በጀርመን የኢትዮጵያውያን የትብብር መድረክ – በፍራንክ ፈርት ከተማ

ሜይ 2 ቀን 2015 ዓመተ-ምህረት ታላቅ ህዝባዊ ስብሰባ አካሄደ፣

May 12, 2015

በእዕቱ እውቁ የኢትዮጵያውያን ሰብዓዊ መብት አቀንቃኝና ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ(አኢጋን) መስራችና መሪ አቶ ኦባንግ ሜቶ እና እውቁ የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ተንታኝና አሰባሳቢ ማንነት በአንድነት መጽሀፍ ደራሲ አቶ የሱፍ ሃሰን በክብር እንግድነት ተገኝተዋል።

Public Meeting In Frankfurt

Public Meeting In Frankfurt

 

 

ስብሰባው በቅርብ በየመን፣ በደቡብ አፍሪካና በሊቢያ ባሰቃቂ ሁኔታ ለተሰዉት ወገኖች የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት በማድረግ የተጀመረ ሲሆን፣ የትብብር መድረኩ ሰብሳቢ አቶ ጌታሁን አሰፋ በመክፈቻ ንግራቸው እዳስረዱት፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የምትገኝበትን የፖለቲካ፣ ማህበራዊ፣ የጎሳና የሃይማኖት ቀውስ፣ እጅ የከፋ ደረጃ ላይ በመድረሱ፣ የዜጎችና የሀገራችን ህልውና አደጋ ላይ ወድቋል ብለዋል። አያይዘውም፣ የዜጎች ሰብዓዊም ሆነ ብሄራዊ መብት ያላግባብ እየተጣሰ በመሆኑ፣ ዜጎች በሀገራቸውም ውስጥ ሆነ በተሰደዱባቸው ሀገራት ለስቃይ፣ ለመከራ እንግልትና ብሎም ሞት እየተዳረጉ ነው ብለዋል። መንግስት ሀዘናቸውን ለመግለጽ አደባባይ በወጡት ዜጎች ላይ በማናለብኝ የወሰደው የሃይል እርምጃ ድርጅታቸው በጥብቅ የሚያወግዘው መሆኑን የገለጹት አቶ ገታሁን፣ ህዝባችን አንድ ቢሆንም ድርጅቶች በሀገራዊ አጀንዳዎች ዙሪያ ባንድ ተማክረው ካልሰሩ ለውጥ ማስመዝገብ አንደማይቻል አስገንዝበዋል። በማያያዝም ይህንን ህልውናችንና ብሄራዊ ማንነታችንም የሚፈታተን ችግር ለማስቆምና ዘለቄታ መፍትሄ ለማበጀት ድርጅቶችም ሆኑ ህዝቡ ልዩነትን አጥቦ በጋራ በአንድነትንና በመቻቻል በመስራት ኢትዮጵያን ማዳን ተገቢ አእንደሆነ ጠቁመው፣ በጀርመን የኢትዮጵውያን የትብብር መድረክ መቋቋም አስፈላጊነትም ይህንኑ ሀገራዊ ተልእኮ ለመወጣት ነው ያሉት ሰብሳቢው፣ የጋራ መድረኩና ዓላማና ተግባር አስርድተዋል። በማያያዝ እንደገለጹት፦ ይህንን አስከፊ ሁኔታ ለመቋቋም እኛ በጀርመን የምንገኝ ኢትዮጵያውያን በመላው ዓለም ከሚገኙ ከሌሎች አቻ ወገኖቻችን ጋር በመሆን፣ ለሀገራችን የሚበጅ ዘለቂታ ያለው መፍትሄ ለማፈላለግና ጸረ-ወያኔ ትግሉን ለማገዝ የተቋቋመ፣ የፖለቲካ፣ የሲቭክ፣ የሃይማኖት ተቋማትና ሀገር ወዳድ ግለሰቦችን ያቀፈ የሲቪክ እንቅስቃሴ እንደ መሆኑ መጠን፣ ማንኛውም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ያገባኛል የሚል ዜጋ ሁሉ ብሄራዊና ሀገራዊ (ኢትዮጵያ ነክ) በሆኑ አጀንዳዎች ዙሪያ ከጋራ መድረኩ ጋር አብሮ እንዲሠራ ለተሰብሳቢው ህዝብና ባካባቢው ለሚንቀሳቀሱ የፖለቲካና የሲቪክ ድርጅቶች፣ የሓይማኖት ተቋማትና ሀገር ወዳድ ግለሰቦች ጥሪ አስተላልፈዋል።

 

