በሊቢያ ከተሰውት መካከል አያልቅበት ስንታየሁ – እናቴን አደራ

May 11, 2015

By Gheremew Araghaw | Time for Change http://tinyurl.com/n4wq2ad

አያልቅበት ስንታየሁ ሱዳን ውስጥ ለ3 ዓመት ያህል የኖረ የብርሀኑ ጌታነህ ወዳጅ ነው። የሚናፍቃቸውን እና ያላባት ብቻቸውን ያሳደጉትን፤ ለስደቱ ምክንያት የሆኑትን እናቱን ለማየት የዛሬ ዓመት ገደማ ወደ ሀገሩ ተመለሰ።

mother

ሱዳን በነበረበት ወቅት ከራሱ ተርፎ እናቱን ለመርዳት የሚልካት ጥቂት ገንዘብ በስተርጅናቸው ሰው ቤት ተቀጥረው የጉልበት ስራ ከመስራት አላዳናቸውም።

ወይዘሮ አለሚቱ በላይነህ ልጃቸው ሱዳን ሳለ የሚልክላቸው ገንዘብ ከቤት ክራይ ክፍያ ውጪ የማይሸፍንላቸው ቢሆንም፤ ችግራቸውን ለልጃቸው ነግረው ከማሳቀቅ፤ በስተርጅናቸው የጉልበት ስራ ውስጥ ገብተው ኑሮዋቸውን በመከራ ተያይዘው ቆዪ።

የእናቱ ነገር የማይሆንለት አያልቅበት፤ በናፍቆቱ ምክንያት ወደ ሀገሩ ሲመለስ ግን ሱዳን እያለ ይልክ የነበረው ገንዘብ ምን ያህል የእናቱን ህይወት ፈቅ ማድረግ እንደተሳነው ተረዳ።

የዚያን ጊዜ ታድያ ከሱዳን አድማስ ማዶ፤ እናቱን ለመጦር ይችልበት ዘንድ ተስፋ የጣለበትን የባህር ላይ ጉዞ ህልም ሰነቀ።

ለልጆቹ ህይወት በእጅጉ ከሚጨነቀው የረዥም ጊዜ ወዳጁ ብርሀኑ ጌታሁን ጋርም ሀሳባቸው ገጠመ። ወደ ሊቢያም በጋራ ሊሻገሩ ተቃጠሩ። ልጆችን ለማሳደግና እናትን ለመጦር።

 

Ayalkibet Sentayehu

Ayalkibet Sentayehu

 

አያልቅበት በሀምሌ 5፣ 2006 ዓ.ም ወደ ሱዳን ለመመለስ በሚሸኝበት ጊዜ፤ ከዚህ ቀደም በሰላም ደርሶ የተመለሰው ልጃቸው ተመልሶ የሚመጣው መርዶው መሆኑን ፈፅሞውኑ ባይገቱም ካይናቸው ልጃቸው ከሚርቅ በርሀብ ቀድመውት ቢሞቱ መርጠው ነበር።

የብርሀኑ እና አያልቅበት ቀጠሮ ቀን ሲደርስ፤ ብርሀኑ ሚስቱን “ድሬዳዋ ለስራ መሄዴ ነው፤ ስልኬ ግን አይሰራም” ብሎ ሀገሩን ለቆ ወደ ሱዳን አመራ።

በተቀጣጠሩ በስድስት ወራቸው ሱዳን ላይ የተገናኙት እኒህ የልብ ወዳጆች፤ አንዳቸው ስለ ልጅ አንዳቸው ስለ እናት ፍቅር ምስክር ሆነው። ልጆቹን ለናታቸው አደራ ሰጥቶ የተሰደደው፤ ለእናት የሚሰጥ ፍቅር ሀያልነት በአያልቅበት ሲማር፤ ለልጆቹ ሲል የተሰደደው ብርሀኑ ደግሞ በተራው የአባት ፍቅር ምሳሌው ነበር።

ወይዘሮ አለሚቱ፤ አያልቅበት ከሄደ በጝላም ቢሆን የዘወትር ፀሎታቸው የሚወዱት ልጃቸው መንከራተት በቅቶት ከእቅፋቸው ዳግም እንዲገባ ነበር።

