የግብርና ዘርፍ ምርቶችን ለዓለም ገበያ የምታቀርበው ኮሪያ፣ ኢትዮጵያም በዚህ መንገድ መጓዝ እንደሚገባት ምሁራኖቿ ይመክራሉ፡፡ ከደቡብ ከሪያ በሚቃረን መልኩ ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከሚላኩ የግብርና ምርቶች ውስጥ የቁም እንስሳት ይገኝበታል፡፡

እንዲህ ዓይነቱን የወጪ ንግድ ኢትዮጵያ በማቆም ወደ ማቀነባበር እንድትገባ ምሁራኑ ይገፋፋሉ፡፡ ይህ ግን ቀላል አልሆነም፡፡ የዓለም ባንክ በቅርቡ ይፋ እንዳደረገው በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከሰሃራ በታች ባሉ አገሮች ውስጥ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ለውጥ ማምጣት አልተቻለም፡፡ ላለፉት 20 ዓመታት ሳያቋርጡ የኢኮኖሚ ዕድገት ቢያስመዘግቡም ኢኮኖሚያቸው የመዋቅር ለውጥ ለማምጣት ብዙ ይቀረዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም የመዋቅር ለውጥ ወይም ኢንዱስትሪያዊ ጉዞን ለመጀመር ጭላጭል እየታየ መሆን ከመግለጽ ውጭ እንዲህ ያለውን ለውጥ ለማምጣት ኢኮኖሚው አቀበት መውጣት እንደሚኖርበት ያምናል፡፡