የእዕቱ የክብር እንዳ አቶ የሱፍ ያሲንም በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያውያን ታሪካዊ ቀደምትነት እንዳላቸውና በኢትዮጵያዊነት ጥላ ማእቀፍ ስር ለዥም ዘመናት በሉዓላዊነት ስለመኖራቸው፣ እንዲሁም፣ ስለ ምሥራቅ አፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ ህብረተሰብ ታሪካዊ የዘር አመሠራረት፣ ስለ ኢትዮጵያ ቀደምትነትነትና ማንነት ለዘመናት ወደኋላ ተጉዘው ታሪክ እየጠቀሱ በሰፊው ካስረዱ በሁዋላ፣ በዛሬይቱ የኢትዮጵያ፣ የጎሳ ፖለቲካና ማህበረ-ሰባዊ ችግሮች ላይ በዝርዝር ተችተዋል። ጉዳዩን ሲያብራሩ እንዳሉት፣ የወያኔ መንግስት ከሚከተለው የተሳሳተ የፊዴራል አወቃቀርና አስተዳደር አንጻር ያሉትና ሊከሰቱ ይችላሉ ያሏቸውን ስጋቶችና ማህበረ-ሰባዊ ቀውሶች በመጠቆም፣ “ሳንጣላ ተራርቀን፣ ሳንቀራረብ ተራርቀን እንድንኖር እየተደረግን ነው” በማለት ለጉባኤው አስረድተዋል። በማያያዝም፣ ልዩነቶቻችን ለጥንካሬያችን መሠረት ናቸው ያሉት አቶ የሱፍ ያሲን፣ ድክመቱን የሚያሻሽል ክፍተትን መሙላት ይችላል፡፡ በሰለጠነ መንገድና በነፃነት መወያየት ለሃገራችን የሚበጅ መፍትሄ ለማግኘት ዓይነተኛ መንገድ ነው ብለዋል።

 

አቶ የሱፍ ያሲን አሰባሳቢ ማንነት በአንድነት የሚለውን ፍኖት በተመለከተ ሲያስረዱ፣ በማንነት ላይ ከመራኮት ይልቅ አሰባሳቢ አንድነት ላይ ትኩረት በመስጠት መወያየትና ለዚህም እውን መሆን አበክሮ መሠራት እንዳለበት አስገንዝበው፣ በየስብሰባውና ውይይት መድረኩ ያለውን አወዛጋቢነት በተመለከተ፣ አቅጣጫ ለማስያዝ ይረዳ ዘንድ ሀሳባቸውን “አሰባሳቢ ማንነት በአንድነት” በሚል መድብል ማቅረባቸውን አስረዱ። አስቀድሞ ተስማምቶ እኛ እንዲህ እንሁን ብሎ ወስኖ የተመሠረተ ሃገር የለም፣ ነገር ግን እንዲህ መሆን አለበት ብሎ መወያይት ይቻላላል ብለዋል። “ማንነት መለያ ነው” ፣ የሚሉት አቶ የሱፍ፣ የሰው ልጆች ተሰባስበው በየ’ሚኖሩበት አካባቢያቸው ባሻቸው ፊና ተደራጅተው እራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደራቸው በየትኛውም ሃገር ያለና የተለመደ ተግባር ነው፣ ካሉ በሁዋላ፣ ነገር ግን ችግሮች በመሃከላቸው ሲከሰቱ በውይይት እርምትና ማሻሻያ እየተደረገበት ዘለቄታ ያለው መፍታት ማበጀት እንደሚቻል የጀርመንን ተመክሮ በማንሳት አስረድተዋል። “የፌደራል አወቃቀር ለኢትዮጵያ አስፈላጊ ነው” የሚሉት አቶ ያሲን፣ የብዙሃን ይሁንታ የታከለበት ሲሆን ብቻ ነው የብርሃን አቅጣጫ የሚኖረው ብለዋል። በማያያዝም፣ ችግሩ በየአካባቢው እራስ በራስ ማስተዳደር መቻሉ ሳይሆን፣ አብሬ መኖር አልፈልግም የሚል አካል ሲመጣ ነው ብለዋል። በማያያዝም ለእንዲህ አይነቱ ጥያቄ አግባብ ያለው ምላሽ በወቅቱ ሳይሰጥ ሲቀር፣ የሁዋላ የሁዋላ ችግሩ የከፋ ሊሆን ይችላ በማለት በሀገር ውስጥ ቀደም ብለው የተከሰቱትን በሰሜን- ኦሞ የቀጫ ብሄረሰብ ከጋሞ ለመነጠል ያደረገውን፣ ከከጉራጌ ዞን የስልጤ ብሄረሰብ የወሰደውን እርምጃ እንደማሳያ በማንሳት አንስተዋል። በመጨረሻም ከቤቱ ለቀረቡላቸው በርካታ ጥያቄዎች አግባብ ያለው መልስ የሰጡ ሲሆን ፣ ችግሩን ለመፍታት ምን መደረግ አለበት ይላ ተብሎ ለተጠየቁት ጥያቄ ሲመልሱ፦ የተሠሩ ግድፈቶችን ማስተካከል፣ ስልጣን እንድ ቦታ ላይ እንዳይከማች ማድረግና ሁሉም እራሱን በራሱ በእኩልነትና በነፃነት እንዲያስተዳድር መፍቀድ፣ ሁሉንም ዜጎች በእኩልነት ማየት፣ መሰባሰባችን በዜግነት ላይ እንጅ በቋንቋ፣ በሃይማኖትና በዘር መሆን እንደሌለበት፣ ነባርና በአባቶች የተገነባው የጋራ አሰባሳቢ “ኢትዮጵያዊነት” ብቻ እንደመሆኑ መጠን፣ በዚሁ የማንነት ጥላ ስር ተሰባስበን ለሀገራችን የሚበጀውን ለመምከርና ለመስራት ስንችል ብቻ ነው ችግሮቻችን ተጋፍጠን ዘላቂ መፍትሄ ልናበጅለት የምንችለው። ያለውንና የነበረውን ስናከብርና ስንቀበል ወደፊት መራመድ እንችላለን በማለት አስገንዝበዋል።