የሀገራችን ሰማይ ጠቁሮ፤ ኢትዮጵያም አምርራ በልጆችዎ የግፍ ሞት ስታለቅስ፤ እንደ ብርሀኑ ባለቤት ብርቱካን እና መላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የአያልቅበት እናትም እንባቸውን ይዘረግፉት ነበር። ሊቢያ የማን ሀገር ጎረቤት እንደሆነች እንክዋን የማያውቁት እናት እንዲሁ በደፈናው ልጆቼ ለሚልዋቸው የኢትዮጵያ ሰማዕታት ሁሉ ያነቡ ነበር።

ከሚወደው ወዳጁ ብርሀኑ ጎን በሊቢያ በርሀ አንገቱን ለሰይፍ የሰጠው አያልቅበት ሰማዕትነቱ የተሰማው ዘግይቶ የሁሉም ቤት ሀዘን በመብረድ ላይ ሳለ ነበር።

የእኒህን እናት አይን ለማየት በውነቱ ማን ይደፍር ይሆን? የሀዘናቸውንስ ጥልቀት ምን ይገልፀው ይሆን? በምንስ አይነት መንገድ….?

ዛሬም ቢሆን ስሜቴ ክፉኛ ተጎድቶአል። ገርጂ ከጊዮርጊስ ቤ.ክርስቲያን ጀርባ በምትገኘው ሰማዕቱ ልጃቸው በተከራየላቸው ጠባብ ቤት ውስጥ፤ በብቸኝነት ተኮራምተው፤ አንድያ ልጃቸው ተመልሶ እንደማያዪት ከተረዱ ሳምንት ሳይሞላቸው ያለ አስተዛዛኝ ብቻቸውን የተቀመጡት እናት፤ የሚያነጋግራቸው ዘመድ፣ ሲቦርቁ እያዪ የሚፅናኑባቸው ህፃናት የሌሉበት ጠባብ ቤት ያለመጠን ሰፍቶ ፍርሀት ሲያነግስባቸው፤ ቤታቸው የተሰቀለው ልጃቸውን ከነገዳዩ የሚያሳይ ምስል እያባነነ እንቅልፍ ሲከለክላቸው፤ ይህንን ሁሉ እየሰማን እና ይህን ሁሉ እያየን ዝም የምንል መሆናችን ያሳፍራል። (በእርግጥ ለህዝቡ ማን ነገረው? የመንግስት ሚድያዎች በሌሎች ጉዳዮች ተጠምደዋል። ሀላፊነታቸውን በብርቱ ይወጡ የነበሩ ጋዜጦች እና መጵሄቶች ዛሬ በስራ ላይ የሉም) ዛሬስ እኔም እፍረት በዝቶብኝ አንቆ ሊደፋኝ ደርሶዋል።

አያልቅበት እኮ “የሞተው ሁላችንንም ተክቶ ነው። እሱ እኮ አንገቱን የደፋው የናቱን አንገት ቀና ሊያደርግ ነው።”

በኢትዮጵያ አምላክ እለምናለው አዛውንት እናትና ህፃናት ልጆች አንድ ናቸው። ስደቱም የመጣው ለማሳደግና ለመጦር ነው። እኚህን እናት አጠገባቸው ሄደን እናጽናናቸው። ቀሪ ህይወታቸውንም ወድቀው እንዳይቀሩ እንደግፋቸው።

የሰማዕቱ አያልቅበት ድምጽ ግን ይሰማል። ብቸኛዋን “እናቴን አደራ”።

ለሰማዕቱ አያልቅበት ነፍስ ይማርልን!! እንፀድቅባቸው ዘንድ እናቱንም ትቶልን ከሱ ሰማዕትነት በረከት እንድንሳተፍ እነሆ “እናቴን አደራ” ይለናል።

ከቻሉ በአካል ተገኝተው እናታችንን ያፅናኑ፤ ካልቻሉ ይህን መልዕክት share በማድረግ የሰማዕታቱ ቤተሰቦች መሆናችንን (እንግለጥ።)

አሁንም በድጋሚ እናገራለው። ከብዙ ቃል መግባት ጥቂት ቃልን መፈፀም ዋጋው የላቀ ነው። እግዚአብሔር ይርዳን!!

፨፨፨
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቦሌ ቅርንጫፍ ሂሳብ ቁጥር፦
0173045290500 ለወ.ሮ አለሚቱ በላይነህ
ስ.ቁጥር 0911811070

 

 

 

 

______________________________________________________________________________