 

ከአቶ ያሲን የሱፍ በመቀጠል ሰፊ ንግግር ያደረጉት፣ ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ(አኢጋን) ጅርጅት መስራችና መሪ አቶ ኦባንግ ሜቶ ሲሆኑ፣ በንግግራቸው መግቢያ እንደገለጹት ይኸ መንግስት ከወደቀ ሀገር ውስጥ ገብቼ የምሠራው ሥራ አለኝ እሱም ጎንደር ሄጄ የአማርኛ መምህር መሆን ነው፣ በማለት ቋንቋ መግባቢያችን እንጅ የዘር መለያችን ሊሆን እንደማይገባ በቀልድ መልክ ያስገነዘቡት አቶ ኦባንግ፣ ንግግራቸውን በመቀጠል፣ በደቡብ አፍሪካ የመጨረሻው የሞት ሞት የሞቱት የእኛ ልጆች ናቸው ብለዋል። በመቀጠልም፣ ከዚህ የበለጠ ብሄራዊ ውርደት የለም። በኢትዮጵያውያን ላይ ጥቁሮችን ጨምሮ ዓለም ፊቷን ያዞረችበት ወቅት ነው ብለዋል። በተጨባጭ በሊቢያ የተከሰተውን የዜጎች አረመኒያዊ ጭፍጨፋ ባስረጅነት አንስተው፣ የዓለም መገናኛ ብዙሃንም ሆኑ ገዳዮቹ እራሳቸው ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን በይፋ እየገለጹ የኢትያጵያ መንግስት ገና እናጣራለን ማለቱ ዜጎቻችን በሀገራቸው እንኳ ምን ያህል ክብራቸው እየተደፈረ፣ ስብዕናቸው እየተጣሰ መሆኑን ያሳያል በማለት የመረረ ሀዘናቸውን የሲቃ እንባ እየተናነቃቸው ለተሰበሰበው ጉባኤ ልብ በሚነካ አገላለጽ አስረድተዋል። ተሰብሳቢዎችም በበኩላቸው በንግግራቸው እጅግ ከመመሰጣቸውም በላይ በወገኖቻችን ላይ በደረሰው አሰቃቂና እልቂትና በደረሰብን ብሔራዊ ውርደት ሳቢያ በእንባ ሲራጩ ውለዋል።

 

በንጉሱ ዘመን ለትምህርት ወደ አውሮፓ ተልኮ በታሪክ አንድም የቀረ ሰው አልነበረም ዛሬ ግን ይኸ ሁሉ ስደት ለምን…? የሚሉት አቶ ኦባንግ፣ ላስረጅነት በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ለ200.000 ሽህ በላይ ስደተኞች ከየመን መመለሳቸውን ይጠቁማሉ። በማስከተልም፣ በሜዲትራንያን ባሀር ከተጣሉት መካከል ኢትዮጵያውያን ይገኙበታል፣ በየመን የወገን አስከሬን በጎዳና ላይ ወድቆ ለ6 ቀናት ያህል አልተነሳም እበሰበሰ ይገኛል። ወገኖቻችን በገዛ ሀገራቸው ሀዘናቸውን እንኳ ለመግለጽ ሰልፍ ተከልክለዋል ካሉ በሁዋላ፣ እኛ ዛሬ የምናለቅሰው ወገኖቻችንን ስለምንወድ ነው፣ ከሞቱት መካከል ክርስቲያን አለበት፣ እስላም አለበት፣ ኦሮሞ አለበት፣ አማራ አለበት፣ ትግሬ አለበት። አንተም አንችም የህን ጊዜ እዛ ኖራችሁ ቢሆን ኖሮ፣ የናንተ እጣ ሊሆን ይችል ነበር በማለት በምሬት የተናገሩት አቶ ኦባንግ፣ ተበታትነን በየቦታው ከምናልቅ አሁን በቁም ኑ’ እንዋደድ፣ እጅ ለእጅ ተያይዘን እንደጋገፍ፣ የጋራ ችግራችንን በጋራ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ተሰባስበን እንፍታ በማለት፣ ልብ በሚመስጥ አገላለፅ ለሁሉም ዜጎችና ድርጅቶች በአንድነት ሆነን በጋራ ሀገርን ከጥፋት የመታደግ ሥራ ለመሥራት ተባብረን እንቁም የሚል ጥሪ አስተላልፋዋል።

 

አቶ ኦባንግ ንግግራቸውን በማስረዘም፣ ስለችግሮቹ መፍትሄ ሲያስረዱ እንደገለጹት፦ ለሀገራችን ችግር መንስኤው እኛው ነን። ችግራችን በእኛው ተፈጠሮ እኛኑ ሰለባ አድርጎናል ብለዋል። እናም እራሳችንን ካላስከብርን ሌላ ማንም ሊያስከብርልንም ሆነ ሊያከብርልን አይችልም ካሉ በሁዋላ፣ ያለፈውን መለወጥ አንችልም ነገር ግን የመወደፊቱን መለወጥ መቻል አለብን በማለት ለውጥ ከእኛው ከራሳችም መጀመር እንዳለበትና ይኸውም ቀዳሚ እርምጃ ሊሆን እንደሚገባ አጽንኦት በመስተት አስገንዝበዋል። “እኛ ስንወለድ ጉሳ ወይም ሃይማኖት አልነበረንም” የሚሉት አቶ ኦባንግ፣ ዛሬ በጎሳና ሓይማኖት ሰበብ መለያየታችን ለምን ..? ሲሉም ይጠይቃሉ። በማስከተልም፣ የእኛ መለያየት ለወያኔ መንግስት መንሰራፋት ትልቅ እድል ሰጥቶታል። በዚህም ሳቢያ ነው ለዜጎች መብትና ክብር ግድ የሌለው በማለት ከገለጹ በሁዋላ፣ መንግስት የሌለው እኛ ሃገር ብቻ ነው፣ እኛ የምንጠይቀው ስልጣን ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው ብለዋል። ለዚህም ማሳያ በቅርቡ በፈረንሳይ ሀገር 11 የፈረንሳይ ዜጎች በተገደሉበት ወቅት መላው የአውሮፓ መንግስታት መሪዎች በስፍራው ተገኝተው ሃዘናቸውን ገልፀው እንደነበር አስታውሰው፣ ዛሬ በዓለም ላይ የሚታየው የሰው ልጅ እኩልነት አንፃራዊና ከወረቀት ያላለፈ እንዳልሆነ በማሳያነት ተጠቅመዋል። በማያያዝም ለራሳችን ነፃነት፣ መብትና ክብር እኛው እራሳችን ኢትዮጵያውያን ቆርጠን ካልተነሳንና ካልታገልን ከማንም እጅ፣ (የአውሮፓውያን መንግስታትንም ጨምሮ) መብት በነፃ እንደማይታደለን ልናውቅ ይገባል በማለት ካስረዱ በሁዋላ፣ ምንም እንኳ በርካታ ድርጅቶች ቢኖሩም ተገቢውን ሥራ ግን መሥራት አልቻሉም ብለዋል። ሆኖም ግን ያጣነው የፖለቲካ መሪ ሳይሆን የፍቅር መሪ፣ የጥበብ መሪ ነው። ስለሆነም አንድነትና ጠንካራ ተቋም(ድርጅት) ሊኖረን ይገባል፣ እንዲኖርም ድርጅቶችንና ተቋማትን በውል መርዳት ያስፈልጋል ካሉ በሁዋላ፣ ከቤቱ ለቀረቡላቸው በርካታ ጥያቄዎች በሰፋት በማብራራት ተገቢ መልስ ስጥተዋል።

 

በመጨረሻም ተሰብሳቢዎቹ፣ የዜግነት መብትን ለማስከበርና የችግሩ ምንጭ የሆነውን አስከፊ የወያኔ ስርዓት ለመለወጥ በሚደረገው ትግል በጋራ አብሮ ለመቆምና ለመስራት ያሰችላሉ ያሏቸውን ባለ 7 ነጥብ የአቋም መግለጫ ተነቦ የእለቱ ስብሰባ በምሽቲ 3 ሰዓት ላይ ተጠናቋል።

 

 

 

 

______________________________________________________________